በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ በእርግጥ ያስብልናል—ይህን እንዴት እናውቃለን?

አምላክ በእርግጥ ያስብልናል—ይህን እንዴት እናውቃለን?

አምላክ በእርግጥ ያስብልናል​—ይህን እንዴት እናውቃለን?

ጥንትም ሆነ ዛሬ ሰዎች ‘አምላክ የሚወደን ከሆነ መከራና ሥቃይ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?’ የሚለውን አንገብጋቢ ጥያቄ ሲጠይቁ ኖረዋል። አንድን ሰው የምትወደው ከሆነ ይህ ሰው እንዲሠቃይ አትፈልግም ወይም ችግር ቢያጋጥመው ልትረዳው ትሞክራለህ ቢባል እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም። ብዙዎች ከዚህ በመነሳት ‘በዓለም ላይ መከራና ሥቃይ የበዛው አምላክ ባያስብልን ነው’ የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ። በመሆኑም በመጀመሪያ፣ አምላክ በእርግጥ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን መመርመራችን አስፈላጊ ነው።

ፍጥረት አምላክ እንደሚወደን ይመሠክራል

“ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ [የፈጠረው]” ይሖዋ አምላክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 4:24) ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ ስናሰላስል በእርግጥ ያስብልናል የሚል መደምደሚያ ላይ እንደምንደርስ ምንም ጥርጥር የለውም። እስቲ ለአንድ አፍታ ስለሚያስደስቱህ ነገሮች ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። የሚጥም ምግብ መመገብ ደስ ይልሃል? ይሖዋ በሕይወት እንድንቆይ ለማድረግ አንድ ዓይነት ምግብ ብቻ ሊሰጠን ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ በመመገብ እንድንደሰት ስለሚፈልግ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የምግብ ዓይነቶች ፈጥሮልናል። በተመሳሳይም ይሖዋ ሕይወት አስደሳችና ማራኪ እንዲሆንልን ለማድረግ ሲል ምድርን በተለያዩ ዓይነት ዛፎችና አበቦች እንድታጌጥ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዲኖራት አድርጓል።

እስቲ ደግሞ ስለ አፈጣጠራችን ለማሰብ ሞክር። የተጫዋችነት ባሕርይ፣ ሙዚቃ የማጣጣምና ውበትን የማድነቅ ችሎታ በሕይወት ለመቀጠል የግድ የሚያስፈልጉን ነገሮች አይደሉም፤ ሆኖም ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ስጦታዎች የሰጠን በሕይወታችን ደስተኞች እንድንሆን ስለሚፈልግ ነው። ከዚህም በላይ ከሌሎች ሰዎች ጋር ስላለህ ግንኙነት አስብ። ከሚወዳቸው ጓደኞቹ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ የማያስደስተው ወይም በጣም የሚወደው ሰው ከፍቅር በመነጨ ስሜት እቅፍ ሲያደርገው የማይደሰት ማን አለ? የማፍቀር ችሎታ ራሱ አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ ነው! ሰዎች የማፍቀር ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠረው አምላክ ስለሆነ ይህ ባሕርይ የእሱም ባሕርይ ነው ብለን መናገር እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንደሚወደን ያረጋግጥልናል

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ፍቅር እንደሆነ ይነግረናል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ አፍቃሪ መሆኑን ከፍጥረት ሥራዎቹ ብቻ ሳይሆን ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስም መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለጥሩ ጤንነት አስተዋጽኦ የሚያደርግ መመሪያ ይሰጠናል፣ ሁሉንም ነገር በልክ እንድናደርግ ያበረታታናል እንዲሁም ከስካርና ከመጠን በላይ ከመብላት እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ እንድንዋደድ፣ ሌሎችን በአክብሮትና በደግነት እንድንይዝ በማበረታታት ከሌሎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጠናል። (ማቴዎስ 7:12) ሥቃይ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ስግብግብነት፣ ሐሜት፣ ቅናት፣ ዝሙትና ግድያ ያሉ ድርጊቶችንና ዝንባሌዎችን ያወግዛል። እያንዳንዱ ሰው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በሚገኙት ግሩም ምክሮች ለመመራት ቢጥር ኖሮ በዓለም ዙሪያ ይህን ያህል ሥቃይ ባልኖረ ነበር!

አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ከገለጸባቸው መንገዶች ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው መላውን የሰው ዘር ለማዳን ካለው ፍላጎት የተነሳ ልጁን ኢየሱስን ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ነው። ዮሐንስ 3:16 እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” በዚህ መንገድ ይሖዋ ሞትንም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ሥቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችለውን ዝግጅት አድርጓል።—1 ዮሐንስ 3:8

ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ እንደሚወደን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። በመሆኑም አምላክ ሥቃይ ሲደርስብን ማየት አይፈልግም ብለን መደምደም እንችላለን። አምላክ ሥቃይንና መከራን ወደፊት ለማስወገድ እርምጃ ይወስዳል። ይህን እርምጃ እንዴት እንደሚወስድ መገመት አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ መከራንና ሥቃይን እንዴት እንደሚያስወግድ በግልጽ ይነግረናል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማፍቀር ችሎታ አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘው ስጦታ ነው