በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈተናዎች ቢደርሱበትም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል

ፈተናዎች ቢደርሱበትም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ፈተናዎች ቢደርሱበትም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል

ጴጥሮስ ኢየሱስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ሁኔታ ስላሳሰበው ፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት በአንክሮ እየተከታተለ ነው። እነዚህ ሰዎች ቅፍርናሆም በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ ነበሩ። ጴጥሮስ የሚኖረው በዚህ ከተማ ሲሆን ዓሣ የማጥመድ ሥራውንም የሚያካሂደው ቅፍርናሆም በሚገኘው የገሊላ ባሕር ዳርቻ ላይ ነበር። አብዛኞቹ ወዳጆቹ፣ ዘመዶቹና በሥራ የሚያውቃቸው ሰዎችም የሚኖሩት በዚሁ ከተማ ነበር። ጴጥሮስ፣ በምድር ላይ ከኖሩት አስተማሪዎች ሁሉ ከሚበልጠው ከኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት መማር ያስገኘለትን ደስታ የአገሩ ሰዎችም እንዲያገኙ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ዳሩ ምን ያደርጋል በዚህ ቀን ሁኔታው ጴጥሮስ እንደጓጓለት ሳይሆን ቀረ።

ብዙዎቹ ኢየሱስን ማዳመጥ አቆሙ። አንዳንዶቹ ኢየሱስ የተናገረውን በመቃወም ጮክ ብለው ማጉረምረም ጀመሩ። ይሁንና ጴጥሮስን ከሁሉ በላይ ያስጨነቀው ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዳንዶቹ ለኢየሱስ መልእክት ያሳዩት ምላሽ ነበር። መንፈሳዊ ትምህርት ሲያገኙ፣ አዲስ ነገር ሲያውቁና እውነትን ሲረዱ በፊታቸው ላይ ይታይ የነበረው ደስታ በዚህ ወቅት እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል። እንዲያውም የተበሳጩ አልፎ ተርፎም በንዴት የበገኑ ይመስላሉ። አንዳንዶቹ የኢየሱስ ንግግር የሚሰቀጥጥ እንደሆነ ተናገሩ። ከዚያ ወዲህ ኢየሱስን ማዳመጥ ስላልፈለጉ ምኩራቡን ለቀው ሄዱ፤ ኢየሱስንም መከተል አቆሙ።

ይህ ወቅት ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት አስቸጋሪ ነበር። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ በዚያ ቀን የተናገረው ነገር ሙሉ በሙሉ አልገባውም ነበር። ኢየሱስ የተናገረው ነገር በደፈናው ከተወሰደ ሌሎችን ቅር ሊያሰኝ እንደሚችል ሳይረዳ አልቀረም። ታዲያ ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን? ለጌታው ያለው ታማኝነት ፈተና ላይ ሲወድቅ ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አልነበረም። እንደነዚህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም እንዲችልና ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል እምነቱ የረዳው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሌሎች ኢየሱስን ቢክዱትም ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል

ጴጥሮስ፣ የኢየሱስ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ግር ያሰኘው ነበር። ምክንያቱም ጌታው ሰዎች ከሚጠብቁት ተቃራኒ የሆነ ነገር እንደሚናገርና እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ጊዜ አስተውሏል። ከአንድ ቀን በፊት እንኳ ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቦ ነበር። በዚህም የተነሳ ሰዎቹ ኢየሱስን ሊያነግሡት ሞከሩ። ይሁንና ኢየሱስ ከእነሱ ሸሽቶ የሄደ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም በጀልባ ወደ ቅፍርናሆም ለመሄድ ተገደዱ፤ ይህም ብዙዎችን አስገርሟቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ በዚያ ሌሊት በጀልባ እየተጓዙ ሳሉ ሌላ እንግዳ ነገር ተመለከቱ፤ ኢየሱስ በማዕበል በሚናወጠው የገሊላ ባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እምነቱን የሚያጠናክር ጠቃሚ ትምህርት አግኝቷል። *

