በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ በከነዓናውያን ላይ ጦርነት ያወጀው ለምንድን ነው?

አምላክ በከነዓናውያን ላይ ጦርነት ያወጀው ለምንድን ነው?

አምላክ በከነዓናውያን ላይ ጦርነት ያወጀው ለምንድን ነው?

“ኬጢያዊውን፣ አሞራዊውን፣ ከነዓናዊውን፣ ፌርዛዊውን፣ ኤዊያዊውን፣ ኢያቡሳዊውን አምላክህ እግዚአብሔር ባዘዘህ መሠረት ፈጽመህ ደምስሳቸው።”—ዘዳግም 20:17

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”—ሮም 12:18

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እርስ በርስ እንደሚጋጩ ይሰማሃል? ብዙ ሰዎች፣ አምላክ እስራኤላውያን ከነዓናውያንን እንዲያጠፏቸው የሰጠው ትእዛዝ ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ ከሚያበረታታው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይቃረናል ብለው ያስባሉ። * (ኢሳይያስ 2:4፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11) እነዚህ ሰዎች ሁለቱ መመሪያዎች ከሥነ ምግባር አኳያ እርስ በርስ እንደሚጋጩ ይሰማቸዋል።

ይህን ጉዳይ በሚመለከት ከአምላክ ጋር የመወያየት አጋጣሚ ብታገኝ ኖሮ ምን ብለህ ትጠይቀው ነበር? ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ የሚነሱ አምስት ጥያቄዎችንና መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቹ የሚሰጠውን መልስ እስቲ እንመልከት።

1. ከነዓናውያን ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ የተደረጉት ለምን ነበር? ከነዓናውያን ይኖሩ የነበሩት የራሳቸው ባልሆነ ምድር ላይ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል። እንዴት? አምላክ ከ400 ዓመታት ገደማ በፊት ታማኝ ሰው ለነበረው ለአብርሃም፣ ዘሮቹ የከነዓንን ምድር እንደሚወርሱ ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍጥረት 15:18) አምላክ የአብርሃም ዘሮች የነበሩት እስራኤላውያን አካባቢውን ወርረው እንዲይዙ ሲያደርግ ለአብርሃም የገባለትን ቃል መፈጸሙ ነበር። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች ከነዓናውያን ቀደም ብሎም እዚያ ይኖሩ ስለነበር ምድሪቱ የእነሱ ነበረች ብለው ይቃወሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን ማን የት መኖር እንዳለበት የመወሰን መብት እንዳለው የተረጋገጠ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 17:26፤ 1 ቆሮንቶስ 10:26

2. አምላክ ከነዓናውያን ከእስራኤላውያን ጋር አብረው እንዲኖሩ ያልፈቀደላቸው ለምንድን ነው? አምላክ ከነዓናውያንን በሚመለከት የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “በምድርህ ላይ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ አለዚያ እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ አማልክቶቻቸውን ማምለክ በርግጥ ወጥመድ ይሆንብሃል።” (ዘፀአት 23:33) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ነቢዩ ሙሴ ለእስራኤላውያን “አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ከክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ [ያባርራቸዋል]” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 9:5) ይሁን እንጂ እነዚያ ሕዝቦች ምን ያህል ክፉ ነበሩ?

በከነዓን ምድር የሥነ ምግባር ብልግና፣ የጣዖት አምልኮና ሕፃናትን መሥዋዕት ማድረግ በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ሄንሪ ሃሌይ፣ አርኪኦሎጂስቶች በዚያ አካባቢ ቁፋሮ ሲያደርጉ “ለበኣል [ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የከነዓናውያን አምላክ] መሥዋዕት ሆነው በቀረቡ ሕፃናት አፅም የተሞሉ በርካታ ማሰሮዎች” እንዳገኙ ተናግረዋል። አክለውም “አካባቢው እንዳለ በአራስ ሕፃናት መካነ መቃብር ተሞልቷል። . . . ከነዓናውያን የአምልኮ ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑት በአማልክቶቻቸው ፊት የፆታ ብልግና በመፈጸምና የበኩር ልጆቻቸውን አርደው ለእነዚሁ አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ነበር። የከነዓን ምድር በጠቅላላ ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሆኖ ነበር። . . . የከነዓናውያንን ከተሞች ፍርስራሽ ቆፍረው ጥናት ያደረጉ አርኪኦሎጂስቶች አምላክ ለምን ከዚያ ቀደም ብሎ እንዳላጠፋቸው በጣም ገርሟቸዋል።”

