በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለርዳታ የምጮኸው እስከ መቼ ነው?’

‘ለርዳታ የምጮኸው እስከ መቼ ነው?’

‘ለርዳታ የምጮኸው እስከ መቼ ነው?’

ጄን እያለቀሰች “የምፈልገው ሥቃዩ እንዲቆምልኝ ብቻ ነው!” በማለት ተናገረች። ጄን ካንሰር ያለባት ሲሆን በሽታው በመላ ሰውነቷ እየተሰራጨ ነው። ቤተሰቦቿም ሆኑ ጓደኞቿ በሽታዋን ቢያስወግዱላትና ከሥቃይዋ ቢገላግሏት ደስ ባላቸው ነበር! ይህን ማድረግ ስለማይችሉ አምላክ እንዲረዳት ጸለዩ። ታዲያ አምላክ ይሰማቸው ይሆን? ደግሞስ የእሷ ጉዳይ ግድ ይሰጠው ይሆን?

አምላክ የሰው ልጅ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ጠንቅቆ ያውቃል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ’ ይናገራል። (ሮም 8:22) አምላክ፣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ልክ እንደ ጄን በየዕለቱ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ አሊያም አእምሯዊ ሥቃይ እንደሚደርስባቸው ያውቃል። በየዕለቱ ጦማቸውን የሚያድሩ ወደ 800 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ ይመለከታል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በቤት ውስጥ በሚፈጸምባቸው ዓመፅ ምክንያት እንደሚሠቃዩ እንዲሁም በርካታ ወላጆች የልጆቻቸው ደኅንነትና የወደፊት ሕይወት እንደሚያስጨንቃቸው ያውቃል። ‘አምላክ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ እርምጃ ይወስድ ይሆን’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ? እንዴታ! እኛ እንኳ የምንወዳቸውን ሰዎች የመርዳት ፍላጎት ካለን አምላክ እንደ ቤተሰቡ የሚመለከታቸውን ፍጥረታት የመርዳት ፍላጎት እንዴት አይኖረውም?

እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቀህ የምታውቅ ከሆነ አንተ የመጀመሪያው ሰው አይደለህም። ከዛሬ 2,600 ዓመታት በፊት ዕንባቆም የተባለ አንድ ታማኝ ሰው በዛሬው ጊዜ እንደሚገኙ በርካታ ሰዎች ይሰማው ስለነበር አምላክን እንደሚከተለው በማለት ጠይቆት ነበር፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው? ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል።” (ዕንባቆም 1:2, 3) ዕብራዊ ነቢይ የነበረው ዕንባቆም በዘመኑ አስደንጋጭ የሆኑ የዓመፅ ድርጊቶችንም ሆነ ግጭቶችን ተመልክቷል። በዛሬው ጊዜም ሩኅሩኅ የሆኑ ሰዎች በየዕለቱ እንዲህ ስላሉ ድርጊቶች ስለሚሰሙ ይጨነቃሉ።

ታዲያ አምላክ የዕንባቆምን ጭንቀት አቅልሎ ተመልክቶት ይሆን? በፍጹም። አምላክ፣ ዕንባቆም በቅንነት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ያዳመጠ ከመሆኑም በላይ ተጨንቆ የነበረውን ይህን ሰው አጽናንቶታል እንዲሁም አበረታቶታል። ይሖዋ አምላክ መከራንና ሥቃይን እንደሚያስወግድ ቃል በመግባት የዕንባቆምን እምነት አጠናክሮለታል። አምላክ የተናገረው ተስፋ ያዘለ መልእክት እንደ ጄንና ቤተሰቧ ሁሉ አንተንም ሊያጽናናህ ይችላል። የሚቀጥሉት ርዕሶች ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ፦ አምላክ ስለ እኛ እንደሚያስብ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? መከራንና ሥቃይን ለማስወገድ ምን እርምጃ ይወስዳል? ይህንንስ የሚያደርገው መቼ ነው?