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በማግስቱ ጠዋት ሰዎቹ በጀልባ ተሳፍረው ተከትለዋቸው እንደመጡ ተረዱ። ይሁንና ከሁኔታው መገንዘብ እንደሚቻለው ሰዎቹ የመጡት በመንፈሳዊ ተርበው ሳይሆን ኢየሱስ እንደገና በተአምር እንዲመግባቸው ፈልገው ስለነበር ነው። በመሆኑም ሕዝቡ ሥጋዊ አስተሳሰብ ስለነበራቸው ኢየሱስ ገሠጻቸው። ኢየሱስ ከሕዝቡ ጋር ጀምሮት የነበረው ይህ ውይይት ቅፍርናሆም በሚገኘው ምኩራብም ቀጥሎ ነበር፤ በዚህ ጊዜም ወሳኝ ሆኖም ለመቀበል የሚከብድ አንድን እውነት ሲያስተምር ሕዝቡ ያልጠበቀውን ነገር ተናገረ።

ኢየሱስ፣ እነዚያ ሰዎች እሱን የሥጋዊ ምግብ ምንጭ አድርገው ሳይሆን ሰው በመሆን በሕይወቱና በሞቱ ያከናወናቸው ነገሮች ሌሎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችል ከአምላክ እንደተገኘ መንፈሳዊ ምግብ አድርገው እንዲያዩት ይፈልግ ነበር። ስለዚህ ራሱን በሙሴ ዘመን ከሰማይ ከወረደው ዳቦ ይኸውም ከመና ጋር በማመሳሰል ምሳሌ ሰጣቸው። አንዳንዶቹ በተቃወሙት ጊዜ ሕይወት ማግኘት ከፈለጉ ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት አስፈላጊ መሆኑን በማብራራት በጣም ግልጽ የሆነ ምሳሌ ነገራቸው። ተቃውሞው የከረረው በዚህ ጊዜ ነበር። አንዳንዶቹ “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብዙዎቹ እሱን መከተላቸውን ለማቆም ወሰኑ። *ዮሐንስ 6:48-60, 66

ታዲያ ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን? እሱም ቢሆን በኢየሱስ አነጋገር ግራ ተጋብቶ መሆን አለበት። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል መሞት እንዳለበት ገና አልተረዳም ነበር። ሆኖም በዚያን ቀን ኢየሱስን ጥለውት እንደሄዱት ወላዋይ ደቀ መዛሙርት እሱም ኢየሱስን መከተሉን እንዲያቆም ተፈትኖ ይሆን? በጭራሽ! ጴጥሮስ እነዚያ ሰዎች የሌላቸው አንድ ወሳኝ ነገር ነበረው። ይህ ነገር ምንድን ነው?

ኢየሱስ ወደ ሐዋርያቱ ዞር ብሎ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። (ዮሐንስ 6:67) ኢየሱስ የተናገረው ለ12ቱ ሐዋርያት ቢሆንም መልስ የሰጠው ጴጥሮስ ነበር፤ ይህ ሐዋርያ ብዙውን ጊዜ ቀድሞ የመመለስ ልማድ ነበረው። ጴጥሮስ እንዲህ የሚያደርገው ከሌሎቹ በዕድሜ ስለሚበልጥ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከሐዋርያቱ መካከል በግልጽ በመናገር የሚታወቀው ጴጥሮስ እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ በእርግጥም ያሰበውን ነገር ከመናገር ወደኋላ የማይል ሰው ይመስላል። ጴጥሮስ በዚህ ወቅት “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት በአእምሮው ውስጥ ይመላለስ የነበረውን ግሩምና መቼም የማይረሳ ሐሳብ ተናገረ።—ዮሐንስ 6:68

እነዚህ ቃላት ልብ የሚነኩ አይደሉም? ጴጥሮስ በኢየሱስ ላይ የነበረው እምነት ድንቅ የሆነ ባሕርይ ይኸውም ታማኝነትን እንዲያዳብር ረድቶታል። ጴጥሮስ ከኢየሱስ ሌላ አዳኝ እንደሌለ በግልጽ ተገንዝቦ ነበር፤ እንዲሁም ኢየሱስ የሚያድነው በንግግሮቹ ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት በሚያስተምራቸው ነገሮች አማካኝነት መሆኑን ተረድቶ ነበር። ጴጥሮስ ግራ የሚያጋቡት አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወት በረከት ማግኘት ከፈለገ ሌላ መሄጃ እንደሌለ አውቆ ነበር።

