በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአልኮል ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር

ለአልኮል ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር

ለአልኮል ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ቶኒ የመጠጥ ችግር እንዳለበት አምኖ ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ አሁንም ሕይወትን ማጣጣም በቻለ ነበር! ይሁን እንጂ ቶኒ የስካር ምልክቶች ሳይታዩበት ብዙ መጠጣት ስለቻለ ብቻ የመጠጥ ችግሩን በቁጥጥሩ ሥር እንዳደረገ ተሰማው። ቶኒ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ማዳበሩ ስህተት ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

ቶኒ ከልክ በላይ የመጠጣት ልማዱ አስተሳሰቡን አዛብቶት ነበር። ቶኒ ተገንዝቦት ይሁን አይሁን አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ሁኔታውን የሚቆጣጠረው የሰውነቱ ክፍል ማለትም አእምሮው ከመጠን በላይ በሚጠጣበት ጊዜ በትክክል አይሠራም ነበር። ብዙ በጠጣ መጠን አእምሮው እሱ ያለበትን ሁኔታ በትክክል የማገናዘብ ችሎታው እየቀነሰ መጥቶ ነበር።

የቶኒ አስተሳሰብ የተሳሳተ ነበር የምንልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የመጠጥ ልማዱን የማቆም ፍላጎት ያልነበረው መሆኑ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አለን መጀመሪያ ላይ የመጠጥ ችግር እንዳለበት አምኖ መቀበል አልፈለገም ነበር። አለን እንዲህ በማለት ችግሩን በግልጽ ተናግሯል፦ “መጠጣቴ እንዳይታወቅብኝ እጠነቀቅ ነበር። ከልክ በላይ ለመጠጣቴ ሰበብ አስባብ እደረድር እንዲሁም ነገሩን አቅልዬ እመለከት ነበር። ይህን ሁሉ የማደርገው መጠጣቴን ላለማቆም ስል ነበር።” ቶኒን እና አለንን የመጠጥ ልማዳቸው እንደተቆጣጠራቸው ሌሎች ሰዎች በግልጽ ቢመለከቱም እነሱ ግን ምንም ችግር እንደሌለ በመናገር ራሳቸውን ያሞኙ ነበር። ሁለቱም ግለሰቦች ያለባቸውን የመጠጥ ችግር ለመቆጣጠር እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው። ታዲያ ሊወስዱት የሚገባ እርምጃ ምን ነበር?

እርምጃ ውሰድ!

ከአልኮል ሱስ መላቀቅ የቻሉ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ከሰጠው ከሚከተለው ማስጠንቀቂያ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስደዋል፦ “ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።”—ማቴዎስ 5:29

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ቃል በቃል የገዛ አካላችንን ቆርጠን እንድንጥል ማበረታታቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳት የሚያስከትልብንን ማንኛውንም ልማድ ከሕይወታችን ነቅለን እንድናወጣ በምሳሌያዊ መንገድ ጠበቅ አድርጎ መግለጹ ነበር። እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ ሥቃይ ሊያስከትልብን እንደሚችል እሙን ነው። ይሁንና አልኮል ያላግባብ ወደ መውሰድ እንድናመራ ሊያደርገን ከሚችል ከማንኛውም አስተሳሰብና ሁኔታ ይጠብቀናል። በመሆኑም ሌሎች ሰዎች ሁኔታው አሳስቧቸው አልኮል ከመጠን በላይ መውሰድ እንደጀመርክ ቢነግሩህ ችግሩን በቁጥጥርህ ሥር ለማድረግ የሚያስችልህን እርምጃ ውሰድ። * የመጠጥ አወሳሰድህን መቆጣጠር እንደማትችል ሆኖ ከተሰማህ ይህን ልማድ ከሕይወትህ ነቅለህ ለማውጣት ፈቃደኛ ሁን። ይህን እርምጃ መውሰድ ከፍተኛ ሥቃይ ሊያስከትል ቢችልም እንኳ ይህ ሥቃይ ሕይወትህ ቢበላሽ ከሚደርስብህ ጉዳት የከፋ አይሆንም።

የመጠጥ ሱስ አይኖርብህ ይሆናል፤ ሆኖም ብዙ የመጠጣት ችግር ይኖርብህ ይሆን? ካለብህ ለአልኮል ትክክለኛ አመለካከት ለማዳበር ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?

