በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጉሥ ዳዊትና ሙዚቃ

ንጉሥ ዳዊትና ሙዚቃ

ንጉሥ ዳዊትና ሙዚቃ

ከዛሬ 3,000 ዓመት በፊት ስለኖረውና ልዩ ሰው ስለነበረው ስለ ዳዊት ስናወሳ በዚያ ዘመን የነበረው ሙዚቃ አብሮ እንደሚነሳ የታወቀ ነው። እንዲያውም በጥንት ዘመን ስለነበረው ሙዚቃ ያለንን እውቀት በአብዛኛው ያገኘነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ከሚገኘው ከዳዊት ታሪክ ይኸውም ወጣት እረኛ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ንጉሥና የተዋጣለት አደራጅ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ካከናወናቸው ነገሮች ነው።

የዳዊትን ታሪክ በመመርመር በጥንቱ ዘመን ስለነበረው ሙዚቃ ብዙ ልንማር እንችላለን። በዚያን ጊዜ ሰዎች ምን ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይጠቀሙ ነበር? እንዴት ዓይነት መዝሙሮችንና ዜማዎችን ይጫወቱ ነበር? እንዲሁም ሙዚቃ በዳዊት ሕይወት ውስጥ ብሎም በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ምን ቦታ ነበረው?

ሙዚቃ በጥንቷ እስራኤል የነበረው ቦታ

የአንድን ዘፈን ወይም መዝሙር ስንኞች ስናስብ በአብዛኛው ዜማው ወደ አእምሯችን መምጣቱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ የበርካታ መዝሙሮችን ግጥሞች የያዘ ቢሆንም ለእነዚህ ግጥሞች የተደረሱት ዜማዎች አይታወቁም። ይሁንና ዜማዎቹ ለጆሮ የሚጥሙና ልብ የሚመስጡ እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። የመዝሙር መጽሐፍ የያዛቸው ግጥሞች የላቀ ደረጃ የሚሰጣቸው ስለሆኑ ዜማዎቹም የግጥሞቹን ያህል ውበትና ጣዕም ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

መጽሐፍ ቅዱስ በዘመኑ ስለነበሩት የሙዚቃ መሣሪያዎች ብዙ ዝርዝር መግለጫ አይሰጥም። ( “በጥንት ዘመን የነበሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሌላው ቀርቶ ዳዊት ይጫወት የነበረው ምን ዓይነት በገና እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። የሆነ ሆኖ እስራኤላውያን ልዩና ውድ የሆኑ ከእንጨት የተሠሩ በገናዎችን ጨምሮ በርካታ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንደፈለሰፉ ማስተዋል ይቻላል።—2 ዜና መዋዕል 9:11፤ አሞጽ 6:5 የ1954 ትርጉም

ይሁንና ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ሙዚቃ በእስራኤላውያን ሕይወት ውስጥ በተለይም ለአምላክ በሚያቀርቡት አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ሙዚቃ በሥርዓተ ንግሥ ላይ፣ በሃይማኖታዊ በዓላት ላይ እንዲሁም በጦርነት ወቅት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በተጨማሪም የቤተ መንግሥት ባለሟሎችን በሙዚቃ ማዝናናት የተለመደ ነበር። ሙዚቃ ሠርግንና የቤተሰብ ግብዣዎችን ያደምቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የእህልና የወይን መከር በዓላት አስደሳች ጊዜያት እንዲሆኑ አስተዋጽኦ አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ በመጥፎ ቦታዎችም ሙዚቃ ይዘወተር ነበር። ከዚህም በላይ ሙዚቃ ሰው የሞተባቸውን ሐዘንተኞች ለማጽናናት ያገለግል ነበር።