አንተስ የሚሰማህ እንዲህ ነው? የሚያሳዝነው ነገር በዛሬው ዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እንደሚወዱት ቢናገሩም ፈተና ሲያጋጥማቸው ለእሱ ያላቸውን ታማኝነት ያጎድፋሉ። ለክርስቶስ እውነተኛ ታማኝነት ማሳየት ከፈለግን ጴጥሮስ ኢየሱስ ላስተማራቸው ነገሮች የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ ያስተማራቸው ነገሮች ያልጠበቅነው ወይም ከግል ምርጫችን ጋር የሚጋጩ ቢሆኑም እንኳ ስለ እነዚህ ነገሮች ማወቅ፣ ትርጉማቸውን መረዳትና ከእነሱ ጋር ተስማምተን መኖር ያስፈልገናል። ኢየሱስ የሚመኝልንን የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ተስፋ ማድረግ የምንችለው ታማኞች ከሆንን ብቻ ነው።

እርማት ሲሰጠውም ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል

በቅፍርናሆም ያሳለፉት ውጥረት የበዛበት ያ ቀን ካለፈ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ሐዋርያቱንና አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ረጅም ጉዞ አደረገ። በተስፋይቱ ምድር ሰሜናዊ ጫፍ ላይ የሚገኘው በበረዶ የተሸፈነው የሄርሞን ተራራ አናት፣ አንዳንድ ጊዜ ከርቀት ሌላው ቀርቶ ሰማያዊ ቀለም ካለው የገሊላ ባሕር ላይ እንኳ ይታያል። ቂሳርያ ፊልጵስዩስ አቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች የሚወስደውን አቀበታማ መንገድ እየወጡ ሲሄዱ የተራራው ከፍታ ይበልጥ ጎልቶ እየታየ ይሄዳል። * አንድ ሰው ከዚህ አካባቢ ሆኖ ፊቱን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲያዞር አብዛኛውን የተስፋይቱ ምድር ገጽታ ማየት ይችላል። ውብ መልክዓ ምድር ባለው በዚህ አካባቢ ሳሉ ኢየሱስ ተከታዮቹን አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ጠየቃቸው።

ኢየሱስ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስ መልስ ለማግኘት የሚጓጉትን የኢየሱስን ዓይኖች ሲመለከት እስቲ በዓይነ ሕሊናችን ይታየን፤ ጴጥሮስ የጌታውን ዓይን ሲመለከት ደግነቱ እንዲሁም ማንም ሰው በቀላሉ ሊረዳው የሚችለውን ከፍተኛ የማስተዋል ችሎታውን እንደገና እንደተገነዘበ መገመት አያዳግትም። ኢየሱስ አድማጮቹ ከተመለከቱትና ከሰሙት ነገር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ እንደደረሱ ማወቅ ፈልጎ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም በኢየሱስ ማንነት ዙሪያ በሰፊው የሚነገሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች በመጥቀስ ለጥያቄው መልስ ሰጡ። ይሁንና ኢየሱስ በዚህ ብቻ አልረካም። የቅርብ ተከታዮቹም እንደ ሌሎቹ ስለ እሱ የተሳሳተ አመለካከት ይኖራቸው ይሆን? በመሆኑም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው።—ሉቃስ 9:18-22

በዚህ ጊዜም ፈጠን ብሎ መልስ የሰጠው ጴጥሮስ ነበር። በአብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ የነበረውን ሐሳብ ግልጽና ድፍረት በተሞላበት መንገድ ተናግሯል። “አንተ መሲሑ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ትክክለኛ መልስ በመስጠቱ ኢየሱስ በፈገግታ እያየው ሞቅ አድርጎ ሲያመሰግነው በዓይነ ሕሊናችን ሊታየን ይችላል። ኢየሱስ፣ እውነተኛ እምነት ላላቸው ሰዎች ይህንን ታላቅ እውነት የገለጠላቸው ይሖዋ አምላክ እንጂ ሰው እንዳልሆነ ለጴጥሮስ አስገነዘበው። ጴጥሮስ፣ ይሖዋ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከገለጣቸው እውነቶች ሁሉ የሚበልጠውን ይኸውም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን መሲሕ ወይም ክርስቶስ ማንነት ማስተዋል እንዲችል ተደርጓል።—ማቴዎስ 16:16, 17