እርዳታ ከየት ማግኘት ትችላለህ?

1. ከልብ የመነጨ ጸሎት ዘወትር ማቅረብ ኃይል እንዳለው እምነት ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሁሉ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) እንዲህ ያለውን የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ምን ብለህ መጸለይ ትችላለህ?

የመጠጥ ችግር እንዳለብህ እንዲሁም ለችግሩ ኃላፊነቱን የምትወስደው አንተው ራስህ እንደሆንክ ምንም ሳታንገራግር አምነህ ተቀበል። ችግሩን ለማሸነፍ ምን ለማድረግ እንዳሰብክ ለአምላክ በጸሎት ንገረው፤ አምላክም ከችግሩ ለመገላገል ብሎም የከፋ ችግር ውስጥ ላለመግባት የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” ይላል። (ምሳሌ 28:13) ኢየሱስም “ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” ብለን መጸለይ እንደምንችል ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:13 የ1954 ትርጉም) ይሁን እንጂ ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ ምን እርምጃ ልትወስድ ትችላለህ? ለምታቀርበው የምልጃ ጸሎት መልስ ማግኘት የምትችለውስ ከየት ነው?

2. ከአምላክ ቃል ብርታት ለማግኘት ጣር። “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ . . . የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” (ዕብራውያን 4:12) ከዚህ ቀደም ኃይለኛ ጠጪዎች የነበሩ በርካታ ሰዎች በየዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ማንበባቸውና ባነበቡት ነገር ላይ ማሰላሰላቸው ረድቷቸዋል። ፈሪሃ አምላክ የነበረው መዝሙራዊ “በክፉዎች ምክር የማይሄድ . . . ሰው ብፁዕ ነው” በማለት ጽፏል። አክሎም “ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። . . . የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ብሏል።—መዝሙር 1:1-3

አለን መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት መጀመሩ ከአልኮል ሱሰኝነቱ ለመላቀቅ የሚያስችል ብርታት አስገኝቶለታል። እንዲህ ብሏል፦ “መጠጥ እንዳቆም የረዳኝን መጽሐፍ ቅዱስንና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ባላውቅ ኖሮ እስካሁን ድረስ በሕይወት እንደማልኖር እርግጠኛ ነኝ።”

3. ራስን የመግዛት ባሕርይ አዳብር። ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ሰካራም የነበሩ አንዳንድ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ‘በአምላካችን መንፈስ ታጥበው’ እንደነጹ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ሰካራምነትንና መረን የለቀቀ ፈንጠዝያን ለማሸነፍ የቻሉት እንዴት ነው? ራስን የመግዛት ባሕርይ በማዳበር ነው፤ ይህን ባሕርይ ማፍራት የሚቻለው ደግሞ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መረን ለለቀቀ ሕይወት ስለሚዳርጋችሁ በወይን ጠጅ አትስከሩ። ከዚህ ይልቅ በመንፈስ መሞላታችሁን ቀጥሉ” ይላል። (ኤፌሶን 5:18፤ ገላትያ 5:21-23) ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣል’ በማለት ቃል ገብቷል። አንተም ‘ደጋግመህ ለምን ይሰጥሃል።’—ሉቃስ 11:9, 13

ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የሚፈልጉ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት እንዲሁም አዘውትረው ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ችለዋል። አንተም ለተስፋ መቁረጥ እጅ ከመስጠት ይልቅ የአምላክ ቃል የሚሰጠውን የሚከተለውን ተስፋ አስታውስ፦ “ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል። ካልታከትን ወቅቱ ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”—ገላትያ 6:8, 9

4. ጥሩ ጓደኞችን ምረጥ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) የአልኮል መጠጥ አወሳሰድህን ለመቀነስ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረግህ ለጓደኞችህ ንገራቸው። ይሁን እንጂ ‘ከልክ በላይ መጠጣት፣ መረን በለቀቀ ፈንጠዝያ መካፈልና በፉክክር ብዙ መጠጣት’ ስታቆም አንዳንድ የቀድሞ ጓደኞችህ ‘እየተደነቁ ሊሰድቡህ’ እንደሚችሉ የአምላክ ቃል አስቀድሞ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 4:3, 4) የምትጠጣውን መጠን ለመቆጣጠር ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ከሚያጣጥሉ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት አቋርጥ።

5. ገደብ አብጅ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።” (ሮም 12:2) በጓደኞችህ ወይም ‘በዚህ ሥርዓት’ ከመመራት ይልቅ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ተመርተህ ገደብ ማበጀትህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሕይወት ጎዳና ያስገኝልሃል። ታዲያ ለአንተ ትክክለኛ የሆነውን ገደብ ማውጣት የምትችለው እንዴት ነው?

