ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
መጽሐፍ ቅዱስ በኣል የተባለውን የሐሰት አምላክ ማምለክን መረን የለቀቀ የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር የሚያያይዘው ለምንድን ነው?
የከነዓናውያን አምላክ የነበረው በኣል የመራባት አምላክ ነበር። የበኣል አምላኪዎች እርሻቸው ምርታማ እንዲሆንና ከብቶቻቸው እንዲባረኩ የሚያደርገው በኣል እንደሆነ ያምኑ ነበር። ማነርስ ኤንድ ከስተምስ ኢን ዘ ባይብል የተባለው የማመሳከሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ምድሪቱ ብዙ ምርት እንድትሰጥ ሲባል የኃይለኛ ዝናብ አምላክ የሆነው በኣል እና የእሱ ሚስት የሆነችው አሼራ መለኮታዊ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ለማነሳሳት በቤተ መቅደስ ውስጥ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይፈጸም ነበር፤ [በኣልና አሼራ የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው] ሰብል እንዲትረፈረፍና ከብቶች እንዲባረኩ ያደርጋል።”
ከነዓናውያን በደረቅ ወራት በኣል፣ ሞት በተባለው የድርቅና የሞት አምላክ ተሸንፎ ጥልቅ ወደሆነው የምድር ክፍል እንደሚገባ ያምኑ ነበር። ሆኖም የዝናቡ ወራት መጀመር በኣል ወደ ሥልጣኑ መመለሱን እንደሚያሳይና ይህም እጽዋትና ሕይወት ያላቸው ሌሎች ነገሮች እንዲበዙ እንደሚያደርግ ይታመናል። ከነዓናውያን ይህን ወቅት የሚያከብሩት መረን የለቀቀ የፆታ ግንኙነት በሚፈጸምባቸው ግብዣዎች ነበር። ይህም እስራኤላውያን የፌጎርን በኣል ማምለካቸው “ከሞዓብ ሴቶች ጋር [ወደ] ማመንዘር” የመራቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።—ዘኍልቍ 25:1-3
ኢየሱስ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “ኖራ የተቀቡ መቃብሮች” እንደሚመስሉ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
ኢየሱስ፣ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን ግብዞች እንደሆኑ በመግለጽ ያወገዛቸው ሲሆን “ከውጭ አምረው የሚታዩ ከውስጥ ግን በሙታን አፅምና በብዙ ዓይነት ርኩሰት የተሞሉ፣ ኖራ የተቀቡ መቃብሮችን” እንደሚመስሉ ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 23:27) አይሁዳውያን በዝናቡ ወራት ማብቂያ አካባቢ ይኸውም ፋሲካ ከመከበሩ ከአንድ ወር በፊት በአዳር ወር በ15ኛው ቀን የመቃብሮቹን ድንጋዮች ኖራ የመቀባት ልማድ ነበራቸው፤ ይህንን የሚያደርጉት መቃብሮቹ ጎላ ብለው እንዲታዩ ለማድረግ ሲሉ ነበር። እርግጥ ነው፣ ዝናብ ሲዘንብ ኖራውን አጥቦ ይወስደው ነበር።
ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው መቃብሮቹ የሚቀቡት “በፋሲካ በዓል ወቅት በዓሉን ለማክበር ከተለያየ ቦታ የመጡት በርካታ ሰዎች በመንገዶቹ ላይ ሲተላለፉ መቃብሮቹን በመንካት እንዳይረክሱ ለማድረግ” ነበር። በዘኍልቍ 19:16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሕግ ማንኛውም ሰው፣ በድን ወይም የሰው ዐፅም አሊያም መቃብር ከነካ እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ እንደሚሆን ይገልጻል። በዚህ መንገድ የረከሰ እስራኤላዊ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈል የተከለከለ ሲሆን ይህን ቢያደርግ ግን በሞት ይቀጣ ነበር። (ዘሌዋውያን 15:31) ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው የፋሲካ በዓል ከመከበሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር፤ በመሆኑም አድማጮቹ ኢየሱስ የተናገረውን ሲሰሙ በየዓመቱ የሚደረገው መቃብሮችን ኖራ የመቀባት ልማድ ወዲያው ወደ አእምሯቸው መምጣቱ አይቀርም። ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ፣ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ ከላይ እንደሚታዩት አለመሆናቸውንና ከእነሱ ጋር መነካካት በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚያረክስ መሆኑን ነበር።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከድንጋይ የተቀረጸ የመብረቅ አምላክ የሆነው የበኣል ሐውልት፣ 14ኛው/13ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.
[የሥዕል ምንጭ]
Musée du Louvre, Paris