በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መኖሪያዎቻቸው

መኖሪያዎቻቸው

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሕይወት

መኖሪያዎቻቸው

“በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ወደኋላ ብዬ አላውቅም።”—የሐዋርያት ሥራ 20:20

የቅጥሩን ግዙፍ በር እንዳለፋችሁ ወደ አንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ከተማ ትገባላችሁ። እንደ ብዙዎቹ ከተሞች ሁሉ ይህ ከተማም የሚገኘው በኮረብታ ላይ ነው። ወደ ላይ ቀና ብላችሁ ስትመለከቱ የከተማው ላይኛው ክፍል ወለል ብሎ ይታያችኋል። ምቾትና ውበት ያላቸው በርካታ ነጫጭ ቪላ ቤቶች የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው ደምቀው ይታያሉ፤ አብዛኞቹ ቤቶች በግንብ በታጠረው ግቢ ውስጥ የአትክልት ስፍራ አላቸው። ይህ የሀብታሞች ሠፈር ነው። ከኮረብታው ወረድ ስትሉ ደግሞ የተለያየ ቅርጽና መጠን ያላቸው በርከት ያሉ ቤቶች ታገኛላችሁ። መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ነጋዴዎችና ባለ ርስቶች የሚኖሩባቸው እነዚህ በድንጋይ የተሠሩ ትላልቅ ፎቆች በመንገዱ ዳርና ዳር ይገኛሉ። ወደታች ወረድ ብሎ በሚገኘው ሸለቋማ አካባቢ ደግሞ የድሆች ሠፈር ይገኛል። በዚህ ሠፈር ውስጥ ያሉት ያረጁ ቤቶች መጠናቸው አነስ አነስ ያለ ሲሆን የሣጥን ቅርጽ አላቸው፤ አንዳንዶቹ በጠባብ ግቢዎች ውስጥ ችምችም ብለው የተሠሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጠባብ መተላለፊያ ያሏቸውና ተጠጋግተው የተሠሩ ናቸው።

በሰው በተጨናነቁ መንገዶች ላይ ስትጓዙ የምትሰሙት ድምፅና የሚያውዳችሁ ሽታ በአካባቢው ምን እየተከናወነ እንዳለ ሹክ ይላችኋል። ሴቶች ምግብ እያበሰሉ ስለሆነ አካባቢው በሚያስጎመጅ የምግብ ሽታ ታውዷል። የእንስሳት ጩኸትና የሚጫወቱ ልጆች ጫጫታ ይሰማችኋል። ወንዶች ደግሞ ውካታ በበዛባቸውና ደስ የማይል ጠረን ባላቸው ሱቆች ውስጥ ደፋ ቀና ይላሉ።

ክርስቲያኖች ይኖሩ የነበረው በእንደነዚህ ዓይነት ቤቶች ውስጥ ነበር። እነዚህም ቤቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን፣ መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰምና ፈጣሪያቸውን ለማምለክ ይጠቀሙባቸው ነበር።

ትንንሽ ቤቶች። በዚያን ጊዜ የነበሩት ቤቶች በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ቤቶች ሁሉ መጠናቸውና ዓይነታቸው እንደ አካባቢውና እንደ ቤተሰቡ የገቢ ሁኔታ ይለያያል። ትንንሾቹ ቤቶች (1) ባለ አንድ ክፍል ሲሆኑ መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ተጨናንቆ የሚኖርባቸው ጠባብና በቂ ብርሃን የሌላቸው ናቸው። ብዙዎቹ ትንንሽ ቤቶች ግድግዳቸው የተሠራው ከጭቃ ጡብ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ባልተጠረበ ድንጋይ የተገነቡ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ሁለቱም ዓይነት ቤቶች የድንጋይ መሠረት አላቸው።

የቤቶቹ የውስጥ ግድግዳ ይመረጋል፤ እንዲሁም ወለሉ ድንጋይ ይነጠፍበታል፤ ሆኖም ምርጉ ቶሎ ቶሎ ስለሚለቅ ዘወትር መታደስ ያስፈልገዋል። እነዚህ ቤቶች በጣሪያቸው ወይም በግድግዳቸው ላይ ጭስ ማውጫ የሚሆን ቢያንስ አንድ ቀዳዳ አላቸው። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ መሠረታዊ የሆኑ ጥቂት የቤት ዕቃዎች ብቻ ይገኙ ነበር።

