በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊረዱ ይችላሉ?

ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊረዱ ይችላሉ?

ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊረዱ ይችላሉ?

ታምባ በምዕራብ አፍሪካ የሚኖር ወጣት ሲሆን የትምህርት ቤት ፈተና ሊፈተን በዝግጅት ላይ ነው። * እናቱ ፈተናውን ለማለፍ የሞቱ ዘመዶቻቸው እርዳታ እንደሚያስፈልገው አበክራ ነገረችው። በፓሌርሞ፣ ሲሲሊ ጎብኚዎች እንዳይፈርሱ በመድኃኒት ከደረቁ በኋላ ዋሻዎች ውስጥ የተቀመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖችን ይጎበኛሉ። አንዳንዶች እነዚህ አስከሬኖች በሕይወት ለሚኖሩ ሰዎች መለኮታዊ ጥበቃ እንደሚያደርጉ ያምናሉ። በየዓመቱ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ፣ በምዕራባዊ ኒው ዮርክ የምትገኘውንና በጣም ብዙ መናፍስት ጠሪዎች እንዳሉባት የሚነገርላትን ሊሊ ደል የተባለች ከተማ ይጎበኛሉ። ጎብኚዎቹ ወደዚያ ቦታ የሚሄዱት ከሞቱ ዘመዶቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት እንዲሁም የእነሱን እርዳታ ለማግኘት ተስፋ አድርገው ነው።

ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊረዱ ይችላሉ የሚለው እምነት በመላው ዓለም በጣም ተስፋፍቷል። አንተስ ምን ይመስልሃል? ምናልባት አንተም እንዲህ ያለውን ትምህርት ተምረህ ወይም ይህን እምነት አጥብቆ የሚከተል ሌላ ሰው በቅርብ ታውቅ ይሆናል። በሞት ያጣናቸውን ዘመዶቻችንን ለማየት መናፈቃችን ያለ ነገር ነው። መናፍስት ጠሪዎች ደግሞ ይህንን ፍላጎታችንን እንደሚያሟሉልን ተስፋ ይሰጣሉ። አንዲት መናፍስት ጠሪ መንፈሳዊው ዓለም “ከተጠየቀ እርዳታ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ ነው” በማለት እንደተናገረች ታይም መጽሔት ዘግቧል። ይህ በእርግጥ እውነት ነው? ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን መርዳት ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ግልጽ መልስ ያስደንቅህ ይሆናል።

የሞቱ ሰዎች የሆነ ቦታ እየኖሩ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ ቀላል በሆነና ለመረዳት በማያስቸግር መንገድ አስቀምጦታል። መክብብ 9:5 “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” እንደሚል ልብ በል። ሙታን ስሜት ሊኖራቸው ይችላል? ቁጥር 6 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል፤ ከፀሓይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ፣ ፈጽሞ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም።” በተጨማሪም ይኸው ምዕራፍ በቁጥር 10 ላይ “ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለም” በማለት እንደሚናገር ልብ በል። እዚህ ላይ “መቃብር” ተብሎ የተተረጎመው “ሺኦል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የሰው ልጆችን የጋራ መቃብር” ለማመልከት ያገለግላል። የዚህ ቃል የግሪክኛ አቻ የሆነው “ሔዲስ” በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ ለጥቂት ቀናት የቆየበትን ቦታ ለማመልከት ተሠርቶበታል።—የሐዋርያት ሥራ 2:31

ኢየሱስ በሕይወት ሳለ ብዙ ሰዎችን ረድቷል፤ ሆኖም መሞት እንደሚገባው ያውቅ ነበር። በመቃብር ውስጥ በሚቆይበት ጊዜ ሰዎችን መርዳቱን እንደሚቀጥል ተሰምቶት ነበር? በፍጹም። የሚሞትበትን ጊዜ ማንም ሰው ምንም ሊሠራ ከማይችልበት ሌሊት ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐንስ 9:4) ኢየሱስ ሰዎች ‘በሞት ሲረቱ’ ሕልውናቸው እንደሚያከትም በሚገባ ያውቅ ነበር።—ኢሳይያስ 26:14 NW

በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ ሞት ተመሳሳይ ሐሳብ ለማስተላለፍ ሌላ ንጽጽር ተጠቅሞ ነበር። ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐንስ 11:11-13) እንቅልፍ የወሰደው ሰው ይረዳናል ብለን እንደማንጠብቅ የታወቀ ነው። እንቅልፍ የተኛ ሰው በአካባቢው ስለሚከናወነው ነገር ምንም ስለማያውቅ ለማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም።

ነፍስ ከሞት በኋላ ሕያው ሆና ትኖራለች?