የወሰድከው አልኮል መጠኑ ምንም ያህል ቢሆን የማስተዋልና የማመዛዘን ችሎታህን ካዛባ ወይም ካዳከመ ለአንተ ከመጠን በላይ ነበር ማለት ነው። በመሆኑም ለመጠጣት ከመረጥክ ለራስህ የምታወጣው ገደብ መስከር ይቅርና እስከ ሞቅታ እንኳ የሚያደርስህ መሆን አይኖርበትም። በመጠጥ አወሳሰድህ ረገድ ያለህበትን ሁኔታ ከመካድ ይልቅ ራስህን በሐቀኝነት መርምር። አቅምህ ምን ይህል እንደሆነ ግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ ጊዜ ምን ያህል መጠጣት እንዳለብህ ቁርጥ ያለ ገደብ አብጅ፤ ይህ ገደብ ከልክ በላይ እንድትጠጣ የሚገፋፋህ መሆን የለበትም።

6. አልፈልግም ማለትን ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን” ይላል። (ማቴዎስ 5:37) የጋበዘህ ሰው በቅንነት ተነሳስቶ ከፍላጎትህ ውጭ እንድትጠጣ ቢገፋፋህ በትሕትና አልፈልግም ማለትን ተማር። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን።”—ቆላስይስ 4:6

7. እርዳታ ለማግኘት ጣር። የመጠጥ ችግርህን ለማሸነፍ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክሩልህ እንዲሁም መንፈሳዊ እርዳታ ሊሰጡህ የሚችሉ ጓደኞችህን እርዳታ ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል።” (መክብብ 4:9, 10፤ ያዕቆብ 5:14, 16) በተመሳሳይም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አልኮልን አላግባብ ስለመጠቀምና ስለ አልኮል ሱሰኝነት ጥናት የሚያደርግ አንድ ብሔራዊ የምርምር ተቋም እንደሚከተለው በማለት ምክር ይሰጣል፦ “አንዳንድ ጊዜ የምትጠጣውን የአልኮል መጠን መቀነስ አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ሆኖም እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ እንዲረዱህ መጠየቅ ትችላለህ።”

8. በአቋምህ ጽና። “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን በማታለል ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። ሆኖም ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያም የሚጸና ሰው ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ስለሆነ ይህን በማድረጉ ደስተኛ ይሆናል።”—ያዕቆብ 1:22, 25

ከሱስ መላቀቅ

ከመጠን በላይ የሚጠጣ ሰው ሁሉ የአልኮል ሱሰኛ ይሆናል ማለት አይደለም። ይሁንና አንዳንዶች ከመጠን በላይ ወይም ሁልጊዜ በመጠጣታቸው የአልኮል ሱሰኛ ሆነዋል። የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች አካላቸውም ሆነ አእምሯቸው ኃይለኛ ለሆነ ንጥረ ነገር ጥገኛ ስለሚሆን እንዲህ ያሉ ሰዎች ከሱሳቸው ለመላቀቅ ቁርጥ ያለ አቋም ከመውሰድና መንፈሳዊ እርዳታ ከማግኘት በተጨማሪ ሌላም ነገር ያስፈልጋቸዋል። አለን እንዲህ ብሏል፦ “አልኮል መጠጣቴን ባቆምኩበት ወቅት በጣም ታምሜ ነበር። ከመንፈሳዊ እርዳታ በተጨማሪ የሕክምና እርዳታ ማግኘት እንዳለብኝ የተገነዘብኩት በዚህ ጊዜ ነበር።”