ሙዚቃ በእስራኤል የነበረው ሚና ይህ ብቻ አልነበረም። ሙዚቃ አእምሮን የማረጋጋት ባሕርይ እንዳለውና ነቢያት መንፈሳዊ ነገሮችን መቀበል እንዲችሉ እንደሚያዘጋጃቸው ይታመን ነበር። ኤልሳዕ ከይሖዋ መመሪያ የተቀበለው በገና ደርዳሪ የሚጫወተውን ሙዚቃ በሰማበት ጊዜ ነበር። (2 ነገሥት 3:15) በተጨማሪም ሙዚቃ ልዩ ቦታ የሚሰጣቸውን ቀናት ለማብሰር አገልግሏል። ለምሳሌ፣ በዓላትንና የአዲስ ጨረቃን መታየት ለማስታወቅ ሁለት ከብር የተሠሩ መለከቶች ይነፉ ነበር። በኢዮቤልዩ ቀን የሚሰማው የመለከት ድምፅ የባሪያዎችን ነፃነት እንዲሁም የተወረሱ መሬቶችና ቤቶች ለባለቤቱ መመለሳቸውን ያበስራል። በእስራኤል የነበሩ ድሆች ነፃ መውጣታቸውን ወይም ንብረታቸው መመለሱን የሚያበስረውን ሙዚቃ ሲሰሙ ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት አስቸጋሪ አይደለም!—ዘሌዋውያን 25:9፤ ዘኍልቍ 10:10

አንዳንድ እስራኤላውያን የተካኑ ሙዚቀኞች ወይም ዘማሪዎች እንደነበሩ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። አንድ የአሦራውያን ውቅር ምስል፣ ንጉሥ ሰናክሬም ወንድና ሴት ሙዚቀኞችን በግብር መልክ እንዲሰጠው ሕዝቅያስን ጠይቆት እንደነበረ ያሳያል። እነዚህ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሙዚቀኞች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሆኖም በሙዚቃ ጥበብ ዳዊትን የሚደርስበት አልነበረም።

ድንቅ ችሎታ ያለው ሙዚቀኛ

ዳዊትን ልዩ የሚያደርገው ሙዚቀኛ ብቻ ሳይሆን ገጣሚ መሆኑም ጭምር ነው። ከመዝሙራት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሆኑትን የገጠመው ዳዊት ነው። አንድ ፍሬ ልጅ ሳለ እረኛ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው የቤተልሔምን ውብ ገጠራማ አካባቢ በመቃኘት ነበር። አረፋ የሚደፍቁት ጅረቶች የሚያሰሙትን ድምፅ ማዳመጥ እንዲሁም ጠቦቶች ጥሪውን ሰምተው ወደ እሱ ሲመጡ መመልከት የሚሰጠውን ደስታ ያውቃል። በዙሪያው ያለው ተፈጥሮ በሚያሰማው ይህን የመሰለ ውብ “ሙዚቃ” ልቡ ሲመሰጥ እሱም በገናውን አንስቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ አምላኩን ያወድስ ነበር። ዳዊት ለ23ኛው መዝሙር ያቀናበረውን ሙዚቃ መስማት ብንችል ኖሮ ምን ያህል ልባችን ሊነካ እንደሚችል መገመት አያዳግትም!

ዳዊት ወጣት ሳለ በገናውን ጥሩ አድርጎ መጫወት ይችል ስለነበር የንጉሥ ሳኦል አገልጋዮች በቤተ መንግሥት ሙዚቃ እንዲጫወት ለንጉሡ ሐሳብ አቀረቡለት። ሳኦልም በሐሳባቸው ተስማምቶ ዳዊትን ወሰደው። ሳኦል ሲጨነቅና መንፈሱ ሲረበሽ ዳዊት ወደ እሱ ይመጣና በበገናው ውብ የሆነና የንጉሡን አእምሮ የሚያረጋጋ ሙዚቃ ይጫወትለትና ይዘፍንለት ነበር። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ይረጋጋል፤ ጭንቀቱም ቀለል ይልለታል።—1 ሳሙኤል 16:16

ዳዊት በጣም ይወደውና ይደሰትበት የነበረው ሙዚቃ ችግር ያመጣበት ጊዜ ነበር። አንድ ቀን ዳዊትና ሳኦል ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋግተው ሲመለሱ ንጉሡ የድልና የደስታ ዘፈን የሚዘፍኑ ሴቶችን ድምፅ ሰማ። ሴቶቹ “ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገደለ” እያሉ ይዘፍኑ ነበር። በዚህ ጊዜ ሳኦል እጅግ ተቈጣ፤ “ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር።”—1 ሳሙኤል 18:7-9

