በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን”

“በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን”

“በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን”

የይሁዳ ንጉሥ ታላቁ ሄሮድስ፣ ሕፃኑን ኢየሱስን ለማስገደል አስቦ በቤተልሔም የሚገኙ ወንድ ሕፃናትን በሙሉ የሚጨፈጭፉ መልእክተኞች ላከ። ታሪክ “በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን” የተከናወኑ በርካታ ክስተቶችን መዝግቦ አቆይቶልናል፤ እነዚህ ታሪኮች ኢየሱስ ከመወለዱ በፊትም ሆነ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት ስለተፈጸሙት ክንውኖች ያለንን ግንዛቤ ያሰፉልናል።—ማቴዎስ 2:1-16

ሄሮድስ ኢየሱስን የመግደል ፍላጎት እንዲያድርበት ያደረገው ምን ነበር? አይሁዳውያን ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት የራሳቸው ንጉሥ ነበራቸው፤ ታዲያ ኢየሱስ ሲሞት ሮማዊው ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ንጉሣቸው ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሄሮድስ በታሪክ ውስጥ የነበረውን ሚና ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ብሎም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች ስለ እሱ ማወቃቸው ጠቃሚ የሆነበትን ምክንያት ለመገንዘብ ኢየሱስ ከመወለዱ ከአሥርተ ዓመታት በፊት የተፈጸሙትን ሁኔታዎች መለስ ብለን መመልከት ይኖርብናል።

በይሁዳ የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ

በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በመጀመሪያ አጋማሽ ይሁዳ፣ የታላቁ እስክንድር አገዛዝ ከፈረሰ በኋላ ከተመሠረቱት አራት ሥርወ መንግሥታት መካከል በአንዱ ይኸውም ሶርያን በሚያስተዳድረው የሰሉሲድ አገዛዝ ሥር ነበረች። ይሁን እንጂ በ168 ዓ.ዓ. ገደማ የሰሉሲድ ንጉሥ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ይካሄድ የነበረውን የይሖዋን አምልኮ በዙስ ጣዖት አምልኮ ለመተካት በሞከረበት ወቅት በመቃብ ቤተሰብ የሚመሩት አይሁዳውያን ዓመፅ ቆሰቆሱ። መቃብያን ወይም ሃስሞናውያን ከ142 እስከ 63 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ይሁዳን ገዙ።

በ66 ዓ.ዓ. የመቃብያን መሳፍንት የሆኑት ዳግማዊ ኸርኬነስ እና ወንድሙ አሪስቶቡለስ ዙፋን ለመቆናጠጥ እርስ በርሳቸው ተዋጉ። በዚህ ምክንያት የእርስ በርስ ጦርነት የተጀመረ ሲሆን ሁለቱም በወቅቱ በሶርያ ለነበረው ሮማዊ ጄኔራል ፖምፒ የእርዳታ ጥሪ አቀረቡ። ፖምፒ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በጉዳዩ ውስጥ እጁን አስገባ።

ሮማውያን ግዛታቸውን በስተ ምሥራቅ እያስፋፉ ስለነበር በዚህ ወቅት የትንሿን እስያ አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥረው ነበር። ይሁን እንጂ በተከታታይ የተነሱት ደካማ የሶርያ ገዥዎች አካባቢውን ለብጥብጥ ዳርገውት ነበር፤ ይህ ደግሞ ሮማውያን በስተ ምሥራቅ እንዲኖር ይፈልጉት የነበረው ሰላም አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል። በመሆኑም ፖምፒ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሶርያን ለመቆጣጠር አንዳንድ እርምጃዎችን ወሰደ።

ፖምፒ በሃስሞናውያን መካከል ለተከሰተው ግጭት መፍትሔ አድርጎ ያቀረበው ሐሳብ ኸርኬነስን መደገፍ ስለነበር በ63 ዓ.ዓ. ሮማውያን ኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኸርኬነስን ንጉሥ አደረጉት። ይህ ሲባል ግን ኸርኬነስ ራሱን ችሎ ይገዛል ማለት አልነበረም። ሮማውያን አንዴ እጃቸውን ስላስገቡ አካባቢውን ጥሎ መውጣት አልፈለጉም። በሮማውያን ቸርነት የተሾመው ኸርኬነስ ሥልጣኑን እንደያዘ ለመቆየት የእነሱ በጎ ፈቃድና ድጋፍ ያስፈልገው ነበር። የአገር ውስጥ ጉዳዮችን እንደፈቃዱ ማድረግ ቢችልም ከውጭ ጉዳይ ጋር በተያያዙ ነገሮች ላይ ግን የሮማውያንን ፖሊሲ መከተል ነበረበት።

