በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም አቀፍ ችግር፣ ዓለም አቀፍ መፍትሔ

ዓለም አቀፍ ችግር፣ ዓለም አቀፍ መፍትሔ

ዓለም አቀፍ ችግር፣ ዓለም አቀፍ መፍትሔ

መከራና ሥቃይ የሌለበት ቦታ የለም፤ በመሆኑም በርካታ ሰዎች በርኅራኄ ተነሳስተው ሥቃይ የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሕክምና ባለሙያዎች የታመሙ ወይም የቆሰሉ ሰዎችን ለመርዳት በሆስፒታል ውስጥ ረጅም ሰዓት ይሠራሉ። የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፖሊሶች፣ ሕግ አርቃቂዎችና ሕይወት አድን ሠራተኞች የሌሎችን ሥቃይ ለማቅለል ወይም ለማስቀረት ተግተው ይሠራሉ። እንዲህ ያለው ጥረት ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርግም ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት በምድር ዙሪያ የሚገኘውን ሥቃይ ማስወገድ አይችልም። በአንጻሩ ግን አምላክ ለችግሩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መፍትሔ ማምጣት ይችላል፤ ደግሞም ያመጣል።

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል በሆነው በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚከተለው ማረጋገጫ ይገኛል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:4) ይህ ተስፋ ሲፈጸም ምን ያህል ሰዎች እንደሚጠቀሙ ለማሰብ ሞክር። ተስፋው፣ አምላክ ሁሉንም ዓይነት ሥቃይ የማስወገድ ዓላማ እንዳለው ይጠቁማል። ይህን የሚያደርገው ክፉ ሰዎችን ጨምሮ ጦርነትን፣ ረሃብን፣ በሽታን እንዲሁም የፍትሕ መዛባትን ከምድር ገጽ በማጥፋት ነው። ማንም ሰው ይህን ሊያደርግ አይችልም።

የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸው ነገሮች

አምላክ የገባቸውን ተስፋዎች የሚፈጽመው በጽንፈ ዓለም ውስጥ ሁለተኛው ኃያል አካል በሆነውና ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። ኢየሱስ ያለምንም ተቃውሞ ንጉሥ ሆኖ መላውን ምድር የሚገዛበት ጊዜ እየመጣ ነው። ከዚያ በኋላ የሰው ዘር በሰብዓዊ ነገሥታት፣ በፕሬዚዳንቶች ወይም በፖለቲካ ሰዎች መገዛቱ ያቆማል። ከዚህ ይልቅ በአንድ ንጉሥና በአንድ መስተዳድር ይኸውም በአምላክ መንግሥት ብቻ ይገዛል።

ይህ መንግሥት የሰው መንግሥታትን በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) በምድር ዙሪያ የሚገኙ የሰው ዘሮች በሙሉ በጽድቅ በሚገዛ አንድ መስተዳድር ይኸውም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት አንድ ይሆናሉ።

ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በኖረበት ወቅት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለዚህ መንግሥት ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚጸልዩ ባስተማረበት የናሙና ጸሎቱ ላይ እንደሚከተለው በማለት ስለዚህ መንግሥት ተናግሮ ነበር፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ መንግሥቱን የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ከመፈጸሙ ጋር አያይዞ እንደገለጸውና አምላክ በምድር ላይ የሚታየውን ሥቃይና መከራ ማስወገድ ፈቃዱ እንደሆነ ልብ በል።

ጽድቅ የሰፈነበት የአምላክ መንግሥት ማንኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ሊያመጣው የማይችለውን በረከት ያመጣል። ይሖዋ ልጁን ቤዛ አድርጎ የሰጠው ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሲል እንደሆነ አስታውስ። ይህ መንግሥት በሚያሰፍነው መልካም አገዛዝ ሥር ሰዎች ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። ይህስ ምን ያስከትላል? ይሖዋ “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ [ይሖዋ] ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ውርደት ከምድር ሁሉ ያስወግዳል።”—ኢሳይያስ 25:8