ሙዚቃ ዳዊትን አነሳስቶታል

ዳዊት በአምላክ መንፈስ መሪነት ያቀናበራቸው መዝሙሮች በብዙ መንገድ የላቀ ደረጃ የሚሰጣቸው ናቸው። ከእነዚህ መካከል ጥልቅ ሐሳብ የሚያስተላልፉና የገጠር ሕይወት የተንጸባረቀባቸው መዝሙሮች ይገኛሉ። ዳዊት ያቀናበራቸው መዝሙሮች በርካታ ርዕሶችን የሚዳስሱ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ውዳሴን፣ ትረካን፣ ትዝታንና በወይን መከር ጊዜ የሚኖረውን ደስታ ብሎም የቤተ መንግሥትን ምረቃ ደማቅ ሥነ ሥርዓት እንዲሁም ተስፋን፣ ልመናንና ምልጃን የሚገልጹ ነበሩ። (መዝሙር 32, 23, 145, 8, 30, 38, 72, 51, 86 እንዲሁም በመዝሙሮቹ አናት ላይ የተጻፉትን መግለጫዎች ተመልከት።) ሳኦልና ልጁ ዮናታን በሞቱበት ወቅት ዳዊት “የቀስት እንጕርጕሮ” ተብሎ የተጠራ የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ። “እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቶአል” በሚሉት ቃላት የሚጀምረው የሐዘን እንጉርጉሮ የትካዜ መንፈስ ያዘለ ነበር። ዳዊት በቃላት እንዲሁም በገናውን ተጠቅሞ በሚጫወተው ሙዚቃ አማካኝነት የተለያዩ ስሜቶችን ልብ በሚነካ መንገድ መግለጽ ያውቅበት ነበር።—2 ሳሙኤል 1:17-19

ዳዊት ደስተኛ ሰው ስለነበር የደስታ መንፈስ የተንጸባረቀበት ሞቅ ያለ ሙዚቃ ይወድ ነበር። የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ጽዮን ባመጣበት ጊዜ ከደስታው የተነሳ በሙሉ ኃይሉ ይዘልና ይጨፍር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በወቅቱ የነበረው ሙዚቃ ስሜት ቀስቃሽ እንደነበረ ይጠቁማል። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ይህ አጋጣሚ ከሚስቱ ከሜልኮል ጋር እንዲጋጭ ቢያደርገውም ዳዊት ይህን ከምንም አልቆጠረውም። ይሖዋን ይወዳል፤ ሙዚቃውም በጣም አስደስቶታል፤ ይህም በአምላኩ ፊት እንዲጨፍር አነሳስቶታል።—2 ሳሙኤል 6:14, 16, 21

የዳዊት ችሎታ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ዳዊት አዳዲስ ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመሥራትም ይታወቅ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 7:6) በአጠቃላይ ሲታይ ዳዊት ልዩ ተሰጥኦ የነበረው የሥነ ጥበብ ሰው ሲሆን የሙዚቃ መሣሪያ ከመሥራት በተጨማሪ ገጣሚ፣ ሙዚቃ አቀናባሪና ተጫዋች ነበር። ይሁንና የዳዊት ሥራ በዚህ አያበቃም።

ሙዚቃና መዝሙር—በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ

ዳዊት ካከናወናቸው ታላላቅ ነገሮች አንዱ በይሖዋ ቤት ውስጥ የሙዚቃና የመዘምራን ቡድኖችን ማደራጀት ነው። አሳፍን፣ ኤማንን እና ኤዶታምን (ኤታን ተብሎም ሳይጠራ አይቀርም) በ4,000 መዘምራንና ሙዚቀኞች ላይ ሾማቸው። ከዚያም 288 የሙዚቃ ባለሙያዎችን አምጥቶ እነዚህን ሙዚቀኞችና መዘምራን እንዲያሠለጥኑና እንዲመሩ ዝግጅት አደረገ። እነዚህ 4,000 ሙዚቀኞችና መዘምራን ሦስቱ ታላላቅ ዓመታዊ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት በቤተ መቅደሱ ይገኙ ነበር። ይህ ታላቅ የመዘምራን ቡድን ምን ያህል ውበትና ድምቀት ያለው መዝሙር ሊዘምር እንደሚችል መገመት ይቻላል!—1 ዜና መዋዕል 23:5፤ 25:1, 6, 7

በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚዘምሩት ወንዶች ብቻ ነበሩ። በ⁠መዝሙር 46 አናት ላይ የሚገኘው “በደናግል የዜማ ስልት” የሚለው ሐሳብ በቀጭን ድምፅ የሚዘመር ወይም ቀጭን ድምፅ በሚያወጣ የሙዚቃ መሣሪያ የሚታጀብ መዝሙር እንደነበር ይጠቁማል። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 5:13 ‘ዘማሪዎች በአንድነት’ እንደዘመሩ ስለሚናገር ድምፃቸው የአንድ ሰው ድምፅ እስኪመስል ሕብረት ነበራቸው ማለት ነው። ሦስተኛው መዝሙር እና ሌሎች በርካታ የዳዊት መዝሙሮች ውብ ጣዕመ ዜማ የነበራቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። አንዳንድ መዝሙሮች ደግሞ በ⁠መዝሙር 42:5, 11 እና 43:5 ላይ እንደሚገኘው ያለ አዝማች አላቸው። ሁለት የመዘምራን ቡድኖች ወይም ሁለት ሰዎች እየተቀባበሉ የሚጫወቷቸው ዜማዎችም በጣም ተወዳጅ ነበሩ። ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ጽዮን ባመጣበት ጊዜ እንደተቀናበረ የሚገመተው 24ኛው መዝሙር ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናል።—2 ሳሙኤል 6:11-17

ይሁንና መዘመር ለሌዋውያን ብቻ የተሰጠ መብት አልነበረም። እስራኤላውያን ለዓመታዊ በዓላት ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጡ በጉዞ ላይ ሆነው ይዘምሩ ነበር። “መዝሙረ መዓርግ” የሚለው መግለጫ ትርጉም ይህ ሳይሆን አይቀርም። (መዝሙር 120 እስከ 134) ለምሳሌ፣ ዳዊት በ133ኛው መዝሙሩ ላይ፣ እንዲህ ባሉት ጊዜያት በእስራኤላውያን መካከል ይታይ የነበረውን የወንድማማች ፍቅር በአድናቆት ስሜት ገልጾታል። የመዝሙሩ የመክፈቻ ስንኝ እንዲህ ይላል፦ “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” ዳዊት ለዚህ ግጥም የደረሰው ዜማ ምንኛ ውብ ይሆን!

ሙዚቃና የይሖዋ አምልኮ

አንድ አሥረኛ የሚያህለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መዝሙር ሲሆን የመዝሙር መጽሐፍ ሁሉም ሰው አምላክን እንዲያወድስ ያበረታታል። (መዝሙር 150) ሙዚቃ አንድ ሰው የሚያስጨንቁትን ነገሮች እንዲረሳ የማድረግ ኃይል አለው። እንዲሁም መዘመር፣ ሕመምን እንደሚያስታግስ ዘይት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልባቸው ደስ የተሰኘ ሰዎች መዝሙር እንዲዘምሩ ያበረታታል።—ያዕቆብ 5:13

መዝሙር መዘመር አንድ ሰው ለአምላክ ያለውን ፍቅርና እምነቱን መግለጽ የሚችልበት መንገድ ነው። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው ምሽት ምግብ ከተመገቡ በኋላ መዝሙር ዘምረዋል። (ማቴዎስ 26:30) በአምላክ ዙፋን ፊት የሚዘመረውን ውብ መዝሙር የሚያውቀው የዳዊት ልጅ ኢየሱስ እንዴት ያለ ልዩ ድምፅ ይኖረው ይሆን! ኢየሱስና ሐዋርያቱ የዘመሩት ከመዝሙር 113 እስከ 118 ላይ የሚገኙትን በዕብራይስጥ የሃሌል መዝሙሮች የሚባሉትን ሳይሆን አይቀርም። እነዚህን መዝሙሮች ዘምረው ከነበረ ኢየሱስ፣ በቅርቡ ምን ሊከሰት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ካልተረዱት ሐዋርያቱ ጋር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ዘምሮ መሆን አለበት፦ “የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና፣ እግዚአብሔርን ወደድሁት። . . . የሞት ወጥመድ ያዘኝ፤ የሲኦልም ጣር አገኘኝ፤ . . . ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ታድናት ዘንድ እለምንሃለሁ።’”—መዝሙር 116:1-4

ሙዚቃ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሙዚቃና መዝሙር በሰማይ እንደተሰማ የሚገልጽ ሲሆን መንፈሳዊ ፍጥረታት ምሳሌያዊ በገና ይዘው በይሖዋ ዙፋን ፊት የውዳሴ መዝሙር እንደዘመሩ ይናገራል። (ራእይ 5:9፤ 14:3፤ 15:2, 3) ሰዎች ለሙዚቃ ፍቅር ሊኖራቸው የቻለው ይሖዋ አምላክ በልባቸው ውስጥ የሙዚቃ ፍቅር ስለተከለ እንዲሁም ስሜታቸውን የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወት ወይም በዜማ አማካኝነት የመግለጽ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ስለፈጠራቸው ነው። ለአንድ የእምነት ሰው ደግሞ ሙዚቃ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው።—ያዕቆብ 1:17

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በደስታችሁ ቀናት ማለት በተደነገጉት በዓሎቻችሁ . . . መለከቱን ንፉ።”—ዘኍልቍ 10:10

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ይሖዋ እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል።’—መዝሙር 23:1, 2

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አራቱ ሺህ ደግሞ ለዚሁ ብዬ ባዘጋጀሁት የዜማ መሣሪያ ይሖዋን ያመስግኑ።”’—1 ዜና መዋዕል 23:4, 5

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዳዊት በቃላት እንዲሁም በሙዚቃ መሣሪያ አማካኝነት የተለያዩ ስሜቶችን ልብ በሚነካ መንገድ መግለጽ ያውቅበት ነበር

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ሃሌ ሉያ። በከበሮና በሽብሸባ አመስግኑት፤ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ያህን ያመስግን።’—መዝሙር 150:1, 4, 6

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 በጥንት ዘመን የነበሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች

የአውታር መሣሪያዎች የሚባሉት ክራር የሚመስል መሣሪያን፣ በገናን እና አሥር አውታር ያለውን መሣሪያ ይጨምሩ ነበር። (መዝሙር 92:3) እነዚህ መሣሪያዎች አላሞት እና ሺሚኒት በሚባሉ ቅኝቶች ይቃኛሉ፤ አላሞት እና ሺሚኒት ደግሞ ቀጭንና ወፍራም ድምፅ የሚያመለክቱ ሳይሆኑ አይቀሩም። (1 ዜና መዋዕል 15:20, 21) የትንፋሽ መሣሪያዎች ከሚባሉት መካከል ደግሞ ከፍተኛ ድምፅ የሚያወጡት እምቢልታ፣ ዋሽንት፣ መለከትና ጥሩምባ ይገኙበታል። (2 ዜና መዋዕል 7:6፤ 1 ሳሙኤል 10:5፤ መዝሙር 150:3, 4) ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ጊዜ መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎች “በአንድነት አንድ ድምፅ” አሰምተው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 5:12, 13) የሚሰማው ድምፅ የአንድ ሰው እስኪመስል ድረስ በሕብረት እንደሚዘምሩ ከዚህ መረዳት ይቻላል። የምት መሣሪያዎች ደግሞ ታምቡርን፣ የሚንሽዋሽዋ ጸናጽልን እና ከጥድ እንጨት የተሠራ ማንኛውንም መሣሪያ ይጨምር ነበር። በተጨማሪም ትንንሽና ትልልቅ ሲምባሎች ወይም ለሙዚቃ ማጀቢያነት የሚያገለግሉ ማጨብጨቢያ ሳህኖችም ነበሩ።—2 ሳሙኤል 6:5፤ መዝሙር 150:5 NW

[ሥዕሎች]

ከላይ፦ ቲቶ ላገኘው ድል መታሰቢያነት በሮም፣ ጣሊያን በተሠራ ሐውልት ላይ የሚገኝ በ70 ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የተወሰደን ጥሩምባ የሚያሳይ ምስል፤ የአይሁዳውያንን የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚያሳዩ በ130 ዓ.ም. አካባቢ የነበሩ ሳንቲሞች

[ምንጭ]

ሳንቲሞች፦ © 2007 by David Hendin. All rights reserved.