በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ስለ አልኮል መጠጥ ምን አመለካከት አለው?

አምላክ ስለ አልኮል መጠጥ ምን አመለካከት አለው?

አምላክ ስለ አልኮል መጠጥ ምን አመለካከት አለው?

ለእኛ የተሻለውን ነገር የሚመኝልን ፈጣሪያችን የአልኮል መጠጥ በልክ እንዳንጠጣ አይከለክለንም። * እንዲያውም ለሰው ልጅ ‘ልቡን ደስ የሚያሰኘውን ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛውን ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታውን እህል’ ሰጥቶታል። (መዝሙር 104:15) በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ‘ወደ ጥሩ የወይን ጠጅ’ በመቀየር ታድሞበት የነበረው ሠርግ ድምቀት እንዲኖረው አስተዋጽኦ አድርጓል።—ዮሐንስ 2:3-10

ፈጣሪያችን፣ አልኮል በሰውነታችንና በአእምሯችን አሠራር ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በሚገባ ያውቃል ብለን መናገራችን ምክንያታዊ ነው። በሰማይ የሚኖረው አባታችን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ‘የሚበጀንን ነገር ያስተምረናል’ እንዲሁም ኃይለኛ መጠጦችን ከመጠን በላይ እንዳንጠጣ አጥብቆ ያስጠነቅቀናል። (ኢሳይያስ 48:17) እነዚህን ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች ልብ በል፦

“መረን ለለቀቀ ሕይወት ስለሚዳርጋችሁ በወይን ጠጅ አትስከሩ።” (ኤፌሶን 5:18) “ሰካራሞች . . . የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የአምላክ ቃል ‘ሰካራምነትን፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያንና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን’ ያወግዛል።—ገላትያ 5:19-21

የአልኮል መጠጦችን ከመጠን በላይ መጠጣት ያለውን አደጋ እስቲ እንመልከት።

ከመጠን በላይ መጠጣት ያለው አደጋ

መጠጥ የተወሰነ ጥቅም ቢኖረውም ኃይለኛ ንጥረ ነገሮችን ስለያዘ አእምሯችንና ሰውነታችን በትክክል እንዳይሠራ ሊያደርግ ይችላል። አልኮልን ከመጠን በላይ መጠጣት የሚከተሉትን ችግሮች ሊያስከትል ይችላል፦

ከመጠን በላይ መጠጣት የማመዛዘን ችሎታን ያዛባል፤ በዚህም ምክንያት ‘አእምሮ ይቀባዥራል።’ (ምሳሌ 23:33) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውና ከመጠን በላይ ይጠጣ የነበረው አለን እንዲህ ብሏል፦ “የመጠጥ ሱስ የሰውነት ደዌ ብቻ ሳይሆን የአንድን ሰው አስተሳሰብና አመለካከት የሚጎዳ ደዌ ጭምር ነው። በሌሎች ሰዎች ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንዳታስቡ ያደርጋችኋል።”

ከመጠን በላይ መጠጣት ሰዎች ምንም ዓይነት የኃፍረት ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋል። ቅዱሳን መጻሕፍት “የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል” በማለት ያስጠነቅቃሉ። (ሆሴዕ 4:11 የ1954 ትርጉም) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? አልኮል በብዛት መጠጣታችን አእምሯችንን እንድንስት ስለሚያደርግ ከዚህ በፊት አምቀን የያዝናቸውን ሐሳቦችና ምኞቶች ተቀባይነት እንዳላቸው አድርገን እንድናስብ አልፎ ተርፎም በተግባር ለመፈጸም እንድንገፋፋ ሊያደርገን ይችላል። እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የወሰድነውን ቁርጥ አቋም ሊያለዝብብን ይችላል። መጠጥ ያለንን የሥነ ምግባር አቋም ስለሚያላላብን መንፈሳዊ ውድቀት ሊያስከትልብን ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ ጆን ከሚስቱ ጋር በመጨቃጨቁ በንዴት ከቤት ወጥቶ መጠጥ ቤት ይገባል። ንዴቱ በረድ እንዲልለት አንድ ሁለት እንደጠጣ አንዲት ሴት ወደ እሱ መጣች። ጆን ጥቂት ከደጋገመ በኋላ ከሴትየዋ ጋር ተያይዞ በመሄድ ምንዝር ፈጸመ። ጆን አልኮል ጠጥቶ የኃፍረት ስሜቱ ባይጠፋ ኖሮ ማድረግ ይቅርና ፈጽሞ የማያስበውን ነገር በማድረጉ በጣም ተጸጸተ።

አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣት ሰዎች አንደበታቸውንም ሆነ ድርጊታቸውን መቆጣጠር እንዲያቅታቸው ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዋይታ የማን ነው? . . . ጠብ የማን ነው? ብሶትስ የማን ነው? . . . የወይን ጠጅ በመጠጣት ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ነው፤ እየዞሩ ድብልቅ የወይን ጠጅ ለሚቀማምሱ ሰዎች ነው።” (ምሳሌ 23:29, 30) ከመጠን በላይ መጠጣት ‘በባሕር ላይ እንደተኛህና በመርከብ ምሰሶ ጫፍ ላይ የተጋደምህ እንዲመስልህ’ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 23:34) ከመጠን በላይ የጠጣ አንድ ሰው ከእንቅልፉ ነቅቶ “በእርግጥ ሳልደበደብ አልቀረሁም፤ ነገር ግን መደብደቤ ትዝ አይለኝም” ሊል ይችላል።—ምሳሌ 23:35 የ1980 ትርጉም

ከመጠን በላይ መጠጣት አካላዊ ጤንነትን ሊጎዳ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “[አልኮል] በመጨረሻው እንደ እባብ ይነድፋል፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል” ይላል። (ምሳሌ 23:32) የሕክምናው ሳይንስ ጥበብ የተንጸባረቀበት ይህ ጥንታዊ አባባል እውነት መሆኑን አረጋግጧል። አልኮል በብዛት መጠጣት ገዳይ የሆኑ መርዞች በሰውነት ውስጥ እንዲከማቹ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህ ደግሞ የተለያዩ የካንሰርና የጉበት በሽታዎች፣ የቆሽት መታወክ፣ በስኳር ሕመምተኞች ላይ የስኳር መጠን መቀነስ፣ የደም መርጋት፣ የልብ በሽታ እንዲሁም በፅንስ ላይ የአእምሮ ወይም የአካል ችግር ሊያስከትል ይችላል። እነዚህ አልኮል ከሚያስከትላቸው ብዙ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ እንኳ ከመጠን በላይ መጠጣቱ ራሱን እንዲስት ሊያደርገው ወይም ለሕልፈተ ሕይወት ሊዳርገው ይችላል። ይሁን እንጂ በሕክምና መጻሕፍት ላይ ያልተጠቀሰ ቢሆንም ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትለው አንድ ሌላ ከባድ መዘዝ አለ።

ከሁሉ የከፋው መዘዝ። አንድ ሰው ባይሰክርም እንኳ ከመጠን በላይ መጠጣቱ መንፈሳዊ አደጋ ሊያስከትልበት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ይናገራል፦ “የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ ማልደው ለሚነሡ፣ እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸው!” ለምን? ኢሳይያስ ከመጠን በላይ መጠጣት ስለሚያስከትለው መንፈሳዊ አደጋ ሲናገር “ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ አልሰጡም፤ ለእጆቹም ሥራ ክብር አላሳዩም” ብሏል።—ኢሳይያስ 5:11, 12

የአምላክ ቃል “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ” ሰዎች ጋር እንዳንወዳጅ ይመክረናል። (ምሳሌ 23:20) አረጋውያን ሴቶች “ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ” እንዲሆኑ ተመክረዋል። (ቲቶ 2:3) ለምን? ሰዎች ብዙውን ጊዜ በትንሹ የጀመሩት መጠጥ ምንም ሳይታወቃቸው ቀስ በቀስ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። በመጨረሻም ግለሰቡ የሚታየው መጠጥ ብቻ ስለሚሆን “ታዲያ፣ ሌላ መጠጥ እንዳገኝ፣ መቼ ነው የምነቃው?” ሊል ይችላል። (ምሳሌ 23:35) በማግስቱ ጠዋት ሰውየው አንጎበር እንዲለቀው ሲል አንድ ሁለት ለማለት ሲፈልግ እንደገና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገባል።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከልክ በላይ የሚጠጡ፣ መረን በለቀቀ ፈንጠዝያ የሚካፈሉ እንዲሁም በፉክክር ብዙ የሚጠጡ ሰዎች በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ እንደሚሰጡ’ ያስጠነቅቃል። (1 ጴጥሮስ 4:3, 5) ኢየሱስ ስለምንኖርበት ወሳኝ ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ ነበር፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ [የይሖዋ] ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል።”—ሉቃስ 21:34, 35

ታዲያ ከመጠን በላይ የመጠጣት ችግር ያለባቸው ሰዎች ‘ከልክ በላይ በመጠጣት ሸክም እንዳይበዛባቸው’ ምን ማድረግ ይችላሉ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ “አልኮል” እና “መጠጥ” የሚሉት ቃላት ቢራን፣ ድራፍትን፣ ወይን ጠጅን፣ ጠላን፣ አረቄን፣ ጠጅንና ሌሎች ኃይለኛ መጠጦችን ያመለክታሉ።

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከመጠን በላይ መጠጣት በርካታ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል