በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ለሰዎች የዘላለም ሕይወት ስጦታ የሰጣቸው ለምንድን ነው?

አምላክ ለሰዎች የዘላለም ሕይወት ስጦታ የሰጣቸው ለምንድን ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አምላክ ለሰዎች የዘላለም ሕይወት ስጦታ የሰጣቸው ለምንድን ነው?

▪ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “የዘላለም ሕይወት” ማግኘት የምንችልበት አጋጣሚ እንደከፈተልን ይናገራል። (ዮሐንስ 6:40) ይሁንና አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ተስፋ እንዲሰጠን ያነሳሳው ምንድን ነው? የፍትሕ ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ነው?

ፍትሕ፣ ሰዎችን ትክክልና ተገቢ በሆነ መንገድ መያዝን ይጨምራል። በእርግጥ እኛ ሕይወት የሚገባን ሰዎች ነን? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ “ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ይላል። (መክብብ 7:20) ኃጢአት ደግሞ ቅጣት ያስከትላል። አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ኃጢአት በሠራበት ቀን እንደሚሞት አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተገፋፍቶ “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 6:23) ታዲያ የአዳም ዘሮች በሙሉ ሞት የሚገባቸው ከሆነ አምላክ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ የከፈተላቸው ለምንድን ነው?

የዘላለም ሕይወት “ነፃ ስጦታ” ነው። ይህ ስጦታ የአምላክ ፍቅርና ጸጋ ምን ያህል ታላቅና ሰፊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል፤ ይሁንና ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው ጻድቃን ተብለው መጠራታቸው እንዲያው የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው።”—ሮም 3:23, 24

ሁላችንም ሞት የሚገባን ቢሆንም እንኳ አምላክ ለሚወዱት ሁሉ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት መረጠ። ታዲያ እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እንግዲህ ምን ማለት እንችላለን? አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም! ምክንያቱም ሙሴን ‘ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፤ ልራራለት የምፈልገውን ደግሞ እራራለታለሁ’ ብሎታል። . . . ለመሆኑ እንዲህ ብለህ ለአምላክ የምትመልሰው አንተ ማን ነህ?”—ሮም 9:14-20

በአንዳንድ አገሮች አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ዳኛ ከባድ ቅጣት ተበይኖበት ለታሰረ ወንጀለኛ ምሕረት ሊያደርግለት ይችላል። ወንጀለኛው በዳኛው ብያኔ ተስማምቶ የሚፈለግበትን ከፈጸመ እንዲሁም የአስተሳሰብና የባሕርይ ለውጥ ካደረገ ዳኛው ወይም ፕሬዚዳንቱ ቅጣቱን በማቅለል ወይም ከነአካቴው ምሕረት በማድረግ ይቅርታ የማድረግ ምርጫ አላቸው። ይህ ወንጀለኛው ይገባኛል ብሎ የሚጠይቀው ሳይሆን እነሱ በደግነት የሚያደርጉለት ነገር ነው።

በተመሳሳይም ይሖዋ ሁሉም ኃጢአተኞች የሚገባቸው ቅጣት እንዳይፈጸምባቸው ሊመርጥ ይችላል። እንዲያውም በፍቅር ተገፋፍቶ እሱን ለሚወዱና ካወጣው መሥፈርት ጋር ተስማምተው ለሚኖሩ ሁሉ የዘላለም ሕይወት መስጠት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” በማለት ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የገለጸበት ከሁሉ የላቀው ተግባር አንድያ ልጁ ለእኛ ሲል ተሠቃይቶ እንዲሞት ማድረጉ ነው። ኢየሱስ አባቱን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16

ሰዎች የኋላ ታሪካቸው ምንም ይሁን ምን ይሖዋን የሚወዱና ፈቃዱን የሚያደርጉ ከሆነ ሁሉም በአምላክ ዘንድ እኩል ተቀባይነት አላቸው። በመሆኑም የዘላለም ሕይወት ተስፋ በዋነኝነት የአምላክ ጸጋ መገለጫ ከመሆኑም በላይ ፍቅሩ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳያል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የዘላለም ሕይወት በዋነኝነት የአምላክ ጸጋ መገለጫ ከመሆኑም በላይ ፍቅሩ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳያል