በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሮም በሄደበት ወቅት የተጓዘው በየትኛው መንገድ ነበር?

የሐዋርያት ሥራ 28:13-16 ጳውሎስ ወደ ጣሊያን የተጓዘባት መርከብ በኔፕልስ የባሕር ዳርቻ በፑቲዮሉስ (በአሁኗ ፖትዞሊ) እንደደረሰች ይናገራል። ከዚያም ቪያ አፒያ በሚባለው በከተማዋ አውራ ጎዳና ወደ ሮም ተጓዘ።

ቪያ አፒያ የተባለው አውራ ጎዳና ስያሜውን ያገኘው በ312 ዓ.ዓ. መንገዱን ማሠራት ከጀመረው አፒየስ ክላውዲየስ ሲከስ ከተባለው ሮማዊ ባለሥልጣን ነው። ከ5 እስከ 6 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋት ያለው ይህ መንገድ በትላልቅ የባልጩት ድንጋዮች (እሳተ ገሞራ የፈጠረው ዐለት) የተሠራ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ከሮም በስተ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 583 ኪሎ ሜትር ተጨምሮበታል። ይህ አውራ ጎዳና ሮምን የምሥራቁ ዓለም መግቢያ ከነበረችው ብሩንዲዚየም (የአሁኗ ብሪንዲዚ) የተባለች የወደብ ከተማ ጋር ያገናኛል። መንገደኞች አንዳንድ ነገሮችን ለመግዛት፣ ለአዳር ወይም ፈረሶችን አሊያም ሌላ የመጓጓዣ ዓይነት ለመቀየር በየ24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ የማረፊያ ቦታዎች ቆይታ ያደርጉ ነበር።

ይሁን እንጂ ጳውሎስ ይጓዝ የነበረው በእግሩ ሳይሆን አይቀርም። እሱ የተጓዘበት የቪያ አፒያ ጎዳና ክፍል 212 ኪሎ ሜትር ርዝመት ነበረው። የዚህ መንገድ የተወሰነ ክፍል ፓንቲን ማርሺዝ የተባለውን ረግረጋማ ቦታ አቋርጦ የሚያልፍ ሲሆን አንድ ሮማዊ ጸሐፊ ይህን ቦታ በሚመለከት የወባ ትንኝና መጥፎ ሽታ የበዛበት እንደሆነ አማርሮ ተናግሯል። ከዚህ ረግረጋማ አካባቢ በስተ ሰሜን ትንሽ አለፍ ብሎ አፍዩስ የገበያ ስፍራ (ከሮም 65 ኪሎ ሜትር ገደማ ያህል ይርቃል) እንዲሁም ሦስት ማደሪያ (ከሮም 50 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል) የሚባለው የማረፊያ ቦታ ይገኛል። የሮም ክርስቲያኖች ወደ እነዚህ ሁለት ማረፊያዎች በመሄድ ጳውሎስን ተቀብለውታል። “ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ።”—የሐዋርያት ሥራ 28:15

በ⁠ሉቃስ 1:63 ላይ የተገለጸው የመጻፊያ ጽላት ምን ዓይነት ነበር?

የሉቃስ ወንጌል እንደዘገበው ዘካርያስን የተወለደው ወንድ ልጁ ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ ወዳጆቹ ጠይቀውት ነበር። በዚህ ጊዜ ዘካርያስ “የእንጨት ጽላት እንዲያመጡለት ጠየቀና ‘ስሙ ዮሐንስ ነው’ ብሎ ጻፈ።” (ሉቃስ 1:63) አንድ የጽሑፍ ሥራ እዚህ ላይ “ጽላት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ብዙውን ጊዜ ከእንጨት ተሠርቶ ሰም በመቀባት የሚዘጋጅ አነስተኛ የመጻፊያ ጽላት” እንደሚያመለክት ገልጿል። እርስ በርስ በተያያዙ የእንጨት ጣውላዎች ላይ ያለው ሰርጎድ ያለው ስፍራ ሰም ይቀባል። ከዚያም አንድ ጸሐፊ ሹል በሆነ መጻፊያ አማካኝነት በዚህ ጣውላ ላይ ማስታወሻ መጻፍ ይችል ነበር። ከዚያም በላዩ ላይ የተጻፈውን ማስታወሻ አጥፍቶ ጽላቱን እንደገና በማለሰስለስ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይቻላል።

ማንበብና መጻፍ በኢየሱስ ዘመን የሚለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በፖምፔ የሚዘጋጁ ሥዕሎች፣ በሮም የተለያዩ ግዛቶች የሚሠሩ ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም ከግብፅ እስከ ሃድርያን ግንብ [ሰሜን ብሪታንያ] ድረስ በሚገኙ በርካታ ቦታዎች ላይ ተቆፍረው የወጡ ሕያው ምሳሌዎች፣ ጽላቶች በስፋት ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ያመለክታሉ።” እንዲህ ያሉ ጽላቶች ከተለያዩ ግለሰቦች ለምሳሌ ከነጋዴዎች፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ምናልባትም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እጅ አይጠፉም ነበር።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቪያ አፒያ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንድ ተማሪ ሰም የተቀባ ጽላት፣ ሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

[ምንጭ]

By permission of the British Library