ሰማይን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
ሰማይን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ለብዙዎች የሚያጓጓ ነው። ሙስሊሞች፣ ሂንዱዎች፣ ቡዲስቶች እንዲሁም የሕዝበ ክርስትና አባላት ሌላው ቀርቶ ስለ ሃይማኖት ግድ የሌላቸው በርካታ ሰዎች እንኳ ‘ከሞት በኋላ ሕይወት አለ’ በሚለው ትምህርት ያምናሉ፤ እርግጥ የሚያምኑበት መንገድ የተለያየ ነው። ሰማይ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከሥቃይ የሚገላገሉበት እንዲሁም “በሞት ከተለዩአቸው ዘመዶቻቸው” ጋር በድጋሚ የሚገናኙበት ውብና አስደሳች ስፍራ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። የሚገርመው ግን ብዙ ሰዎች መሞት አይፈልጉም፤ ይህ ደግሞ ‘ሁሉም ሰው ወደ ሰማይ መሄድ ይፈልጋል፤ እዚያ ለመሄድ ሲል ግን መሞት የሚፈልግ ማንም የለም’ የሚለውን አንድ የቆየ አባባል እውነተኝነት ያረጋግጥልናል። ታዲያ ሰዎች ወደ ሰማይ መሄድ እየፈለጉ ሞትን የማይመኙት ለምንድን ነው?
የተፈጠርነው ሞተን ወደ ሰማይ ለመሄድ ቢሆን ኖሮ አንድ ልጅ ለማደግ ወይም አንድ ወጣት ለማግባት እንደሚጓጓው ሁሉ ብዙ ሰዎች ሞቶ ወደ ሰማይ መሄድን የሚናፍቁት ነገር አይሆንም ነበር? ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች መሞት አይፈልጉም።
ያም ሆኖ የሃይማኖት ሰባኪዎች፣ ሰዎች ጊዜያዊ መኖሪያ በሆነችው በምድር ላይ ለጥቂት ጊዜ ከኖሩ በኋላ ዋነኛ መኖሪያቸው ወደሆነው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ብለው ያስተምራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የዋሽንግተን ዲሲ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ቲዎዶር ኤድጋር ካርዲናል መካሪክ “የተፈጠርነው እንዲህ ያለ ሕይወት ለመኖር አይደለም። የተፈጠርነው በሰማይ ለመኖር ነው” ብለው ነበር። በተመሳሳይም የዩናይትድ ስቴትስ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩ ሰው “የሕይወት ዓላማ አምላክን አስከብሮ ወደ ሰማይ መሄድ ነው፤ ምክንያቱም ሰማይ ቤታችን ነው” ብለዋል።
ሰው ከሞተ በኋላ በሰማይ ይኖራል ብለው የሚያምኑ ሰዎች ይህ እምነታቸው በአብዛኛው የተመሠረተው ቁንጽል በሆነ መረጃ ላይ ነው። በተለያዩ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ላይ ጥናት የሚያደርግ የአንድ ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆርጅ ባርና፣ በርካታ ሰዎች “ስለ ሕይወትም ሆነ ከሞት በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት ያላቸውን አመለካከት ሊያዳብሩ የቻሉት ከተለያዩ ምንጮች ማለትም ከፊልሞች፣ ከሙዚቃ ወይም ከልብ ወለድ መጻሕፍት ነው” በማለት ተናግረዋል። በፍሎሪዳ የሚገኙ አንድ የኤጲስቆጶሳውያን ፓስተር “ሰማይ አምላክ የሚኖርበት ቦታ ከመሆኑ በስተቀር ስለ ሰማይ የምናውቀው ምንም ነገር የለም” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሰማይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ነው። ታዲያ የአምላክ ቃል እንደሚናገረው ከሆነ ሰማይ ምን ይመስላል? ሰው የተፈጠረው በሰማይ እንዲኖር ነበር? ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱ ከሆነ በዚያ ምን ይሠራሉ?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ ]
ሰዎች ወደ ሰማይ መሄድ ቢፈልጉም ብዙዎቹ እዚያ ለመሄድ ሲሉ ግን መሞት የማይፈልጉት ለምንድን ነው?