ብዙ ሰዎች ነፍስ ከሞት በኋላ ሕያው ሆና የምትኖር ረቂቅ ነገር እንደሆነች የሚገልጽ ትምህርት ተምረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ግን ከዚህ የተለየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ የሆነው ዘፍጥረት ነፍስ ምን እንደሆነ ይነግረናል። ዘፍጥረት 2:7 የመጀመሪያው ሰው በተፈጠረበት ወቅት ‘ሕያው ነፍስ እንደሆነ’ ይናገራል። ሰው ራሱ ነፍስ ነው፤ እንስሳትም ነፍስ ናቸው። (ዘፍጥረት 1:20-25) ስለዚህ አንድ ሰው ወይም እንስሳ ሲሞት ነፍስ ሞተ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጥልናል።—ሕዝቅኤል 18:4

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ከሙታን ጋር እንደተገናኙ፣ ድምፃቸውን እንደሰሙ አልፎ ተርፎም በዓይናቸው እንዳዩአቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ አይደለም?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። በብዙ የዓለም ክፍሎች እንዲህ ያሉ ወሬዎችን መስማት የተለመደ ነው። እንዲህ ያሉ ወሬዎች ብዙዎች የሞቱ ዘመዶቻቸውን ወይም የቅርብ ጓደኞቻቸውን ማግኘት እንደሚችሉ እንዲያምኑና ሰዎችን ከሙታን ጋር ማገናኘት እንደሚችሉ ወደሚናገሩ ሙታን ሳቢዎች እንዲሄዱ ይገፋፏቸዋል።

ታዲያ እንዲህ ያሉ ወሬዎች እውነትነት አላቸው? ከሆነስ ከላይ ከተመለከትናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች ጋር አይጋጩም? ክርስቶስ ኢየሱስ የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) እውነት ደግሞ እርስ በርሱ አይቃረንም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉትን ይረዳሉ ለሚለው ሐሳብ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ የሚያሳይ ግልጽ መመሪያ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞተ ሰው እርዳታ ለማግኘት ስለሞከረ አንድ ሰው ይናገራል። ይህን ታሪክ በጥንቃቄ ብንመረምር እውነቱ ግልጽ ይሆንልናል።

ንጉሡ ከሞተ ሰው እርዳታ ጠየቀ

ታሪኩ የተፈጸመው በሰሜን እስራኤል ሲሆን በዚህ ቦታ ጦርነት እየተካሄደ ነበር። ንጉሥ ሳኦልና ሠራዊቱ አስፈሪ ከነበረው የፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠዋል። ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ባየ ጊዜ ‘ልቡ እጅግ ተሸበረ።’ በዚህ ወቅት ንጉሡ ለእውነተኛው አምልኮ ጀርባውን ሰጥቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ለጸሎቱ ምላሽ ሳይሰጠው ቀረ። ታዲያ ሳኦል እርዳታ ለማግኘት ወዴት ዘወር ይል ይሆን? የአምላክ ነቢይ የነበረው ሳሙኤልም ሞቶ ነበር።—1 ሳሙኤል 28:3, 5, 6

ሳኦል መመሪያ ለመጠየቅ በዓይንዶር ወደምትገኝ ሙታን ሳቢ ሄደ። ይህችን ሴት ‘ሳሙኤልን እንድታስነሳለት’ ለመናት። ሴትየዋ አንድ መንፈስ እንዲመጣ አደረገች። “ሳሙኤል” ተብሎ የተነሳው ይህ መንፈስ ለሳኦል ፍልስጥኤማውያን እንደሚያሸንፉትና እሱም ሆነ ወንዶች ልጆቹ በጦርነቱ እንደሚገደሉ ነገረው። (1 ሳሙኤል 28:7-19) በእርግጥ ሳሙኤል ከሞት ተነስቶ ይህን ተናግሯል?