3. በዚያ ጊዜ በምድር ላይ ሌሎች ክፉ ሕዝቦች አልነበሩም? ከነዓናውያንን ብቻ ነጥሎ ያጠፋቸው ለምንድን ነው? አምላክ ኃጢአተኞችን ብቻ ነጥሎ ሲያጠፋ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ አልነበረም። በኖኅ ዘመን ምድር ‘በዓመፅ በተሞላች’ ጊዜ አምላክ የጥፋት ውኃ በማምጣት የኖኅን ቤተሰብ ብቻ አስቀርቶ ሁሉንም አጥፍቷል። (ዘፍጥረት 6:11፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) የሰዶምና ገሞራ ነዋሪዎች ኃጢአታቸው ‘እጅግ በከፋ’ ጊዜ አምላክ አጥፍቷቸዋል። (ዘፍጥረት 18:20፤ 2 ጴጥሮስ 2:6) እንዲሁም ‘የደም ከተማ’ በተባለችው የአሦር ዋና ከተማ በነነዌ ላይ የጥፋት ፍርድ በይኖ ነበር፤ ይሁን እንጂ ነዋሪዎቿ ከመጥፎ መንገዳቸው ንስሐ ስለገቡ ከተማዋን ሳያጠፋት ቀርቷል። (ናሆም 3:1፤ ዮናስ 1:1, 2፤ 3:2, 5-10) ከነዓናውያንን በተመለከተ ግን አምላክ እነሱን ያጠፋቸው ከጊዜ በኋላ የመሲሑ መገኛ የሚሆነውን የእስራኤልን ብሔር ለመጠበቅ ሲል ነበር።—መዝሙር 132:11, 12

4. አምላክ ከነዓናውያንን ማጥፋቱ እሱ ፍቅር እንደሆነ ከሚናገረው ሐሳብ ጋር አይጋጭም? ላይ ላዩን ሲታይ አምላክ ከነዓናውያንን ማጥፋቱ እሱ አፍቃሪ ከመሆኑ ጋር የሚጋጭ ሊመስል ይችላል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሁን እንጂ ሁኔታውን ጠለቅ ብለን ስንመረምር ፍቅሩ ጎልቶ ይታያል።

አምላክ፣ የከነዓን ነዋሪዎች መጥፎ ጎዳና እንደሚከተሉ አስቀድሞ ያውቅ ነበር። ሆኖም ወዲያውኑ አላጠፋቸውም፤ ከዚህ ይልቅ የኃጢአታቸው ‘ጽዋ እስኪሞላ’ ድረስ 400 ዓመት ታግሷቸዋል።—ዘፍጥረት 15:16

ከነዓናውያን ኃጢአታቸው በዝቶ ሊሻሻሉ ይችላሉ የሚለው ተስፋ ሲሟጠጥ ይሖዋ እንዲጠፉ አደረገ። ይሁንና ከነዓናውያንን ሁሉ በጅምላ አላጠፋቸውም። ለምን? ምክንያቱም ለመለወጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ነበሩ። ለመለወጥ ፈቃደኛ ለነበሩት እንደ ረዓብና ገባዖናውያን ላሉ ሰዎች ምሕረት አድርጎላቸዋል።—ኢያሱ 9:3-11, 16-27፤ ዕብራውያን 11:31

5. የፍቅር አምላክ ማንንስ ቢሆን እንዴት ጨክኖ ያጠፋል? ይህ ጥያቄ የተነሳበትን ምክንያት መረዳት አዳጋች አይሆንም፤ ምክንያቱም የሰውን ሕይወት ማጥፋት ሲያስቡት እንኳ ደስ የማይል ነገር ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አምላክ በክፉዎች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ከባድ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳው ፍቅሩ ነው። ይህን በግልጽ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሕመምተኛ ጋንግሪን የሚባል የማይድን ቁስል ከያዘው ሐኪሞች ብዙውን ጊዜ በሽታው ያለበትን እጅ ወይም እግር ከመቁረጥ በቀር ምንም አማራጭ አይኖራቸውም። የሰውን እጅ ወይም እግር መቁረጥ የሚያስደስት ነገር ባይሆንም እንኳ አንድ ጥሩ ሐኪም ይህን ሳያደርግ ቢቀር የሕመምተኛው ቁስል አመርቅዞ በሰውነቱ ሁሉ እንደሚሰራጭና የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል ያውቃል። አሳቢ የሆነው ሐኪም ለታካሚው ጥቅም ሲል ደስ የማይለውን ይህን ሥራ መፈጸም ግድ ይሆንበታል።

በተመሳሳይም ይሖዋ ከነዓናውያንን ማጥፋት የሚያስደስተው ነገር አልነበረም። እሱ ራሱ “በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም” በማለት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 33:11) በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ የእስራኤል ብሔር መሲሑ የሚገኝበት ዘር እንዲሆን ዓላማው ነበር፤ ይህ መሲሕ እምነታቸውን በተግባር ለሚያሳዩ ሁሉ የመዳን መንገድ ይሆንላቸዋል። (ዮሐንስ 3:16) በዚህም ምክንያት አምላክ፣ እስራኤላውያን በከነዓናውያን አስጸያፊ ልማዶች ሲበከሉ ዝም ብሎ ማየት አልቻለም። ስለሆነም ከነዓናውያን ከምድሪቱ እንዲጠፉ ወይም እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ አምላክ የላቀ ፍቅሩን አሳይቷል፤ ይህም ሲባል ለታማኝ አምላኪዎቹ ጥቅም ሲል ደስ የማይለውን ተግባር እንዲፈጽም ፍቅሩ ገፋፍቶታል ማለት ነው።

ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ጥቅም

ስለ ከነዓናውያን ጥፋት የሚገልጸው ታሪክ ለእኛ የሚያስገኘው ጥቅም አለ? አዎን፣ ሮም 15:4 እንዲህ ይላል፦ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” ታዲያ በከነዓን የተፈጸመው ነገር ለእኛ ትምህርት የሚሆነን እንዲሁም ተስፋ የሚሰጠን እንዴት ነው?