ጥንት በተነገረ አንድ ትንቢት ላይ ክርስቶስ ግንበኞች የሚንቁት ድንጋይ ተብሎ ተገልጿል። (መዝሙር 118:22፤ ሉቃስ 20:17) ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ትንቢቶችን በአእምሮው በመያዝ ጴጥሮስ ባወቀው ድንጋይ ወይም ዐለት ላይ ይሖዋ አንድ ጉባኤ እንደሚመሠርት ገለጸ። * ከዚያም ጴጥሮስ በዚያ ጉባኤ ውስጥ የሚያከናውናቸው በጣም ወሳኝ የሆኑ አንዳንድ ኃላፊነቶች ተሰጠው። ኢየሱስ ለጴጥሮስ ኃላፊነቶችን እንጂ አንዳንዶች እንደሚያስቡት በሐዋርያት ላይ የበላይ እንዲሆን ሥልጣን አልሰጠውም። ኢየሱስ “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” ለጴጥሮስ ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 16:19) በመሆኑም ሦስት የተለያዩ የሰው ዘር ቡድኖች ይኸውም መጀመሪያ አይሁዶች ቀጥሎ ሳምራውያን በመጨረሻም አሕዛብ ወይም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት የመግባት ተስፋ እንዲያገኙ በሩን የመክፈት መብት ተሰጥቶታል ማለት ነው።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ብዙ ከተሰጠው ብዙ እንደሚጠበቅ የተናገረ ሲሆን ይህ አባባል እውነት መሆኑን በጴጥሮስ ላይ ታይቷል። (ሉቃስ 12:48) ኢየሱስ፣ በቅርቡ በኢየሩሳሌም ሥቃይና ሞት የግድ እንደሚደርስበት እንዲሁም ስለ መሲሑ ሌሎች ወሳኝ እውነቶችን መግለጡን ቀጠለ። ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ ተረበሸ። ኢየሱስን ለብቻው ገለል አድርጎ ከወሰደው በኋላ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” በማለት ገሠጸው።—ማቴዎስ 16:21, 22

ጴጥሮስ ይህን የተናገረው ለእሱ አስቦ ስለነበር የኢየሱስ ምላሽ እንደሚያስደነግጠው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ጀርባውን ለጴጥሮስ በመስጠት ወደ ተቀሩት ደቀ መዛሙርት እያየ (እነሱም ተመሳሳይ ነገር እያሰቡ ሳይሆን አይቀርም) “ከአጠገቤ ራቅ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለ። (ማቴዎስ 16:23፤ ማርቆስ 8:32, 33) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለሁላችንም የሚሆን ጠቃሚ ምክር ይዟል። ብዙውን ጊዜ ነገሮችን በምናከናውንበት ጊዜ በአምላክ አስተሳሰብ ከመመራት ይልቅ በሰብዓዊ አስተሳሰብ መመራት ይቀናናል። ይህን የምናደርገው በአሳቢነት ተነሳስተን ሌሎችን ለመርዳት ቢሆንም ሳይታወቀን ከአምላክ ይልቅ የሰይጣንን ዓላማ ልናራምድ እንችላለን። ይሁንና ጴጥሮስ ምን ምላሽ ሰጠ?

ኢየሱስ “ሰይጣን” ሲለው ቃል በቃል ሰይጣን ዲያብሎስ ብሎ እየጠራው እንዳልሆነ ጴጥሮስ አውቆ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ደግሞም ኢየሱስ ለጴጥሮስ የተናገረው ለሰይጣን በተናገረበት መንገድ አይደለም። ኢየሱስ ለሰይጣን “ከፊቴ ራቅ” ያለው ሲሆን ለጴጥሮስ ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ወደ ኋላዬ ሂድ” የሚል ፍቺ ያለውን ሐረግ ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 4:10) ኢየሱስ ይህን ያደረገው መልካም ጎኖች ያሉትን ይህን ሐዋርያ ዓይን ላፈር ሊለው ፈልጎ ሳይሆን የተሳሳተ አስተሳሰቡን ለማረም ስለፈለገ ብቻ ነው። ደግሞም ጴጥሮስ እንደ እንቅፋት ከጌታው ፊት መጋረጡን ትቶ ከኋላው በመሆን ድጋፍ ሰጪ ተከታዩ መሆን ያስፈልገው እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም።

ታዲያ ጴጥሮስ ተከራክሮ ወይም ተናዶ አሊያም አኩርፎ ይሆን? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ የተሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሏል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስን የሚከተሉ ሁሉ እርማት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ አለ። ከኢየሱስ ክርስቶስና ከአባቱ ከይሖዋ አምላክ ጋር ይበልጥ እየተቀራረብን መሄድ የምንችለው ተግሣጽ ሲሰጠን በትሕትና የምንቀበልና ከተግሣጹም ትምህርት ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ብቻ ነው።—ምሳሌ 4:13