አንዳንዶች ‘አምላክ እስካሁን እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው? ለመሆኑ ምን እየጠበቀ ነው?’ በማለት ይጠይቁ ይሆናል። ይሖዋ ማንኛውንም ሥቃይና መከራ ለማጥፋት ወይም ለመከላከል ከረጅም ጊዜ በፊት እርምጃ መውሰድ ይችል ነበር። ይሁንና ይሖዋ ለራሱ ሳይሆን በምድር ላይ ላሉት ልጆቹ ዘላለማዊ ጥቅም ሲል ሥቃይና መከራ እስካሁን እንዲቀጥል ፈቅዷል። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ለልጃቸው ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስገኝ ከተሰማቸው ሥቃይ ሊያስከትልበት የሚችል ነገር እንዲደርስበት ሊፈቅዱ ይችላሉ። በተመሳሳይም ይሖዋ የሰው ልጆች ለጊዜው ሥቃይ እንዲደርስባቸው የፈቀደበት ጥሩ ምክንያት ያለው ሲሆን ምክንያቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጸዋል። ሥቃይ እንዲፈቅድ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል ነፃ ምርጫ፣ ኃጢአትና ከይሖዋ የመግዛት መብት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ ይገኙበታል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ የሆነ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር ለተወሰነ ጊዜ ዓለምን እንዲገዛ እንደተፈቀደለት ይገልጻል። *

በዚህ መጽሔት ላይ ምክንያቶቹን ሁሉ ለማብራራት ቦታ ቢገድበንም ተስፋና ማበረታቻ ሊሰጡን የሚችሉ ሁለት ነጥቦችን መመልከት እንችላለን። የመጀመሪያው የሚከተለው ነው፦ ይሖዋ አሁን እየደረሰብን ካለው ሥቃይና መከራ ጋር ሊወዳደር የማይችል የተትረፈረፈ በረከት ይሰጠናል። ከዚህም በላይ አምላክ “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 65:17) አምላክ፣ ክፋትን ለጊዜው በመፍቀዱ የደረሰብንን መከራና ሥቃይ ሙሉ በሙሉ ለዘለቄታው ያስወግድልናል።

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ የሚከተለው ነው፦ አምላክ መከራንና ሥቃይን የሚያስወግድበት ጊዜ የወሰነ ሲሆን ይህን ጊዜ ፈጽሞ አይለውጠውም። ነቢዩ ዕንባቆም ዓመፅና ግፍን የሚታገሰው እስከ መቼ እንደሆነ ይሖዋን ጠይቆት እንደነበር አስታውስ። ይሖዋም “ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃልና፤ . . . ከቶም አይዘገይም” የሚል መልስ ሰጥቶታል። (ዕንባቆም 2:3) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ‘የተወሰነው ጊዜ’ ቅርብ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚመጣ የሚጠቁሙ ጥቅሶች

ጦርነት አይኖርም፦

“እናንተ ሕዝቦች ኑ፤ የይሖዋን ሥራዎች፣ በምድርም ላይ እንዴት አስደናቂ ነገሮች እንዳከናወነ ተመልከቱ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ያስወግዳል።”—መዝሙር 46:8, 9 NW

የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ፦

“ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 24:15

የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል፦

“በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።”—መዝሙር 72:16

ሕመም አይኖርም፦

“‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24

ክፉ ሰዎች ይጠፋሉ፦

“ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”—ምሳሌ 2:22

ፍትሕ ይሰፍናል፦

“እነሆ፤ ንጉሥ [ክርስቶስ ኢየሱስ] በጽድቅ ይነግሣል፤ ገዦችም በፍትሕ ይገዛሉ።”—ኢሳይያስ 32:1

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ለሚደርስብን መከራና ሥቃይ ሁሉ መፍትሔ ያመጣል