ከዚህ ታሪክ ብዙ የምናገኘው ትምህርት አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ረዓብና ገባዖናውያን በአምላክ ላይ እምነት ሲያሳድሩ እሱም በምሕረቱ ተገፋፍቶ ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል። ይህ ሁኔታ ማንኛውም ሰው፣ የኋላ ታሪኩ ወይም ቀድሞ የፈጸመው ኃጢአት ምንም ይሁን ምን አምላክን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ካለው ይህን ማድረግ እንደሚችል ያስገነዝበናል።—የሐዋርያት ሥራ 17:30

በተጨማሪም ስለ ከነዓናውያን ጥፋት የሚገልጸው ዘገባ አምላክ በቅርቡ ለሚወስደው እርምጃ እንደ ናሙና በመሆን ተስፋ ይፈነጥቅልናል። ይህ ታሪክ አምላክ፣ ክፋት አይሎ ጥሩነትን ሙሉ በሙሉ እንዲውጠው የማይፈቅድ መሆኑን ያረጋግጥልናል። እንዲያውም አምላክ በቅርቡ ክፉዎችን ሁሉ ለማጥፋት እርምጃ እንደሚወስድ፣ እሱን የሚወዱትን ሰዎች ግን ከጥፋት እንዲተርፉ በማድረግ ጽድቅ ወደሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚያስገባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። (2 ጴጥሮስ 2:9፤ ራእይ 21:3, 4) በዚያን ጊዜ የሚከተሉት አጽናኝ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ፦ “[ይሖዋን] ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ።”—መዝሙር 37:34

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ “ከነዓናውያን” የሚለው መጠሪያ አምላክ፣ እስራኤላውያን ከአካባቢያቸው እንዲያፈናቅሏቸው ያዘዛቸውን ብሔራት በሙሉ ያመለክታል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የሚያካሂዱትን ጦርነት ይደግፋል?

አምላክ፣ እስራኤላውያን ከነዓናውያንን እንዲያጠፉ ማዘዙ በዛሬው ጊዜ ሰዎች ጦርነት እንዲያካሂዱ ምክንያት ይሆናቸዋል? አይሆናቸውም፤ ለዚህ ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦

አምላክ በዛሬው ጊዜ ለየት አድርጎ የሚመለከተው አንድም አገር ወይም ብሔር የለም። እስራኤላውያን የኢየሱስን መሲሕነት ሳይቀበሉ በቀሩ ጊዜ ፍርድ አስፈጻሚ ሆነው ማገልገላቸውን ጨምሮ በማንኛውም ሁኔታ የአምላክ ወኪል መሆናቸው አከተመ። (ማቴዎስ 21:42, 43) በመሆኑም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንደማንኛውም ብሔር ይመለከታቸው ጀመር። (ዘሌዋውያን 18:24-28) ከዚያን ጊዜ አንስቶ የትኛውም አገር በሚያካሂደው ጦርነት የአምላክ ድጋፍ አለኝ ሊል አይችልም።

ይሖዋ አምላኪዎቹ በአንድ የተወሰነ የምድር ክፍል ወይም ክልል እንዲኖሩ አላዘዘም። ከዚህ ይልቅ አገልጋዮቹ በምድር ላይ ‘በሁሉም ብሔራትና ነገዶች’ ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ።—ራእይ 7:9፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ኢየሱስ ተከታዮቹ በጦርነት እንደማይካፈሉ በግልጽ አመልክቷል። በኢየሩሳሌም ላይ ስላንዣበበው አደጋ ተከታዮቹን ባስጠነቀቃቸው ጊዜ በከተማይቱ ውስጥ ቆይተው ከመዋጋት ይልቅ ሸሽተው እንዲያመልጡ አዟቸዋል፤ እነሱም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። (ማቴዎስ 24:15, 16) እውነተኛ ክርስቲያኖች የጦር መሣሪያ በማንሳት ፈንታ በቅርቡ ከምድር ላይ ክፋትን ጠራርጎ በሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ላይ ሙሉ በሙሉ ይተማመናሉ።—ዳንኤል 2:44፤ ዮሐንስ 18:36

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ያለው ሰው በእርግጥ ሊያስደስተው እንደሚችል የረዓብ ምሳሌ ያሳያል