በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትምህርት ቤት የደረሰው እልቂትና ሰለባዎቹን ለማጽናናት የተደረገ ጥረት

በትምህርት ቤት የደረሰው እልቂትና ሰለባዎቹን ለማጽናናት የተደረገ ጥረት

በትምህርት ቤት የደረሰው እልቂትና ሰለባዎቹን ለማጽናናት የተደረገ ጥረት

የጋዜጣው ፊተኛ ገጽ ሙሉ በሙሉ ጥቁር ነው። በላዩ ላይ “ለምን?” የሚል አንድ ቃል ብቻ በትልቁ ተጽፎ ነበር። ይህ በደቡባዊ ጀርመን በምትገኘው ቪነንደን በተባለች ከተማ አንድ የ17 ዓመት ወጣት 15 ሰዎችን በጥይት ገድሎ በመጨረሻ ራሱን ካጠፋ በኋላ ሰዎች ሁሉ ሲያነሱት የነበረ ጥያቄ ነው። በዚያን ጊዜ በመላው ጀርመን፣ ባንዲራዎች ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ የተደረገ ሲሆን ይህ አሳዛኝ ዜና በዓለም ዙሪያ በፍጥነት ተሰራጭቷል።

ቪነንደን በወይንና በፍራፍሬ እርሻዋ የምትታወቅ የበለጸገችና ሰላማዊ ከተማ ናት። መጋቢት 11, 2009 ጠዋት ላይ በአልበርትቪል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁሉም ነገር እንደወትሮው ነበር። በ3:30 ላይ ግን ሁኔታው ተለውጦ ድንገት ረብሻና ግርግር ተፈጠረ።

አንድ ወጣት፣ ከወላጆቹ መኝታ ቤት የወሰደውን መሣሪያ ይዞ በንዴት ቀድሞ ይማርበት ወደ ነበረበት ትምህርት ቤት ዘው ብሎ ገባ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በሦስት ክፍሎች ውስጥ እንዲሁም በኮሪደሮች ላይ ያገኛቸውን ዘጠኝ ተማሪዎችና ሦስት አስተማሪዎች ገድሎ ሌሎች ሰዎችን አቆሰለ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፖሊስ በቦታው ደረሰ። በዚህ ጊዜ ገዳዩ ከትምህርት ቤቱ ወጥቶ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የአእምሮ ሕክምና ወደሚሰጥበት ክሊኒክ ገባ። በዚያም አንድ የጥገና ሠራተኛን ገደለ። ከዚያም አንድን አሽከርካሪ መሣሪያ ደግኖበት መኪናውን ጠልፎ ሄደ። አርባ ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ ሾፌሩ እንደምንም ብሎ አመለጠ። በኋላም ታጣቂው በአንድ መኪና መሸጫ ድርጅት ውስጥ ገብቶ አሻሻጩንና አንድ ሌላ ደንበኛን ከገደለ በኋላ ሲከታተሉት ከነበሩት ፖሊሶች ውስጥ በሁለቱ ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰባቸው። በመጨረሻም ፖሊሶች ሊይዙት ሲቃረቡ ጭንቅላቱ ላይ ተኩሶ ራሱን ገደለ።

ይህን መሣሪያ የታጠቀ ወጣት የሚያውቁት ሰዎች፣ ስለ እሱ እንደተናገሩት ከሆነ ወጣቱ በሌሎች ዘንድ መወደድ እንዲሁም ጓደኞች ማፍራት የሚፈልግ እንደማንኛውም ዓይነት ወጣት ነበረ። ታዲያ እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? በዚያን ወቅት ጭንቀት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም በአሻንጉሊት መሣሪያ ወይም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ አንዳንድ ዘግናኝ የኮምፒውተር ጌሞችን የመጫወት ልማድ ይኖረው ይሆናል። ይሁንና አንዳንዶች ‘በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ወጣቶችስ እንዲህ ያደርጉ የለም እንዴ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ምን ዓይነት ሰዎችን ነው የገደለው? የተወሰኑ ሰዎችን ለይቶ ነው የገደለው ወይስ በጅምላ? አንዳንዶች ስምንት ሴቶችን ሲገድል አንድ ወንድ ብቻ የገደለው ለምን ሊሆን እንደሚችል የራሳቸውን መላ ምት ሰንዝረዋል። ይህን በሚመለከት ማንም ሰው ተጨባጭነት ያለው ማብራሪያ ሊሰጥ አይችልም።