የቤቱን ጣሪያ ለመሥራት በመጀመሪያ በቋሚዎች ላይ ወራጅ ይመታል፤ ከዚያም በወራጆቹና በማገሮቹ ላይ ቀጫጭን ርብራቦች፣ መቃዎችና ቅርንጫፎች ከተደረጉ በኋላ አፈር ይደለደልበታል። ጥቅጥቅ ተደርጎ የተደለደለው ጣሪያ በተቻለ መጠን ውኃ እንዳያሳልፍ ይለሰናል። ብዙውን ጊዜ ጣሪያ ላይ መውጣት የሚቻለው በውጭ በኩል በሚደረግ መሰላል አማካኝነት ነበር።

ክርስቲያኖች እንዲህ ባሉ ጠባብ ክፍሎች ውስጥ ቢኖሩም ቤታቸው ደስ የሚያሰኝ ነበር፤ ድሃ ቤተሰቦች እንኳ ሳይቀሩ በመንፈሳዊ ባለጠጎችና ደስተኞች መሆን ይችሉ ነበር።

መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች። ትላልቅ የሆኑትና በድንጋይ የተገነቡት እነዚህ ባለ ሁለት ፎቅ ቤቶች (2) የእንግዳ ማረፊያ ክፍል አላቸው። (ማርቆስ 14:13-16፤ የሐዋርያት ሥራ 1:13, 14) በላይኛው ደርብ ላይ ይገኝ የነበረው ይህ ትልቅ የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ስብሰባዎች ለማካሄድ ያገለግል የነበረ ከመሆኑም ሌላ አብዛኛውን ጊዜ በዓል ለማዘጋጀት ያገለግል ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) እነዚህ ቤቶችም ሆኑ ከእነዚህ ተለቅ የሚሉት የነጋዴዎችና የባለ ርስቶች ቤቶች (3) የተጠረቡ የበሃ ድንጋዮችን በኖራ በማያያዝ ይገነቡ ነበር። ድንጋይ የተነጠፈባቸው ወለሎቻቸውና የውስጥ ግድግዳዎቻቸው ይለሰናሉ፤ የውጭ ግድግዳዎቻቸው ደግሞ ኖራ ይቀባሉ።

በፎቅ ላይ ወደሚገኙት ክፍሎችና ወደ ጣሪያ መውጣት የሚቻለው በደረጃ ነበር። ሰዎች ከጣሪያ ላይ እንዳይወድቁም ሆነ ሌሎች አደጋዎች እንዳይደርሱባቸው ለመከላከል ሲባል ጠፍጣፋ በሆኑት ጣሪያዎች ዙሪያ መከታ ይደረግ ነበር። (ዘዳግም 22:8) ከዚህም በተጨማሪ ጣሪያው ፀሐይ በምትበረታበት ሰዓት ለማጥናት፣ ለማሰላሰል፣ ለመጸለይ ወይም ለማረፍ የሚያስችል ዳስ ለመጣል ያገለግል ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 10:9

ብዙውን ጊዜ ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ የሚኖርባቸው እነዚህ በጥሩ ሁኔታ የተሠሩ ቤቶች ተጨማሪ ሳሎን፣ መኝታ ቤቶች፣ ትልቅ ኩሽናና የመመገቢያ ክፍል አላቸው።

ይበልጥ ምቾትና ውበት ያላቸው ቤቶች። የሮማውያንን የቤት አሠራር ዘዴ ተከትለው የተሠሩት እነዚህ ቤቶች (4) መጠናቸው፣ ቅርጻቸውና የተገነቡበት ሁኔታ የተለያየ ነበር። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚገኙት ሰፋፊ ክፍሎች የተሠሩት ቤተሰቡ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ማዕከል ሆኖ በሚያገለግለው ትልቅ ምግብ ቤት ዙሪያ ነው። አንዳንዶቹ ቤቶች ሁለት ወይም ሦስት ፎቆች (5) አሊያም በግንብ በታጠረ ግቢ ውስጥ የሚያምር የአትክልት ስፍራ አላቸው።

