እንዲሳካልን ይፈልጋል
ወደ አምላክ ቅረብ
እንዲሳካልን ይፈልጋል
አሳቢ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲሳካላቸው ማለትም ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋሉ። በተመሳሳይም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ ምድራዊ ልጆቹ አስደሳች ሕይወት ሲመሩ ማየት ይፈልጋል። በመሆኑም ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለብን በመንገር በጥልቅ እንደሚያስብልን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለኢያሱ የተናገራቸውን ቃላት ከኢያሱ 1:6-9 ላይ እንመልከት።
በስተቀኝ ባለው ሥዕል ላይ እንደሚታየው መቼቱን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። የሙሴን ሞት ተከትሎ ኢያሱ በሚሊዮን የሚቆጠረውን የእስራኤል ሕዝብ እንዲመራ ገና ሹመት መቀበሉ ነው። እስራኤላውያን፣ አምላክ ለአባቶቻቸው ቃል ወደገባላቸው ምድር ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው። በዚህ ጊዜ አምላክ ለኢያሱ አንዳንድ ምክሮች ሰጠው። ኢያሱ እነዚህን ምክሮች ከተከተለ ይሳካለታል። ይሁን እንጂ እነዚህ ምክሮች ጥቅም የሚያስገኙት ለኢያሱ ብቻ አይደለም። በተግባር ካዋልናቸው የእኛም ሕይወት የተሳካ ይሆናል።—ሮም 15:4
ይሖዋ ኢያሱ እንዲጸና፣ እንዲበረታና ደፋር እንዲሆን ከአንዴም ሦስት ጊዜ ነግሮታል። (ቁጥር 6, 7, 9) ኢያሱ የእስራኤልን ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር በማስገባት ረገድ እንዲሳካለት ድፍረትና ብርታት እንደሚያስፈልገው ጥርጥር የለውም። ታዲያ ኢያሱ ደፋርና ብርቱ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ኢያሱ ደፋርና ብርቱ ለመሆን የሚረዱትን ሐሳቦች ከቅዱሳን መጻሕፍት ማግኘት ይችል ነበር። ይሖዋ “ባሪያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ” አለው። (ቁጥር 7) በወቅቱ ኢያሱ በጽሑፍ የሰፈሩ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማግኘት ይችል ነበር። * ይሁንና የአምላክን ቃል ማግኘት ስለቻለ ብቻ ስኬታማ ይሆናል ማለት አይደለም። ኢያሱ ከአምላክ ቃል ጥቅም እንዲያገኝ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ነበረበት።
መጀመሪያ ኢያሱ ልቡን በአምላክ ቃል ዘወትር መሙላት ነበረበት። ይሖዋ “ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው [“ድምፅህን ዝቅ አድርገህ አንብበው፣” NW]” ብሎታል። (ቁጥር 8) አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ጥቅስ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ፣ ኢያሱ ድምፁን ዝቅ አድርጎ ለራሱ ‘እየደገመ፣’ ‘እያሰላሰለ’ ወይም ‘እያወጣ እያወረደ’ ሕጎቹን እንዲያስታውስ መንገሩ ነበር።” ኢያሱ በየቀኑ የአምላክን ቃል ማንበቡና ማሰላሰሉ ከፊቱ የሚጠብቀውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ይረዳዋል።
ሁለተኛ ኢያሱ ከአምላክ ቃል የተማረውን በተግባር እንዲያውል ይጠበቅበት ነበር። ይሖዋ “በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ [ፈጽመው።] . . . ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም” ብሎታል። (ቁጥር 8) ኢያሱ ስኬታማ መሆኑ የተመካው የአምላክን ፈቃድ በመፈጸሙ ላይ ነው። ይህ መሆኑ ምንም አያስደንቅም፤ ምክንያቱም የአምላክ ፈቃድ ምንጊዜም ይፈጸማል ወይም ይሳካል።—ኢሳይያስ 55:10, 11
ኢያሱ የይሖዋን ምክር ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ በመሆን ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት ኖሯል።—ኢያሱ 23:14፤ 24:15
አንተስ እንደ ኢያሱ አርኪና አስደሳች ሕይወት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? ይሖዋ በዚህ ረገድ እንዲሳካልህ ይፈልጋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ያለህ መሆኑ ብቻውን በቂ አይደለም። ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገለ አንድ ታማኝ ክርስቲያን “መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡት እንዲሁም ወደ ልባችሁ ጠልቆ እንዲገባ አድርጉ” በማለት ምክር ሰጥቷል። ልብህን በአምላክ ቃል አዘውትረህ ከሞላህና የተማርከውን በሕይወትህ ተግባራዊ ካደረግክ አንተም እንደ ኢያሱ ‘ያሰብኸው ይቃናልሃል እንዲሁም ይሳካልሃል።’
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 ኢያሱ ሊያገኛቸው የሚችላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ሙሴ የጻፋቸውን አምስት መጻሕፍት (ዘፍጥረት፣ ዘፀአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኍልቍና ዘዳግም)፣ የኢዮብን መጽሐፍ እና አንድ ወይም ሁለት መዝሙራትን ይጨምራል።