ወዲያው የተወሰዱ እርምጃዎች

ሄይከ የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ልጃችን ደውሎ በትምህርት ቤት ውስጥ እየተፈጸመ ስላለው ግድያ ሲነግረኝ ማመን አልቻልኩም። ይሁንና የፖሊስ መኪናዎችና የአምቡላንሶች ድምፅ እየጨመረ እንደመጣ ስሰማ ብርክ ያዘኝ።” ፖሊስ ወደ አካባቢው ቶሎ መድረሱ መሣሪያ የታጠቀው ወጣት ትምህርት ቤት ውስጥ ሌሎች ሰዎችን እንዳይገድል ሳያደርግ አልቀረም። ተማሪዎች ትምህርት ቤቱን ለቅቀው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ነርሶች፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችና ቄሶች ወደ ቦታው በመምጣት ተማሪዎቹን ለመርዳት መሯሯጥ ጀመሩ።

ጋዜጠኞች በአንድ ጊዜ ትምህርት ቤቱን በመውረር ለተማሪዎቹ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ይሞክሩ ጀመር፤ አብዛኞቹ ተማሪዎች ገና ድንጋጤው እንኳ አለቀቃቸውም። አንድ ተማሪ ከትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ቆመው ከነበሩ መኪናዎች መካከል የ26 ቴሌቪዥን ጣቢያ ንብረት የሆኑ 28 መኪናዎችን ቆጥሮ ነበር። በመገናኛ ብዙኃን መካከል የነበረው ፉክክር ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶችን እስከመዘገብ ደርሰዋል። እንዲያውም አንድ ጋዜጠኛ፣ ከተገደሉት ሴቶች ልጆች መካከል ወደ አንደኛዋ ቤት የዚያኑ ዕለት በመሄድ የልጅቷን ፎቶ ግራፍ እንዲሰጡት ቤተሰቧን የጠየቀ ሲሆን ሌሎች ጋዜጠኞች ደግሞ ገንዘብ ከፍለው ተማሪዎቹን ፎቶግራፍ ያነሱ ነበር። አንዳንድ ጋዜጠኞች በግርግሩ ከመጠን በላይ ከመወጠራቸው የተነሳ ከሌሎች ጋዜጠኞች ቀድሞ ዜና ከማግኘትና ለጥቃቱ ሰለባዎች አሳቢነትና አክብሮት ከማሳየት የትኛውን ማስቀደም እንዳለባቸው እንኳ መለየት ተስኗቸው ነበር።

ብዙ ጊዜ እንደሚታየው፣ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ሲፈጠር ሰዎች መጽናኛና ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ወደ ሃይማኖት ተቋማት መሄዳቸው የተለመደ ነገር ነው። እልቂቱ በተፈጸመበት ዕለት የተለያዩ ሃይማኖቶች ቅንጅት ፈጥረው አንድ ዝግጅት አድርገው ነበር። በርካታ ሰዎች የተደረገውን ጥረት አድንቀዋል። ይሁንና ከአምላክ ቃል ማጽናኛ ይፈልጉ የነበሩ ወይም ግራ ላጋቡዋቸው ጥያቄዎች መልስ ይሹ የነበሩ ሰዎች በጣም አዝነዋል። አንድ ቤተሰብ በልጃቸው የክፍል ጓደኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ነበር። እናትየው እንዲህ ብላለች፦ “ቄሱ ኢዮብ ስለደረሰበት ሥቃይ መናገር ጀመሩ። ቀጥለው ምን ትምህርት እንደምናገኝ ያብራራሉ ወይም አንዳንድ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ይናገራሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፤ ግን ምንም ያሉት ነገር የለም። ኢዮብ ሥቃይ ለምን እንደደረሰበትም ሆነ በመጨረሻ ላይ ስላገኛቸው ነገሮች አንዲትም ቃል አልተናገሩም።”

አንድ ሰው በሰማው ትርጉም አልባ ንግግር በጣም ተበሳጭቶ ነበር። ይህ ሰው ከ30 ዓመታት በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምሮ ያቆመ ነበር። አሁን ግን እንደ ገና በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀምሯል።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስ የምታጠና ቫሊዛ የተባለች የ14 ዓመት ወጣት ግድያው ከተፈጸመበት አጠገብ ባለው ክፍል ውስጥ ነበረች። ይህች ልጅ የተኩስ ድምፅ ስትሰማ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረች። በኋላ ሁኔታውን እንዴት እንደተቋቋመችው ስትጠየቅ የተፈጸመው ነገር የመጨረሻዎቹን ቀኖች በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማረችው ነገር ትክክል እንደሆነ እንዳረጋገጠላት ተናግራለች። (2 ጢሞ. 3:1-5) ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች የሚያጽናኑ ቃላትን በመናገር ተጠምደው ነበር። አንዲት አረጋዊ ሴት ወደ እነሱ ቀርበው “ብዙዎች እናንተ እያከናወናችሁት ያላችሁትን ነገር ማድረግ ነበረባቸው” ብለዋል። የደረሰው እልቂት አሳዛኝና አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶች የአምላክ ቃል ለሚሰጠው ተስፋና ማጽናኛ ጆሯቸውን እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።

በቀላሉ ከአእምሮ የማይጠፋ እልቂት

እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ከልብ ተነሳስቶ ምንም ያክል የሚያጽናኑ ቃላትን ቢናገር በእልቂቱ በቀጥታ የተጎዱ ሰዎች የሚሰማቸውን የድንጋጤና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሙሉ በሙሉ ከልባቸው እንዲወጣ ማድረግ አይችልም። ልጁ የተገደለበት ወላጅ ወይም ወደ ትምህርት ቤቱ ሮጦ ሲሄድ ከሞቱት ሰዎች መካከል የእሱም ሚስት እንደምትገኝበት ያወቀ ፖሊስ የሚሰማውን ጥልቅ ሐዘን ሊሽር የሚችል አንድም ቃል የለም።

ከዚህ እልቂት የተረፉ ተማሪዎችም ሆኑ የእነሱ ቤተሰቦች ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሁለቱም ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ደርሶባቸዋል። ቫሲሊዮስ የተባለ አንድ ወጣት፣ ታጣቂው ተኩስ እንደከፈተ ለአደጋ ጊዜ በተዘጋጀው መውጫ ዘሎ ወጣ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ እንዲህ ብሏል፦ “በመስኮት ዘልዬ ስወጣ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። የምሞት መስሎኝ ነበር። ይህ የመጨረሻ ጸሎቴ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ።” ይህ ወጣት በቀጣዮቹ ሳምንታት በቅዠት ይሠቃይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ማንንም ሰው ማነጋገር አይፈልግም ነበር። በተለይ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ስለ እልቂቱ ለመዘገብ ሲሽቀዳደሙ ማየቱ እንዲሁም ዝርዝር ታሪኩን ለመስማት ይጓጉ የነበሩ ሰዎች ለሌሎች ስሜት ምንም ግድ የሌላቸው መሆኑን መመልከቱ በጣም አሳዝኖት ነበር። እርግጥ ከጊዜ በኋላ እውነታውን ተቀብሏል።

ዮናስም ከቫሲሊዮስ ጋር አንድ ክፍል ስለነበር አምስት የክፍሉ ልጆች ሲገደሉ ተመልክቷል። እንዲህ ብሏል፦ “የተከሰተውን ነገር ወዲያውኑ መናገር ምንም አልቸገረኝም ነበር፤ ሁኔታው አስፈሪ ፊልም ይመስል ነበር። አሁን ስለሚሰማኝ ነገር መናገር ግን ለእኔ በጣም ከባድ ነው። ስሜቴ ይለዋወጣል። አንዳንድ ጊዜ ስለ ሁኔታው ማውራት አልፈልግም፤ አንዳንዴ ደግሞ ስለ ሁኔታው በጣም አወራለሁ።” ዮናስም በቅዠትና እንቅልፍ በማጣት ችግር ይሠቃያል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ተማሪዎቹ ዕቃዎቻቸውን ከየክፍሎቻቸው እንዲወስዱ ተደርጎ ነበር። የሥነ ልቦና ሐኪሞች ተማሪዎቹ እንዲህ ያሉ ዕቃዎችን ማየታቸው መጥፎ ትዝታዎችን ሊቀሰቅስባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ዮናስ መጀመሪያ ላይ ጃኬቱን፣ ቦርሳውንና የሞተር ብስክሌት ራስ ቁሩን መንካት እንኳ አልፈለገም። ከዚህም በላይ ታጣቂውን የሚመስል ሰው ወይም ከታጣቂው ጋር የሚመሳሰል ቦርሳ ያዘለ ሰው ባየ ቁጥር በፍርሃት ይሸበር ነበር። ወላጆቹ ፊልም ሲመለከቱ የተኩስ ድምፅ ከሰማ በጣም ይደነግጣል። የሥነ ልቦና ሐኪሞች አንዳንድ ነገሮችን ከእልቂቱ ጋር በማያያዝ የሚሠቃዩ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት አድርገዋል።

የዮናስ አባት ዩርገን የሚሠሩት አንደኛው ሰውዬ በተገደለበት ክሊኒክ ውስጥ ነው። በርካታ ወላጆችና የሥራ ባልደረቦቻቸው ‘ለምን?’ እና ‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ’ እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦችን እያነሱ እንደሚጨነቁ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መሣሪያ የታጠቀው ወጣት ሲገባ የፎቁ በረንዳ ላይ ሆና አይታው የነበረች አንዲት የክሊኒኩ ሠራተኛ ታጣቂው ‘እኔንስ ቢገለኝ ኖሮ’ በሚል ሐሳብ በጣም ከመጨነቋ የተነሳ የሕክምና እርዳታ አስፈልጓት ነበር።