የሄሮድስ አነሳስ

ኸርኬነስ ጠንካራ ገዥ አልነበረም። ስለሆነም የታላቁ ሄሮድስ አባት የሆነው ኤዶማዊው አንቲጳስ ይረዳው ነበር። በሌላ አነጋገር በእጅ አዙር ይገዛ የነበረው አንቲጳስ ነበር። አንቲጳስ የአይሁድ ተቃዋሚ ኃይሎች ይሁዳን እንዳይቆጣጠሩ በማድረግ ሳይውል ሳያድር ይሁዳን ሙሉ በሙሉ እጁ አስገባ። ጁሊየስ ቄሳር ጠላቱ የነበረችውን ግብፅን ሲዋጋ አንቲጳስ ከጎኑ ተሰልፎ ረድቶታል፤ በዚህም ምክንያት ሮማውያን አንቲጳስን ሕጋዊ መብት ያለው አገረ ገዥ አድርገው ሾሙት። በዚህ ጊዜ አንቲጳስ ቀጥተኛ ተጠሪነቱ ለሮማውያን ሆነ። እሱ ደግሞ በበኩሉ ፋሴል እና ሄሮድስ የተባሉ ልጆቹን በኢየሩሳሌምና በገሊላ ላይ ገዥዎች አድርጎ ሾማቸው።

አንቲጳስ፣ ያለ ሮማውያን ፈቃድ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ልጆቹን አሠልጥኗቸው ነበር። ሄሮድስ ይህን ፈጽሞ ዘንግቶ አያውቅም። በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ ለሥልጣን ያበቁትን የሮማውያንንም ሆነ ተገዢዎቹ የነበሩትን የአይሁዳውያንን ጥያቄ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ያስተናግድ ነበር። በማደራጀት ችሎታውና በጦር አዛዥነቱ ያካበተው ተሞክሮ በዚህ ረገድ በእጅጉ ጠቅሞታል። ሄሮድስ በ25 ዓመቱ አገረ ገዥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ሽፍቶችን ከግዛቱ ጠራርጎ በማጥፋት የአይሁዳውያንንና የሮማውያንን አድናቆት ለማትረፍ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።

አንቲጳስ በ43 ዓ.ዓ. በተቀናቃኞቹ በመርዝ ከተገደለ በኋላ ሄሮድስ በመላው ይሁዳ በኃያልነቱ ፈጽሞ ተወዳዳሪ የሌለው ሰው ሆነ። ያም ሆኖ ጠላቶች ነበሩት። የኢየሩሳሌም መሳፍንትና መኳንንት፣ ሄሮድስ ያላግባብ ሥልጣን እንደያዘ ይሰማቸው ስለነበረ ከሥልጣን እንዲያወርዱት ሮማውያንን ለማሳመን ይጥሩ ነበር። ይሁን እንጂ ሙከራቸው አልተሳካም። ሮማውያን የአባቱ የአንቲጳስን ውለታ ያልዘነጉ ከመሆኑም በላይ የእሱን ችሎታ ተገንዝበው ነበር።

በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆኖ ተሾመ

ፖምፒ ከ20 ዓመታት በፊት በሃስሞናውያን መካከል ለተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ መፍትሔ ለማምጣት የወሰደው እርምጃ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር። ያልተሳካላቸው ወገኖች ሥልጣኑን እጃቸው ለማስገባት ተደጋጋሚ ሙከራ ከማድረግ አልተቆጠቡም፤ በመጨረሻም በ40 ዓ.ዓ. የሮማውያን ጠላቶች በነበሩት በፓርታውያን እርዳታ ሊሳካላቸው ችሏል። እነዚህ ሰዎች በሮም ውስጥ የተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን ግርግር ተጠቅመው ሶርያን ከወረሩ በኋላ ኸርኬነስን ከሥልጣን አውርደው ፀረ ሮማውያን አቋም የነበረውን አንድ የሃስሞናውያን ቤተሰብ አባል ሥልጣን ላይ አወጡ።

በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ወደ ሮም የሸሸ ሲሆን በዚያም ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገለት። ሮማውያን ፓርታውያንን ከይሁዳ በማባረር እንዲሁም አካባቢውን እንደገና በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ የራሳቸውን ገዥ መሾም ይፈልጉ ነበር። በዚህ ረገድ እምነት የሚጣልበት ሁነኛ ሰው የማግኘት ፍላጎት ነበራቸው፤ ለዚህ ደግሞ ተስማሚ ሆኖ ያገኙት ሄሮድስን ነው። በመሆኑም የሮም ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሄሮድስን የይሁዳ ንጉሥ አድርጎ ሾመው። ሄሮድስ ሥልጣኑን በእጁ ለማቆየት ሲል ከሚወስዳቸው አቋምን የማላላት እርምጃዎች መካከል ከሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ተነስቶ ለአረማውያን አማልክት መሥዋዕት እስካቀረበበት እስከ ጁፒተር ቤተ መቅደስ ድረስ የመራው ሰልፍ ተጠቃሽ ነው።

ሄሮድስ በሮማውያን ሠራዊት ታግዞ በይሁዳ ያሉትን ጠላቶቹን ድል በማድረግ ዙፋኑን አስመለሰ። ተቃዋሚዎቹን ለመበቀል የወሰደው እርምጃ በጭካኔ የተሞላ ነበር። ሃስሞናውያንንና እነሱን ሲረዱ የነበሩትን አይሁዳውያን መሳፍንትና መኳንንት አልፎ ተርፎም የሮማውያን ወዳጅ በሆነ ገዥ መተዳደራቸው እረፍት የነሳቸውን ሌሎች ወገኖች በሙሉ አጠፋ።

ሄሮድስ ሥልጣኑን አጠናከረ

ከጊዜ በኋላ አውግስጦስ ቄሳር በመባል የሚታወቀው ኦክታቪየስ፣ በ31 ዓ.ዓ. አክሺየም በተባለች ከተማ ማርክ አንቶኒን ድል በማድረግ ያለምንም ተቀናቃኝ የሮማውያን ገዥ ሆነ፤ በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ከማርክ አንቶኒ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነት ስለነበረው በጥርጣሬ ዓይን ሊታይ እንደሚችል ተሰማው። ስለሆነም ሄሮድስ ጊዜ ሳያጠፋ ለኦክታቪየስ ያለውን ታማኝነት ገለጸ። አዲሱ የሮማውያን ገዥም በምላሹ ለሄሮድስ የይሁዳ ንጉሥ መሆኑን ያረጋገጠለት ከመሆኑም በላይ የግዛት ክልሉን አሰፋለት።

በቀጣዮቹ ዓመታት ሄሮድስ፣ ኢየሩሳሌም የግሪካውያን የባሕል ማዕከል እንድትሆን በማድረግ መንግሥቱን አጠናከረ። ከዚያም ቤተ መንግሥቶችንና የወደብ ከተማ የሆነችውን ቂሳርያን በመገንባት እንዲሁም በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ ታላቅ የማስፋፊያ ሥራ በማከናወን ትልቅ ግምት የሚሰጠውን የግንባታ ፕሮጀክቱን ጀመረ። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የሚከተለው ፖሊሲም ሆነ የኃያልነቱ ምንጭ ከሮማውያን ጋር በነበረው ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ነበር።

ሄሮድስ ይሁዳን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ ሲሆን ሥልጣኑም ገደብ የለሽ ነበር። በተጨማሪም ሄሮድስ የፈለገውን ሊቀ ካህናት በመሾም የክህነት ሥርዓቱን እንዳሻው ያሽከረክረው ነበር።

ቅናት ለግድያ አነሳሳው

የሄሮድስ የቤተሰብ ሕይወት ውጥንቅጡ የወጣ ነበር። ከነበሩት አሥር ሚስቶች መካከል አብዛኞቹ ወንዶች ልጆቻቸው አልጋ ወራሽ እንዲሆኑ ይፈልጉ ነበር። በቤተ መንግሥት ውስጥ ይጠነሰስ የነበረው ሴራ ሄሮድስ ተጠራጣሪና ጨካኝ እንዲሆን አድርጎታል። በቅናት ተነሳስቶ ይበልጥ ይወዳት የነበረችውን ማርያምኔ የተባለች ሚስቱን አስገድሏል፤ ከጊዜ በኋላም በእሱ ላይ በማሴራቸው ምክንያት ሁለት ወንዶች ልጆቹን በስቅላት አስገድሏል። ሄሮድስ ተቀናቃኝ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸውን ሰዎች ከማስወገድ የማይመለስ ብሎም የግልፍተኝነት ባሕርይ ያለው ሰው መሆኑ ማቴዎስ በቤተልሔም ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ ከዘገበው ታሪክ ጋር ይስማማል።

አንዳንድ ሰዎች፣ ሄሮድስ ተወዳጅ እንዳልሆነ ስለሚያውቅ በሞቱ ዕለት ሰዎች እንዳይደሰቱ ከዚህ ይልቅ መላው ሕዝብ እንዲያዝን የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ይናገራሉ። ይህን ፍላጎቱን ከግብ ለማድረስ ሲል በይሁዳ የሚኖሩ ታዋቂ ሰዎችን ያሰረ ሲሆን የእሱ ሞት ይፋ በሚሆንበት ዕለት ሁሉም እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። እርግጥ ነው፣ ይህ ትእዛዝ ተግባራዊ አልሆነም።

ታላቁ ሄሮድስ ያተረፈው ስም

ሄሮድስ ሲሞት ሮማውያን ግዛቱን ለአራት በመክፈል አርኬላዎስ አባቱን ተክቶ በይሁዳ ላይ እንዲገዛ ሌሎች ሁለት ልጆቹ ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ መሳፍንት ሆነው እንዲገዙ አደረጉ፤ በዚህ መሠረት አንቲጳስ ገሊላንና ፔሪያን ፊልጶስ ደግሞ ኢጡርያስንና ጥራኮኒዶስን ማስተዳደር ጀመሩ። አርኬላዎስ በተገዥዎቹም ሆነ በሮማውያን ዘንድ ተወዳጅነት አላተረፈም። ለአሥር ዓመት ያህል በዚህ ሁኔታ ከገዛ በኋላ ሮማውያን ከሥልጣኑ አውርደው የራሳቸውን ገዥ ማለትም ከጳንጥዮስ ጲላጦስ በፊት የነበረውን ገዥ ሾሙ። በዚህ ጊዜ ሉቃስ ሄሮድስ ብሎ የገለጸው አንቲጳስና ወንድሙ ፊልጶስ በተሾሙባቸው አውራጃዎች መግዛታቸውን ቀጥለው ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር።—ሉቃስ 3:1

ታላቁ ሄሮድስ ብልህ ፖለቲከኛና ምሕረት የማያውቅ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ ከወሰዳቸው የጭካኔ ድርጊቶች የከፋው ሕፃኑን ኢየሱስን ለማስገደል ያደረገው ሙከራ ሳይሆን አይቀርም። የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ሄሮድስ በታሪክ ውስጥ የተጫወተውን ሚና መመርመራቸው ጥቅም ያስገኝላቸዋል፤ ምክንያቱም ይህ ታሪክ ሮማውያን እንዴት በአይሁዳውያን ላይ መግዛት እንደጀመሩና ኢየሱስ ከመወለዱ በፊትም ሆነ አገልግሎቱን በፈጸመባቸው ዓመታት ምን ነገሮች እንደተከናወኑ በመግለጽ በእነዚያ የታሪክ ዘመናት ስለተፈጸሙት ሁኔታዎች ያላቸውን ግንዛቤ ያሰፋላቸዋል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በሄሮድስ የግዛት ዘመን ፓለስቲና እና በዙሪያዋ የነበሩ አካባቢዎች

ሶርያ

ኢጡርያስ

ገሊላ

ጥራኮኒዶስ

የገሊላ ባሕር

የዮርዳኖስ ወንዝ

ቂሳርያ

ሰማርያ

ፔሪያ

ኢየሩሳሌም

ቤተልሔም

ይሁዳ

የጨው ባሕር

ኤዶምያስ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሄሮድስ ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ሁለት መቶ ዓመታት በይሁዳ ላይ ከተፈራረቁት ገዥዎች አንዱ ነበር