በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የድሮውን ጊዜ እንድናይ ያደረገን ጉዞ

የድሮውን ጊዜ እንድናይ ያደረገን ጉዞ

ከዩናይትድ ስቴትስ የተላከ ደብዳቤ

የድሮውን ጊዜ እንድናይ ያደረገን ጉዞ

የቀድሞ አባቶቻችሁ እንዴት ይኖሩ እንደነበር ለማወቅ ወደሚያስችላችሁ አንድ ቦታ ብትጓዙ ምን ያህል እንደምትደሰቱ እስቲ ገምቱ። እኛ ያደረግነው ጉዞ እንዲህ ዓይነት ነበር ማለት ይቻላል። ጉዞውን ያደረግነው ከስዊዘርላንድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ነበር። ብዙዎች ዩናይትድ ስቴትስ በሁሉ ነገር የሠለጠነች አገር እንደሆነች ይሰማቸዋል፤ ይሁን እንጂ ጉዟችን ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመት በፊት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ወደኋላ መለስ ብለን እንድናይ አድርጎናል። እስቲ ስለ ጉዟችን እናውጋችሁ።

የስዊስ ጀርመን ቀበልኛ መናገር ስለምንችል ኢንዲያና በምትባለው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ውስጥ ለሦስት ወር እንድናሳልፍ ግብዣ ቀረበልን። ወደዚያ የምንሄድበት ዓላማ የቀድሞ አባቶቻቸው ይናገሩት የነበረውን ይህን ቀበልኛ አሁን ድረስ ለሚናገሩት የአሚሽ ማኅበረሰብ አባላት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሚሽ እምነት ተከታይ የሆኑ ቤተሰቦች በኢንዲያና ይኖራሉ።

አሚሾች በ17ኛው መቶ ዘመን በቡድን ሆነው ይኖሩ የነበሩና አናባፕቲስት የተባለው ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሰዎች የልጅ ልጆች ናቸው። አሚሾች ስማቸውን ያገኙት በስዊዘርላንድ ይኖር ከነበረው ያኮብ አማን የተባለ መሪያቸው ነው። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው እነዚህ ሰዎች በዚያን ወቅት ካደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተነስተው ‘የሕፃናት ጥምቀት እና በውትድርና አገልግሎት መካፈል ስህተት ነው’ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር። እነዚህ ሰዎች በያዙት እምነት ምክንያት መንግሥት ስደት አደረሰባቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ በሃይማኖታዊ አቋማቸው የተነሳ ተገድለዋል። ስደቱ እየተባባሰ በመምጣቱ በርካታ አሚሾች ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎችና ወደ ፈረንሳይ ለመሰደድ ተገደዋል። እስከ 19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ አሚሾች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰደዱ። እነዚህ ሰዎች በተሰደዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ባሕላቸውንና ቋንቋቸውን አልለቀቁም።

ገራገር የሆኑት እነዚህ ሰዎች ቤታቸው ሄደን በገዛ ቋንቋቸው ስናናግራቸው በጣም ተደነቁ! እስቲ ሁኔታው በዓይነ ሕሊናችሁ ይታያችሁ።

“የእኛን ቋንቋ ልትናገሩ የቻላችሁት እንዴት ነው?” በማለት በስዊስ ጀርመንኛ ጠየቁን።

እኛም “የመጣነው ከስዊዘርላንድ ስለሆነ ነው” ብለን መለስንላቸው።

ግራ በመጋባት ስሜት “ግን እኮ አሚሾች አይደላችሁም!” አሉን።

ብዙዎቹ አሚሾች የተቀበሉን በደስታ ነበር። የሚከተሉት የአኗኗር ዘይቤ የድሮው ዘመን ምን እንደሚመስል በመጠኑም ቢሆን እንድንገነዘብ አድርጎናል። ከኤሌክትሪክ መብራት ይልቅ ኩራዝ መጠቀም፣ ከመኪና ይልቅ በፈረስና በጋሪ መጓዝ፣ ከቧንቧ ውኃ ይልቅ የጉድጓድ ውኃ መጠቀም፣ ሬዲዮ ከመስማት ይልቅ ማንጎራጎር ይመርጣሉ።

ሰዎቹ የኩራት መንፈስ የማይታይባቸው ትሑት ሰዎች መሆናቸው ከምንም በላይ አስደንቆናል። ብዙዎቹ አሚሾች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ ያላቸው ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ማድረግ ያስደስታቸዋል። ይህ ደግሞ አምላክ ለሰው ዘሮችና ለምድር ስላለው ዓላማ ከእነሱ ጋር ውይይቶችን እንድናደርግ በር ከፍቶልናል።