አንዳንዶች የደረሰባቸውን የስሜት ቀውስ እንዲቋቋሙ የተደረገላቸው እርዳታ

አንዳንዶች እንዲህ ያለውን አስደንጋጭ ሁኔታ እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? ዩርገን እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆን ቢችልም ከሌሎች ጋር መሆን ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርግሃል። ብቻህን እንዳልሆንክ ማለትም ሌሎች ሰዎች እንደሚያስቡልህ ማወቅህ ይረዳሃል።”

ዮናስም ሌሎች ላደረጉለት እርዳታ ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎች ካርድና መልእክት ልከውልኛል። አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጠቅሰውልኝ ስለነበር አውጥቼ አንብቤያቸዋለሁ። ይህ በጣም ረድቶኛል።” ዮናስን የረዳው ሌላው ነገር ምንድን ነው? “ሌሊት ከእንቅልፌ ባንኜ ሁኔታው ከአቅም በላይ ሲሆንብኝ እጸልያለሁ። አንዳንድ ጊዜ ሙዚቃ ወይም የንቁ! መጽሔት * ቅጂዎችን አዳምጣለሁ” በማለት ተናግሯል። አክሎም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ነገሮች የሚከሰቱበትን ምክንያት እንደሚነግረን ገልጿል፦ ሰይጣን ዓለምን እየገዛ ሲሆን የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው። የዮናስ አባትም እንዲህ ያለውን ሁኔታ ማወቃቸው ችግሩን እንዲቋቋሙ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

ሥቃይና መከራ በቅርቡ ይወገዳል

በትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት የሚገኘው ቦታ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰዎች በሚያስቀምጡት ሻማ፣ አበባና ደብዳቤ ተሸፈነ። በርካታ ሰዎች በጻፉት ማስታወሻ ላይ ‘ይህ ሁኔታ የተከሰተው ለምንድን ነው? አምላክስ ሁኔታውን ለምን ፈቀደ?’ የሚል ጥያቄ አስፍረው እንደነበር ከርስቲን አስተዋለች። በመሆኑም እነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንደሚያሻቸው ስለተሰማት ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሆና ደብዳቤ በመጻፍ በቦታው ከነበሩት ሌሎች ማስታወሻዎች መካከል አስቀመጠች።

በይፋ በተደረገው የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የከርስቲንን ደብዳቤ ካሳየ በኋላ መጀመሪያ አካባቢ የሚገኘውን ሐሳብ እንዲህ በማለት ጠቀሰ፦ “በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ለምን? የሚለው ጥያቄ በተለይ ደግሞ ‘አምላክ የት ነበር? እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲደርስ የፈቀደውስ ለምንድን ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ እየተነሱ ነው።” የሚያሳዝነው የቴሌቪዥን ጣቢያው ከደብዳቤው ላይ የጠቀሰው ይህን ብቻ ነው።

ታዲያ የሚያሳዝነው ምኑ ነው? ምክንያቱም ደብዳቤው በመቀጠል ሥቃይና መከራ የጀመረው እንዴት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ አምላክ “በሰዎች ምክንያት የመጡትን ችግሮች በሙሉ ያስወግዳል” በማለት ይናገር ነበር። አክሎም እንዲህ ይላል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ላይ አምላክ ከሰዎች ዓይን ላይ እንባን ሁሉ እንደሚጠርግ፣ ከዚያ በኋላ ሞት፣ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ እንደማይኖሩና ቀድሞ የነበሩት ነገሮች እንደሚያልፉ ተናግሯል።” ሌላው ቀርቶ ይሖዋ አምላክ ሙታንን እንኳ ያስነሳል። በቅርቡ በሚመጣው በእሱ መንግሥት ሥር አሳዛኝ ነገር ወይም እልቂት አሊያም ሥቃይና መከራ አይኖርም። አምላክ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።—ራእይ 21:4, 5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.20 በጽሑፍ ታትመው የሚወጡትም ሆኑ በድምፅ የሚቀረጹት የንቁ! መጽሔት እትሞች የሚዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮናስ “ስለ አንተ እናስባለን” የሚል ሐሳብ የተጻፈበት ካርድ ደርሶታል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Focus Agency/WPN

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© imagebroker/Alamy

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Foto: picture alliance

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Foto: picture alliance