ታማኝ መሆኑ ወሮታ አስገኝቶለታል

ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ እንደሚከተለው በማለት አድማጮቹን ግር የሚያሰኝ ሌላ ነገር ተናገረ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።” (ማቴዎስ 16:28) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ የጴጥሮስን የማወቅ ጉጉት እንደቀሰቀሰው ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል? ምናልባት ጴጥሮስ ጠንከር ያለ እርማት የተሰጠው መሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ልዩ መብት ማግኘት መቻሉን በተመለከተ ጥያቄ ፈጥሮበት ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ያዕቆብን፣ ዮሐንስንና ጴጥሮስን ይዞ “ወደ አንድ ረጅም ተራራ” (ከነበሩበት ስፍራ ብዙም ወደማይርቀው የሄርሞን ተራራ ሳይሆን አይቀርም) ወጣ። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እንቅልፍ እየታገላቸው ስለነበር ይህ የሆነው ማታ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ኢየሱስ ሲጸልይ ተጫጭኗቸው የነበረውን እንቅልፍ የሚያባርር አንድ ነገር ተከሰተ።—ማቴዎስ 17:1፤ ሉቃስ 9:28, 29, 32

ኢየሱስ እያዩት መለወጥ ጀመረ። የፊቱ መልክ እንደ ፀሐይ እስኪያንጸባርቅ ድረስ አበራ። ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ። ከዚያም አንደኛው ሙሴን ሌላኛው ደግሞ ኤልያስን የሚወክሉ ሁለት ሰዎች ከኢየሱስ አጠገብ ታዩ። እነዚህ ሰዎች “በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ስለሚሄድበት ሁኔታ” ከኢየሱስ ጋር ተነጋገሩ፤ ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የተነጋገሩት ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን እንዲህ ያለ መከራ እንዳይደርስበት ጴጥሮስ መከላከሉ ስህተት መሆኑ በእርግጥም ግልጽ ነበር።—ሉቃስ 9:30, 31

ጴጥሮስ በሆነ መንገድ በዚህ አስደናቂ ራእይ ውስጥ ለመሳተፍ በጣም ፈልጎ ነበር። ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ተለይተው ሊሄዱ ስለመሰለው ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ “መምህር፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል።” እርግጥ ነው፣ እነዚህ በራእዩ ላይ የታዩት ከሞቱ ረጅም ጊዜ የሆናቸው ሁለቱ የይሖዋ አገልጋዮች ድንኳን እንደማያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። ጴጥሮስ በእርግጥ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ይሁንና ጴጥሮስ ንቁ ብሎም የደግነት ባሕርይ ያለው ሰው መሆኑ እንድትወደው አያደርግህም?—ሉቃስ 9:33

ጴጥሮስን ጨምሮ ያዕቆብና ዮሐንስ በዚያ ሌሊት ሌላ መብት በማግኘት ወሮታ ተቀብለዋል። በተራራው ላይ እንዳሉ ደመና መጥቶ ሸፈናቸው። ከደመናውም እንዲህ የሚል የይሖዋ አምላክ ድምፅ ተሰማ፦ “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።” ከዚያም ራእዩ ሲያበቃ በተራራው ላይ እነሱና ኢየሱስ ብቻቸውን ቀሩ።—ሉቃስ 9:34-36

ይህ ራእይ ለጴጥሮስም ሆነ ለእኛ ድንቅ ስጦታ ነው! ጴጥሮስ በዚያ ሌሊት ‘ግርማውን በገዛ ዐይኑ የማየት’ መብት ማግኘቱን አስመልክቶ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ የጻፈ ሲሆን በእርግጥም ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሲሆን የሚኖረውን ክብር አስቀድሞ አይቷል። ይህ ራእይ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትንቢቶች እውነት መሆናቸውን ያረጋገጠ ከመሆኑም ሌላ የጴጥሮስን እምነት በማጠናከር ወደፊት ለሚደርስበት ፈተና አዘጋጅቶታል። (2 ጴጥሮስ 1:16-19) እኛም እንደ ጴጥሮስ ይሖዋ በእኛ ላይ ለሾመው ጌታ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት ከእሱ የምንማር፣ የሚሰጠንን ተግሣጽና እርማት የምንቀበል እንዲሁም እሱን በየዕለቱ በትሕትና የምንከተል ከሆነ ራእዩ የእኛንም እምነት ያጠናክረዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 በጥቅምት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በእምነታቸው ምሰሏቸው—ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 ሕዝቡ፣ በዚህ ዕለት የሰጡት ምላሽ ከአንድ ቀን በፊት ኢየሱስ የአምላክ ነቢይ እንደሆነ በአድናቆት ስሜት ተውጠው ከተናገሩት ጋር ስናወዳድር ምን ያህል ወላዋይ እንደሆኑ በግልጽ ታይቷል።—ዮሐንስ 6:14