ብዙም ሳይቆይ ከስዊዘርላንድ የመጡ እንግዶች መኖራቸውን የሚገልጽ ወሬ በአካባቢው ተሰራጨ። ብዙዎቹ ወደ ዘመዶቻቸው ቤት እንድንሄድ የጠየቁን ሲሆን እኛም በደስታ ጎብኝተናቸዋል። አንድን የአሚሾች ትምህርት ቤት እንድንጎበኝ ግብዣ ሲቀርብልን በጣም ከመደሰታችን የተነሳ ቦታውን ለማየት ጉጉት አደረብን። ምን እንደገጠመን ታውቃላችሁ?

የትምህርት ቤቱን በር ስናንኳኳ አስተማሪው ከፈተልን። ከዚያም 38 ተማሪዎች ወዳሉበት አንድ ክፍል አስገባን፤ አራት የምንሆን ሰዎች ወደ ክፍሉ ስንገባ ተማሪዎቹ እንግዶች ስለሆንባቸው ዓይናቸው ቁልጭ ቁልጭ አለ። የስምንት ክፍል ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው የነበረ ሲሆን ልጆቹ ከ7 እስከ 15 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ነበሩ። ሴቶቹ ሰማያዊ ዩኒፎርም ለብሰው ነጭ ቆብ አጥልቀዋል፤ ወንዶቹ ደግሞ ጠቆር ያለ ሱሪና ጥቁር ሰማያዊ ሸሚዝ ለብሰዋል። የክፍሉ ጣሪያ ከፍ ያለ ሲሆን ፊት ለፊት ካለው ጥቁር ሰሌዳ ከተሰቀለበት ግድግዳ በስተቀር ሁሉም ግድግዳ ውኃ ሰማያዊ ቀለም ተቀብቷል። ከፊት አካባቢ አንድ ሉልና የተጠቀለሉ የዓለም ካርታዎች ይታያሉ። ጥግ ላይ ደግሞ ክፍሉን የሚያሞቅ ትልቅ የብረት ምድጃ ይገኛል።

ከፊት ባሉት ወንበሮች ላይ ስንቀመጥ ልጆቹ በአግራሞት ይመለከቱን ነበር። አስተማሪው ተማሪዎቹን ተራ በተራ እየጠራ የቤት ሥራቸውን እንዲያሳዩ ጠየቃቸው። አስተማሪው በስዊዘርላንድ ስለሚገኙት ሰንሰለታማ ተራሮች ልጆቹን ሲጠይቃቸው ተገረምን። ማስተማሪያ መጻሕፍቱ በጣም ያረጁ ናቸው፤ አስተማሪው ስዊዘርላንድ አሁንም ድረስ መጻሕፍቱ እንደሚገልጹት ዓይነት ገጽታ ያላት መሆን አለመሆኗን ለማወቅ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም ‘ከብቶቹ በበጋ ወቅት ለግጦሽ አሁንም ጋራ ላይ ይወጣሉ? ወይስ እንደ ድሮው በተራሮቹ አናት ላይ በረዶ ይጋገራል?’ ብሎ ጠየቀን። በዚህ ጊዜ በመጽሐፉ ላይ የሚገኙትን በጥቁርና ነጭ ፎቶ ግራፍ የተነሱትን በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮች በተሻለ ሁኔታ እንዲመለከት ብለን በከለር ፎቶ የተነሱትን ተራሮች ስናሳየው ፊቱ በፈገግታ ተሞላ።

በሥራው የምትረዳው የአስተማሪው ባለቤት “ባሕላዊዉን የዜማ አወጣጣችንን ትችላላችሁ?” በማለት በተደጋጋሚ የሚነሳ አንድ ጥያቄ ጠየቅችን። እንደማንችል ነገርናት። ይሁንና አሚሾች በመዝፈንና ለየት ያለ ዜማ በማውጣት የተካኑ መሆናቸውን ስለምናውቅ አንድ ዘፈን እንዲዘፍኑልን ጠየቅናቸው። እነሱም ፈቃደኞች ሆኑ፤ 40 ሆነው አንድ ላይ ሲዘፍኑልን ተመስጠን አዳመጥናቸው። ከዚያም አስተማሪው ተማሪዎቹን ለእረፍት ለቀቃቸው።