በርካታ ጠጪዎች ከሱሳቸው ለመላቀቅ ብሎም ሱሳቸው እንደገና እንዳያገረሽባቸው የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ትግል በድል አድራጊነት ለመወጣት የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። * አንዳንዶች መጠጥ ማቆማቸው የሚያስከትልባቸውን ከባድ ሕመም ለማስታገስ ወይም የሚሰማቸውን ከፍተኛ የመጠጥ አምሮት ለመቀነስ እንዲሁም ከነጭራሹ ከአልኮል ለመራቅ ሆስፒታል ገብተው እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ተአምራትን ይፈጽም የነበረው የአምላክ ልጅ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው በሽተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” በማለት ተናግሯል።—ማርቆስ 2:17

መለኮታዊ መመሪያዎችን መታዘዝ ያለው ጥቅም

የአልኮል መጠጥን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር የሰጠው በአሁኑ ሕይወታችን እንድንደሰት ብቻ ሳይሆን ዘላለማዊ ጥቅም እንድናገኝ የሚፈልገው እውነተኛው አምላክ ነው። መጠጥ ካቆመ 24 ዓመት የሆነው አለን ሁኔታውን አስታውሶ “መለወጥ እንደምችል ማወቄና ይሖዋ ሕይወቴን እንዳስተካክል ሊረዳኝ እንደሚፈልግ መረዳቴ አስደስቶኛል፤ እንዲሁም አምላክ . . .” ካለ በኋላ እንባ ተናንቆት ለትንሽ ጊዜ ጸጥ አለ። ከዚያም “እም . . . ይሖዋ ያለሁበትን ሁኔታ እንደሚረዳልኝ፣ እንደሚያስብልኝ እንዲሁም የሚያስፈልገኝን እርዳታ እንደሚሰጠኝ ማወቄ ለእኔ ልዩ ነገር ነበር” በማለት ተናገረ።

አንተም አልኮል ያላግባብ የምትጠጣ ወይም የአልኮል ሱሰኛ ከሆንክ በራስህ ተስፋ አትቁረጥ ወይም የመላቀቅ ተስፋ የለኝም ብለህ አትደምድም። አለንና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች አንተ ባለህበት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን የሚጠጡትን መጠን ቀንሰዋል ወይም ከናካቴው መጠጣታቸውን አቁመዋል። እነዚህ ሰዎች ባደረጉት ውሳኔ በፍጹም አይጸጸቱም፤ አንተም ብትሆን አትጸጸትም።

ምርጫህ አልኮልን በልክ መጠጣትም ይሁን ከነጭራሹ አለመጠጣት አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ያቀረበልህን የሚከተለውን ልመና ልብ በል፦ “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”—ኢሳይያስ 48:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7  “የአልኮል ተገዢ ሆኛለሁ?” የሚለውን በገጽ 8 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.24 በብዙ አገሮች እርዳታ ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ የሕክምና ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎችና የማገገሚያ ፕሮግራሞች አሉ። መጠበቂያ ግንብ ማንኛውንም የሕክምና ዓይነት የሚደግፍ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ያሉትን የሕክምና አማራጮች በጥንቃቄ ካመዛዘነ በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጭ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 የአልኮል ተገዢ ሆኛለሁ?

ራስህን እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ፦

• ከወትሮው በተለየ ብዙ መጠጣት ጀምሬያለሁ?

• ከወትሮው በተለየ ቶሎ ቶሎ እጠጣለሁ?

• በአንድ ጊዜ የምጠጣው የአልኮል መጠን እየጨመረ ነው?

• ያለብኝን ውጥረት ለመቋቋም ወይም ከችግሬ ለመሸሽ ስል መጠጥ እጠጣለሁ?

• ጓደኛዬ ወይም ከቤተሰቤ አባላት መካከል አንዱ የመጠጥ አወሳሰዴ አሳስቦት አነጋግሮኛል?

• የመጠጥ ልማዴ በቤተሰቤ ውስጥ፣ በሥራ ቦታ ወይም በምጓዝበት ወቅት ችግር እያስከተለ ነው?

• የአልኮል መጠጥ ሳልቀምስ ለሳምንት መቆየት ይከብደኛል?

• ሌሎች ሙሉ በሙሉ ከአልኮል ስለ መራቅ ሲናገሩ ቅር ይለኛል?

• ሌሎች ምን ያህል እንደምጠጣ እንዳያውቁብኝ እጠነቀቃለሁ?

ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ለአንዱ ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑት ጥያቄዎች አዎ የሚል ምላሽ ከሰጠህ የመጠጥ ልማድህን ለመቆጣጠር እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብሃል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአልኮል መጠጥን በተመለከተ የጥበብ እርምጃ መውሰድ

አልኮል ከመጠጣትህ በፊት የሚከተሉትን ነገሮች አስብባቸው፦

አልኮል ብጠጣ ጥሩ ነው? ወይስ ባልጠጣ ይሻላል?

ምክር፦ ራሱን መግዛት የማይችል ሰው ሙሉ በሙሉ ከአልኮል መራቅ አለበት።

ምን ያህል መጠጣት ይኖርብኛል?

ምክር፦ የምትወስደው አልኮል የማመዛዘን ችሎታህ ከማዛባቱ በፊት ምን ያህል መጠጣት እንዳለብህ ወስን።

መጠጣት ያለብኝ መቼ ነው?

ምክር፦ ከማሽከርከርህ ወይም ንቃት የሚጠይቁ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ከማድረግህ በፊት አሊያም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን ከማከናወንህ በፊት አትጠጣ፤ በእርግዝና ወቅት ወይም አንዳንድ መድኃኒቶች ሲወሰዱ መጠጣት ተገቢ አይደለም።

የት ብጠጣ ይሻላል?

ምክር፦ ክብርን ዝቅ በሚያደርጉ ቦታዎች አትጠጣ፤ መጠጣትህ እንዳይታወቅብህ ብለህ ተደብቀህ አትጠጣ፤ አልኮል መጠጣት በሚያሰናክላቸው ሰዎች ፊት አትጠጣ።

መጠጣት ያለብኝ ከእነማን ጋር ነው?

ምክር፦ ጥሩ ባሕርይ ካላቸው ጓደኞችህ ወይም ከቤተሰብህ አባላት ጋር መጠጣት ትችላለህ፤ የመጠጥ ችግር ካለባቸው ሰዎች ጋ አትጠጣ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሰካራም የነበረ ሰው ከአምላክ ቃል እርዳታ አገኘ

በታይላንድ የሚኖረው ሱፖት ኃይለኛ ጠጪ ነበር። መጀመሪያ ላይ የሚጠጣው ማታ ማታ ነበር። ቀስ በቀስ ጠዋት መጠጣት የጀመረ ሲሆን ውሎ አድሮ ምሳ ሰዓትም መጠጣት ጀመረ። ብዙውን ጊዜ የሚጠጣው ለመስከር ሲል ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ሱፖት መስከር በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ሲያውቅ መጠጣቱን አቆመ። በኋላ ላይ ግን የመጠጥ ችግሩ አገረሸበት። በዚህም የተነሳ ቤተሰቡ በጣም አዘነ።

ያም ሆኖ ግን ሱፖት ይሖዋን ይወድ እንዲሁም እሱን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ ይፈልግ ነበር። የሱፖት ጓደኞች እሱን መርዳት የቀጠሉ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቦቹን ከእሱ ጋር የበለጠ ጊዜ እንዲያሳልፉና በእሱ ተስፋ እንዳይቆርጡ ያበረታቷቸው ነበር። በአንድ ወቅት ሱፖት በ1 ቆሮንቶስ 6:10 ላይ የሚገኘው ‘ሰካራሞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም’ የሚለው ግልጽ ሐሳብ ያለበት ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረዳው። በዚህ ጊዜ የመጠጥ ችግሩን ለማሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ገባው።

ከዚያም ሱፖት አልኮል መጠጣቱን ከናካቴው ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። በመጨረሻም ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሚያገኘው ኃይል፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ባለው መመሪያና ቤተሰቡና ጉባኤው በሚያደርግለት እርዳታ ታግዞ በመንፈሳዊ የተበረታታ ከመሆኑም ሌላ የአልኮል ሱሱን ማሸነፍ ቻለ። ሱፖት ለአምላክ ራሱን ወስኖ ሲጠመቅ ቤተሰቦቹ እጅግ ተደሰቱ። ሱፖት ይመኘው እንደነበረው ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ችሏል፤ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ጊዜውን ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት እየተጠቀመበት ነው።