እነዚህ ምቾትና ውበት ያላቸው ቤቶች ምርጥ በሆኑ የቤት ዕቃዎች የተሞሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ዕቃዎች በዝሆን ጥርስና በወርቅ ያጌጡ ናቸው። ቤቶቹ የቧንቧ ውኃና የገላ መታጠቢያ ገንዳ አላቸው። የቤቶቹ ወለል በጣውላ ወይም የተለያየ ቀለም ባላቸው ዕብነ በረዶች የተሠራ ሊሆን ይችላል፤ ግድግዳዎቹ በአርዘሊባኖስ ጣውላ የተለበዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰዎች ቤቶቻቸውን ለማሞቅ የከሰል ማንደጃዎችን ይጠቀሙ ነበር። በመስኮቶቹ ላይ ለደኅንነት ሲባል አብዛኛውን ጊዜ የእንጨት ማገር ይደረግባቸዋል፤ አላፊ አግዳሚው ውስጡን እንዳያይ ደግሞ መጋረጃ ይጋረዳል። ወፍራም የሆነው ግድግዳ ተቦርቡሮ መስኮት ይወጣለትና የታችኛው ክፍል ተስተካክሎ ለመቀመጫነት ያገለግል ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 20:9, 10

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የቤቶቻቸው መጠን ወይም ዓይነት ምንም ይሁን ምን እንግዳ ተቀባዮችና ያላቸውን ከማካፈል ወደኋላ የማይሉ ለጋሶች ነበሩ። በመሆኑም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚጎበኙት ከተማ ትልቅም ይሁን ትንሽ አገልግሎታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ በእንግድነት ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸው አፍቃሪ የሆነ ቤተሰብ አያጡም ነበር።—ማቴዎስ 10:11፤ የሐዋርያት ሥራ 16:14, 15

‘የስምዖንና የእንድርያስ ቤት።’ ኢየሱስ ‘በስምዖንና በእንድርያስ ቤት’ የሞቀ አቀባበል ተደርጎለት ነበር። (ማርቆስ 1:29-31) የእነዚህ ዓሣ አጥማጆች ቤት የሚገኘው ቀለል ያለ አሠራር ያላቸውና (6) ችምችም ብለው የተሠሩ ቤቶች በሚገኙበት ሠፈር ውስጥ ሳይሆን አይቀርም፤ እነዚህ ቤቶች በድንጋይ የተነጠፉ ግቢዎች አሏቸው።

እንዲህ ያሉት ቤቶች በራቸውም ሆነ መስኮታቸው የሚገኘው በግቢው በኩል ነው፤ ግቢው ደግሞ ብዙውን ጊዜ ምግብ ለማብሰል፣ ለመጋገር፣ እህል ለመፍጨት እንዲሁም ከሰዎች ጋር እንደ መጫወትና አብሮ እንደ መብላት ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ያገለግላል።

በቅፍርናሆም የነበሩት ባለ አንድ ፎቅ ቤቶች ከባልጩት ድንጋይ (እሳተ ገሞራ የፈጠረው ዐለት) የተሠሩ ነበሩ። በውጪ በኩል በሚገኙት ደረጃዎች አማካኝነት በተጠቀጠቀ የሸክላ አፈር ወይም በጡብ ወደተሠራው ጠፍጣፋ ጣሪያ መውጣት ይቻላል። (ማርቆስ 2:1-5) የቤቶቹ ወለል በተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የስጋጃ ምንጣፍ ይነጠፍባቸዋል።

በገሊላ የባሕር ዳርቻ ትይዩ ሆነው በመደዳ የተሠሩት ቤቶች ትላልቅ መንገዶችንና ጠባብ መተላለፊያዎችን ፈጥረዋል። ቅፍርናሆም ገቢያቸው በባሕር ላይ ለተመሠረተው ዓሣ አጥማጆች ተስማሚ መኖሪያ ነበረች።

“ከቤት ወደ ቤት።” በአጠቃላይ ሲታይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይገኙ የነበሩ ክርስቲያኖች ቤቶቻቸው የተለያየ ዓይነት ነበሩ፤ የአንዳንዶቹ ከጭቃ ጡብ የተሠራ ባለ አንድ ክፍል ቤት ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ በድንጋይ የተገነቡ ትልልቅ ቤቶች አሊያም የበለጠ ምቾትና ውበት ያላቸው ቪላ ቤቶች ነበሩ።

እነዚህ ቤቶች ለቤተሰቡ መጠለያ ከመሆን ያለፈ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ቤቶቹ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለመቅሰም ያገለግላሉ። እያንዳንዱ ቤተሰብ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ፈጣሪውን በአንድነት ያመልክ ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናትና ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ተገናኝተው ለመጨዋወት በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚማሩትን ነገር እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ተግባራቸውን ለማከናወን ማለትም በመላው የሮማውያን ዓለም “ከቤት ወደ ቤት” እየሄዱ ለመስበክና ለማስተማር ይጠቀሙበት ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 20:20