እስቲ ስለ ሁኔታው አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ‘ወደ መሬት እንደሚመለሱ’ እንዲሁም ‘ዕቅዳቸው እንዳልነበር እንደሚሆን’ ይናገራል። (መዝሙር 146:4) ሳኦልም ሆነ ሳሙኤል አምላክ ከሙታን ሳቢዎች ጋር መገናኘትን እንደሚያወግዝ ያውቃሉ። እንዲያውም ሳኦል ከዚያ ቀደም መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች ከምድሪቱ እንዲጠፉ አድርጎ ነበር።—ዘሌዋውያን 19:31

እስቲ ጉዳዩን ለማገናዘብ ሞክር። ታማኝ የሆነው ሳሙኤል መንፈስ ሆኖ የሚኖር ቢሆን ኖሮ የአምላክን ሕግ ጥሶ በሙታን ሳቢ በኩል ከሳኦል ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ ይሆን ነበር? ይሖዋ ለሳኦል መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም። ታዲያ አንዲት ሙታን ሳቢ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ በሞተው ሳሙኤል በኩል ሳኦልን እንዲያናግረው ማስገደድ ትችላለች? በፍጹም። ተነሳ የተባለው ይህ ሳሙኤል የአምላክ ታማኝ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ የሞተውን ሳሙኤል መስሎ የቀረበው አንድ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም አጋንንት ነው።

አጋንንት በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ በአምላክ ሥልጣን ላይ ያመፁ መላእክት ናቸው። (ዘፍጥረት 6:1-4፤ ይሁዳ 6) እነዚህ አጋንንት ሰዎችን በሕይወት ሳሉ ማየት ይችላሉ፤ በመሆኑም አንድ ሰው እንዴት እንደሚናገር፣ ምን እንደሚመስልና የሚያደርገውን ነገር በሙሉ ያውቃሉ። የእነዚህ አጋንንት ዋነኛ ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ሐሰት ነው የሚለውን ሐሳብ ማስፋፋት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ መናፍስታዊ ኃይላት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ማስጠንቀቁ የሚያስገርም አይደለም! (ዘዳግም 18:10-12) እነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን አሁንም አሉ።

ብዙ ሰዎች የሞቱ ዘመዶቻቸውን ድምፅ “እንደሰሙ” ወይም “እንዳዩአቸው” የሚናገሩት ለምን እንደሆነ ተገንዝበናል። እነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ኃይላት አንዳንድ ጊዜ ጥሩ መስለው ቢቀርቡም ዓላማቸው ሰዎችን ማታለል ነው። * (ኤፌሶን 6:12) እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይሖዋ ስለ እኛ የሚያስብ አፍቃሪ አምላክ ነው። የሞቱ ሰዎች ሌላ ቦታ እየኖሩ እንዲሁም ወዳጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት የሚችሉ ቢሆን ኖሮ አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን ከእነሱ ጋር እንዳንገናኝ ይከለክለን ነበር? ደግሞስ ከእነሱ ጋር ለመገናኘት የሚደረገው ጥረት “አስጸያፊ” እንደሆነ ይናገር ነበር? በፍጹም! (1 ጴጥሮስ 5:7) ታዲያ አስተማማኝ እርዳታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

ለሙታንም ሆነ በሕይወት ላሉት ሰዎች የሚሆን እውነተኛ እርዳታ

ከላይ ከተገለጹት ሐሳቦች እንደተረዳነው የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉትን መርዳት አይችሉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሞቱ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የከፋ ውጤት ያስከትላል፤ ይህ ድርጊት በጣም አደገኛ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ሕግ እንድንጥስ እንዲሁም በአጋንንት ተጽዕኖ ሥር እንድንወድቅ ያደርገናል።

መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ እርዳታ ማግኘት የምንችለው ፈጣሪያችን ከሆነው ከይሖዋ እንደሆነ ይናገራል። ይሖዋ ከሞት እንኳ ነፃ ሊያደርገን ይችላል። (መዝሙር 33:19, 20) በአሁኑ ጊዜም ሊረዳን ዝግጁ ነው። እሱ የሚሰጠን ተስፋ እንደ ሙታን ሳቢዎች ሐሰተኛ ሳይሆን እውነተኛ ነው።

