ሕፃኑን ኢየሱስን የጠየቁት በእርግጥ ሦስት ጠቢባን ነበሩ?
አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ
ሕፃኑን ኢየሱስን የጠየቁት በእርግጥ ሦስት ጠቢባን ነበሩ?
በገና ሰሞን በደቡብ አሜሪካ፣ በምሥራቅ አውሮፓና በእስያ ሦስት ነገሥታት ወይም ጠቢባን ለሕፃኑ ኢየሱስ ውድ ስጦታዎችን እንዳመጡለት የሚገልጽ ታሪክ ይወራል። ይሁንና ይህ ታሪክ እውነት ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር ይስማማል? እስቲ ታሪኩን እንመርምር።
ሁለቱ ወንጌሎች ማለትም ማቴዎስና ሉቃስ የኢየሱስን ልደት ዘግበዋል። ከእነዚህ ዘገባዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ ሊጠይቁት የመጡት በአካባቢው የነበሩ ተራ እረኞች ብቻ ነበሩ። ነገሥታት ወይም ጠቢባን እንደሆኑ ተደርገው የሚገለጹት ኮከብ ቆጣሪዎች እንጂ ነገሥታት አልነበሩም፤ ቁጥራቸውም ቢሆን አልተገለጸም። በተጨማሪም እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች ኢየሱስን የጠየቁት በግርግም ውስጥ የተኛ አራስ ሕፃን ሳለ ሳይሆን አደግ ብሎ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመረ በኋላ ነው። እንዲያውም እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመጠየቅ መምጣታቸው የኢየሱስን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎት ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ልደት ያሰፈረውን የሚከተለውን ዘገባ ልብ በል፦ “ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። በድንገት የይሖዋ መልአክ መጥቶ አጠገባቸው ቆመ፤ . . . እንዲህ አላቸው፦ ‘. . . አንድ ሕፃን በመጠቅለያ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።’ . . . በፍጥነትም ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑም በግርግም ተኝቶ ነበር።”—ሉቃስ 2:8-16
በዚህ ወቅት ከሕፃኑ ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ዮሴፍ፣ ማርያምና እረኞቹ ብቻ ነበሩ። በሉቃስ ዘገባ ላይ ከእነዚህ ሌላ የተጠቀሰ የለም።
አሁን ደግሞ በአዲሱ መደበኛ ትርጉም በማቴዎስ 2:1-11 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት፦ “በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም [መጡ] . . . ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩ።”
ዘገባው እነዚህን ሰዎች “ጠቢባን” እንጂ “ሦስት ጠቢባን” በማለት እንዳልገለጻቸው ልብ በል፤ እንዲሁም ሰዎቹ መጀመሪያ የተጓዙት ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም እንጂ ኢየሱስ ወደተወለደባት ወደ ቤተልሔም ከተማ አይደለም። መጨረሻ ላይ ቤተልሔም ሲደርሱ ኢየሱስን ያገኙት በግርግም ተኝቶ ሳይሆን ቤት ውስጥ ሆኖ ነበር።
አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስን ሊጠይቁ የመጡትን ሰዎች “ጠቢባን” በማለት የገለጻቸው ቢሆንም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ኮከብ ቆጣሪዎች” ወይም “ከዋክብት ተመራማሪዎች” ይላቸዋል። ኤ ሃንድቡክ ኦን ዘ ጎስፕል ኦቭ ማቲው የተባለ መጽሐፍ “ጠቢባን” የሚለውን ቃል ሲተረጉም እንዲህ ይላል፦ “በጥንት ጊዜ በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ፋርሳውያን ቀሳውስትን ለማመልከት ይሠራበት የነበረ ግሪክኛ ስም ነው።” በተጨማሪም ዚ ኤክስፓንድድ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ ቃሉን “ጠንቋይ፣ አስማተኛ፣ ምትሃታዊ ኃይል አለኝ የሚል ሰው፣ በጥንቆላ ጥበብ የተካነ ሰው” በማለት ይፈታዋል።
በዛሬው ጊዜ ኮከብ ቆጠራና ጥንቆላ የተለመዱ ነገሮች ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ካሉት ድርጊቶች እንድንርቅ ያስጠነቅቃል። (ኢሳይያስ 47:13-15) ከመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚፈረጁ ስለሆኑ ይሖዋ አምላክ አጥብቆ ይጸየፋቸዋል። (ዘዳግም 18:10-12) በዚህም ምክንያት የትኛውም የአምላክ መልአክ ቢሆን የኢየሱስን መወለድ ለኮከብ ቆጣሪዎች አላበሰረም። ይሁንና አምላክ በሕልም አማካኝነት ክፉ ወደነበረው ንጉሥ ተመልሰው በመሄድ ኢየሱስ ያለበትን እንዳይናገሩ አስጠንቅቋቸዋል፤ ምክንያቱም ንጉሥ ሄሮድስ ኢየሱስን መግደል ይፈልግ ነበር። በመሆኑም “በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመለሱ።”—ማቴዎስ 2:11-16
ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ልደት ጋር በተያያዘ የሚነገረው ከእውነት የራቀ ታሪክ መስፋፋቱን እንዲቀጥል ይፈልጋሉ? መልሱ በጭራሽ የሚል እንደሆነ ጥርጥር የለውም።