የአስተማሪው ባለቤት ‘እስቲ አሁን ደግሞ እናንተ አንድ ዘፈን ዝፈኑልን?’ ብላ ጠየቀችን። እኛም በስዊስ ጀርመንኛ የሚዜሙ በርካታ ባሕላዊ ዘፈኖችን ስለምናውቅ በሐሳቡ ተስማማን። ድምፃችን ጎላ ብሎ ስለተሰማ ሜዳው ላይ ይጫወቱ ወደነበሩት ልጆች ጆሮ ገባ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ልጆች እየተሯሯጡ ወደ ክፍሉ መጡ። ከተማሪዎቹ ፊት ቆመን እነሱን ለማስደሰት ከልባችን ዘፈንን።

በኋላ ላይ ደግሞ 12 አባላት ያሉት አንድ የአሚሽ ቤተሰብ ምሳ ጋበዘን። የተፈጨ የድንች ገንፎ፣ የአሳማ ሥጋ፣ በቆሎ፣ ዳቦ፣ አይብ፣ የተለያዩ አትክልቶች፣ ጣፋጮችና ሌሎች ምግቦች በእንጨት በተሠራ አንድ ትልቅ ጠረጴዛ ላይ ተደርድረው ነበር። መመገብ ከመጀመራቸው በፊት ሁሉም በልባቸው ይጸልያሉ። እየበላን ሳለ የቅድመ አያቶቻቸው አገር ስለሆነችው ስለ ስዊዘርላንድ ማውራት ጀመርን፤ እነሱም ስለ ግብርና ሕይወታቸው አንዳንድ ነገር አጫወቱን። ልጆቹ ስላፈሩ ማዕዱ እስኪነሳ ድረስ እርስ በርሳቸው ይንሾካሾኩና ይሳሳቁ ነበር። ሁሉም በልቶ ሲጨርስ ለሁለተኛ ጊዜ የሚጸለይ ሲሆን ሁልጊዜም ልጆቹ ከገበታው ተነስተው መሄድ የሚችሉት በዚህ ጊዜ ነው፤ ይሁን እንጂ የሚሄዱት ለመጫወት አይደለም። ሁሉም ልጆች የተበላበትን ጠረጴዛ የማጽዳትና ሳህኖቹን የማጠብ ኃላፊነት አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ከጉድጓድ ውኃ ቀድቶ ማሞቅን ይጨምራል።

ልጆቹ ሳህኖቹን እያጠቡ ሳለ ወላጆቻቸው ወደ ሳሎን እንድንገባ ጋበዙን። በክፍሉ ሶፋ የሚባል ነገር የለም፤ ይሁንና ከእንጨት በተሠሩትና ምቹ በሆኑት የሚወዛወዙ ወንበሮች ላይ ተቀመጥን። ወዲያውኑም በጀርመንኛ የተዘጋጀ ያረጀ መጽሐፍ ቅዱስ ከሣጥን ውስጥ አውጥተው አመጡ። ከዚያም በአሚሽ ቤተሰቦች ዘንድ እንደተለመደው ሞቅ ያለ መንፈሳዊ ጭውውት ያዝን። በጭውውታችን መሃል ከተነሱት ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ‘ይሖዋ አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ኢየሱስ ገሮች ምድርን እንደሚወርሱ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? አምላክ በእርግጥ ክፉ ሰዎችን ለዘላለም በገሃነመ እሳት የመቅጣት ዓላማ አለው? ኢየሱስ ምሥራቹ በመላው ምድር እንዲሰበክ የሰጠውን ትእዛዝ የሚፈጽሙት እነማን ናቸው?’ በእነዚህና በሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ላይ ውይይት አደረግን። የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ካላቸውና መንፈሳዊ ነገሮችን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ውይይት በማድረጋችን በጣም ተደሰትን።

የድሮውን ጊዜ እንድናይ ያደረገንን ጉዞ አሁን መለስ ብለን ስናስታውሰው ልባችን በደስታ ስሜት ይሞላል፤ ፈጽሞ የማይረሱ ብዙ ትዝታዎችን አሳልፈናል። በስዊስ ጀርመንኛ ውይይት ለማድረግ ያደረግነው ጥረት፣ ብዙዎች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ለመቀበል በራቸውን እንዲከፍቱ እንዳደረጋቸው ሁሉ ልባቸውን ጭምር እንዲከፍት ምኞታችን እና ጸሎታችን ነው።