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ታምባ ሙታን ሳቢዎች የሚሰጡት የሐሰት ተስፋ ይሖዋ ከሚሰጠን እውነተኛ ተስፋ ፍጹም የተለየ እንደሆነ በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። ሙታን ሳቢዎች ለሞቱ ዘመዶቹ መሥዋዕት የማያቀርብ ከሆነ ፈተና እንደማያልፍ ተናግረው ነበር። በዚህ ጊዜ ታምባ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምሮ ነበር። ሙታን ያሉበትን ትክክለኛ ሁኔታ እንዲሁም የሞቱ ዘመዶቹን መስለው የሚቀርቡት እነማን እንደሆኑ ተምሯል። እናቱ ሙታን ሳቢዎች የሚሉትን እንዲያደርግ ብትጎተጉተውም ታምባ “ፈተናውን ብወድቅ እንኳ በሚቀጥለው ዓመት በደንብ አጥንቼ እንደገና እፈተናለሁ” በማለት እናቱ ያለችውን ሳያደርግ ቀረ።

ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ታምባ በፈተናው አንደኛ ወጣ! እናቱም በሁኔታው በጣም ተገረመች፤ በሙታን ሳቢዎች ላይ የነበራትን እምነት ያጣች ከመሆኑም በላይ ከዚያ በኋላ ለሞቱ ዘመዶቻቸው መሥዋዕት ስለማድረግ አንስታ አታውቅም። ታምባ፣ ይሖዋ ‘ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ለመጠየቅ’ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያወግዝ ተማረ። (ኢሳይያስ 8:19 1954 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ በአምላክ ሕግ ደስ እስከተሰኘ ድረስ ስኬታማ እንደሚሆን ያለውን እምነት አጠናከረለት።—መዝሙር 1:1-3

በሞት ስላጣናቸው ዘመዶቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? ምንም ተስፋ የላቸውም? ይሖዋ በሕይወት ያለነውን እኛን ከመርዳት በተጨማሪ በመቃብር ያሉትን እንደሚረዳቸው ቃል ገብቷል። ነቢዩ ኢሳይያስ የሞቱ ሰዎች ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ከገለጸ በኋላ በኢሳይያስ ምዕራፍ 26 ቁጥር 19 ላይ “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ . . . እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ” በማለት እንደተናገረ ልብ በል። ትንቢቱ በመቀጠል ‘በሞት የተረቱ’ እንደገና በሕይወት እንደሚኖሩ ይናገራል።

እስቲ የሚከተለውን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። በመቃብር ውስጥ ያሉና ምንም ማድረግ የማይችሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሙታን ሕይወት ያገኛሉ! እንዲያውም ይሖዋ ለሙታን ሕይወትን ለመስጠት ‘እንደሚናፍቅ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 14:14, 15) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ ለማመን የሚከብድ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ ስለነበር ሙታንን በይሖዋ ዓይን ሕያዋን እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል።—ሉቃስ 20:37, 38

አንተስ እንዲህ ዓይነት ተስፋ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? * የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት መቅሰምህን ቀጥል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ስትቀጥል ይሖዋ በሕይወት ያሉትንም ሆነ የሞቱትን መርዳት እንደሚችል እንዲሁም ተስፋዎቹ “እምነት የሚጣልባቸውና እውነት” እንደሆኑ እርግጠኛ ትሆናለህ።—ራእይ 21:4, 5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ስሙ ተለውጧል።

^ አን.18 በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሙታን መናፍስት—ሊረዱህ ወይም ሊጎዱህ ይችላሉን? ደግሞስ በእርግጥ አሉን? የሚል ርዕስ ያለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ተመልከት።

^ አን.26 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠውን ሐሳብ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሞት ያጣናቸውን ዘመዶቻችንን ለማየት መናፈቃችን ያለ ነገር ነው

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነቢዩ ሳሙኤል ከሞት ተነስቶ ንጉሥ ሳኦልን አነጋግሮታል?