^ አን.15 ኢየሱስና ተከታዮቹ 48 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚፈጀውን ይህን ጉዞ ያደረጉት ከገሊላ ባሕር ዳርቻዎች ይኸውም ከባሕር ወለል በታች 210 ሜትር ገደማ ከሆነ ዝቅተኛ ስፍራ ተነስተው ድንቅ የተፈጥሮ ውበት የተላበሰውን አካባቢ እያቋረጡ 350 ሜትር የሚጠጋ ከፍታ ወዳለው ቦታ ነው።

^ አን.18 በገጽ 28 ላይ የሚገኘውን  “ዐለት የተባለው ማነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ዐለት የተባለው ማነው?

“ደግሞም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚች ዐለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የሔዲስ በሮችም አያሸንፏትም።” (ማቴዎስ 16:18) ብዙዎች፣ ኢየሱስ ሐዋርያው ለሆነው ለጴጥሮስ የተናገረውን ይህን ሐሳብ ጴጥሮስ የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት ይሆናል ተብሎ እንደተነገረ አድርገው ይረዱታል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ጴጥሮስን ከሌሎች ሐዋርያት አስበልጦታል በሌላ አባባል የመጀመሪያው ጳጳስ አድርጎ ሾሞታል ብላ ታስተምራለች። በመሆኑም በሮም በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስ በማቴዎስ 16:18 ላይ የተናገራቸው ቃላት ከሰው ቁመት የሚበልጥ ርዝመት ባላቸው ትልልቅ ፊደላት በላቲን ቋንቋ ተጽፈዋል።

ኢየሱስ ይህን ሐሳብ ሲናገር ጴጥሮስን የሚገነባው ጉባኤ ዐለት እንደሚያደርገው መናገሩ ነበር? በፍጹም። በዚህ ረገድ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርጉንን ሦስት ምክንያቶች እንመልከት። በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ይህን የተናገረው ሌሎች ሐዋርያት ባሉበት ሲሆን እነሱም የተረዱት ጴጥሮስ ዐለት እንደሚሆን አልነበረም። ኢየሱስ በእነሱ ፊት ጴጥሮስን የበላይ አድርጎ ሾሞት ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜ ከእነሱ መካከል ማን እንደሚበልጥ ባልተከራከሩ ነበር። (ማርቆስ 9:33-35፤ ሉቃስ 22:24-26) ሁለተኛ፣ ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የጉባኤው ዐለት ጴጥሮስ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አመልክቷል። (1 ቆሮንቶስ 3:11፤ 10:4) ሦስተኛ፣ ጴጥሮስ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ራሱን ዐለት አድርጎ እንደማይቆጥር አሳይቷል። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት በአምላክ የተመረጠ “የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ” እንደሆነ ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 2:4-8

ያም ሆኖ አንዳንዶች የጴጥሮስ ስም ትርጉሙ “ዐለት” የሚል በመሆኑ እሱ ዐለት መሆኑን ያሳያል በማለት ይከራከራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የጴጥሮስ ስም ትርጉም በዚህ ጥቅስ ላይ ከገባው “ዐለት” ከሚለው ቃል ትርጉም ጋር ተመሳሳይ አይደለም። የጴጥሮስ ስም ትርጉም “ትንሽ ድንጋይ” የሚል ሲሆን የተገለጸውም በተባዕታይ ጾታ ነው፤ ኢየሱስ በተናገረው ሐሳብ ላይ ግን “ዐለት” የሚለው ቃል የተገለጸው በአንስታይ ጾታ ነው። ታዲያ ኢየሱስ የተናገረውን ይህን ሐሳብ ልንረዳው የሚገባን እንዴት ነው? ኢየሱስ ለጴጥሮስ “ጴጥሮስ ወይም ድንጋይ ብዬ የጠራሁህ አንተ፣ የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት ሆኖ የሚያገለግለውን ‘ዐለት’ ማለትም የክርስቶስን ማንነት ለይተህ አውቀሃል” ብሎ የተናገረ ያህል ነበር። ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነቱን ታላቅ እውነት ማሳወቅ መቻሉ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

[በገጽ 24,25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ እርማት መቀበል ባስፈለገው ጊዜም እንኳ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ ታማኝ መሆኑ አስደናቂ ራእይ የማየት መብት አስገኝቶለታል