መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሁሉንም ነገር በትክክል ይነግረናል?
ኢየሱስ በጎልጎታ እንደሞተ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው በተቃራኒ ከሞት ተርፎ ቢሆንስ? መግደላዊት ማርያምን አግብቶ ከእሷ ልጆች ወልዶ ሊሆን ቢችልስ? አሊያም ከማንኛውም ምድራዊ ደስታ በመራቅ የብሕትውና ሕይወት ኖሮ ቢሆንስ? ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው የተለዩ መሠረተ ትምህርቶችን አስተምሮስ ቢሆን?
እንዲህ ያሉ ግምታዊ ሐሳቦች እየተስፋፉ የመጡት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሲሆን ለዚህም በከፊል አስተዋጽኦ ያደረጉት ታዋቂ የሆኑ ፊልሞችና ልብ ወለድ መጻሕፍት ናቸው። ከእነዚህ የፈጠራ ታሪኮች በተጨማሪ አፖክሪፋ ወይም አዋልድ በሚባሉት በቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የማይካተቱ መጻሕፍት ላይ ያተኮሩ በርካታ ጽሑፎች ወጥተዋል፤ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተጻፉት የአዋልድ መጻሕፍት በወንጌሎች ውስጥ የማይገኙ ስለ ኢየሱስ የሚገልጹ ታሪኮችን እንደያዙ ይታመናል። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሁሉንም ነገር በትክክል እንደሚነግረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መሠረታዊ የሆኑ ሦስት ነገሮችን መመርመሩ ጠቃሚ ነው። በመጀመሪያ፣ የወንጌል ዘገባዎችን የጻፉትን ሰዎች በተመለከተ እንዲሁም ዘገባዎቹን የጻፏቸው መቼ እንደሆነ መረጃ ማግኘታችን ጠቃሚ ነው፤ ሁለተኛ፣ የቅዱሳን መጻሕፍትን ቀኖና ያዘጋጀው ማን እንደሆነና እንዴት እንደተዘጋጀ ማወቅ ያስፈልገናል፤ *
ሦስተኛ፣ የአዋልድ መጻሕፍት ታሪክ ምን እንደሆነና በቀኖና ውስጥ ከተካተቱት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት እንደሚለዩ መገንዘብ ያስፈልገናል።የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት መቼና በማን ነው?
አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው ክርስቶስ ከሞተ ከስምንት ዓመት በኋላ ማለትም በ41 ዓ.ም. ገደማ ነበር። በርካታ ምሑራን የማቴዎስ ወንጌል ከዚህ ጊዜ በኋላ እንደተጻፈ ይናገራሉ፤ ያም ሆነ ይህ ሁሉም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ውስጥ እንደተጻፉ ብዙዎች ይስማማሉ።
እነዚህ መጻሕፍት በተጻፉበት ወቅት የኢየሱስን ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የተመለከቱ ሰዎች በሕይወት ነበሩ፤ በመሆኑም የወንጌል ዘገባዎቹ ትክክል መሆናቸውን ማረጋገጥ ይችሉ ነበር። እንዲሁም በወንጌሎቹ ላይ ትክክል ያልሆነ ሐሳብ ቢሰፍር ኖሮ ይህን ማጋለጥ ይችሉ ነበር። ፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ብሩስ እንዲህ ብለዋል፦ “የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ስብከት ትክክለኛ ለመሆኑ ማስረጃ ከሚሆኑት ጠንካራ ነጥቦች አንዱ የሚሰብኩትን ነገር አድማጮቻቸው እንደሚያውቁት በልበ ሙሉነት መናገር መቻላቸው ነበር፤ ሐዋርያት ‘ለዚህ ነገር እኛ ምሥክሮች ነን’ ከማለት አልፈው ‘እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት’ በማለት ይናገሩ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:22)”
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት እነማን ናቸው? ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት መካከል አንዳንዶች ይገኙበታል። እነዚህም ሆኑ እንደ ያዕቆብ፣ ይሁዳና ምናልባትም ማርቆስ ያሉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም በዚያ ተገኝተው ነበር። ጳውሎስን ጨምሮ ሁሉም ጸሐፊዎች፣ ሐዋርያትንና በኢየሩሳሌም የነበሩ ሽማግሌዎችን ካቀፈው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የበላይ አካል ጋር ተባብረው ይሠሩ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 15:2, 6, 12-14, 22፤ ገላትያ 2:7-10
ኢየሱስ፣ እሱ የጀመረውን የስብከትና የማስተማር ሥራ ተከታዮቹ ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ ተልእኮ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) እንዲያውም “እናንተን የሚሰማ እኔንም ይሰማል” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 10:16) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን ኃይል እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሐዋርያትን ወይም የእነሱን የቅርብ የሥራ ባልደረቦች እንደሚመራቸው በግልጽ ይታይ ስለነበር የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እነዚህ ሰዎች የጻፏቸውን መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ አድርገው ተቀብለዋቸዋል።
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች፣ እንደ እነሱ የአምላክን ቃል የጻፉ ሌሎች ሰዎች ይህን ያደረጉት በአምላክ መንፈስ መሪነት መሆኑን እንዲሁም ጽሑፋቸው ትክክል መሆኑን መሥክረዋል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ የጻፋቸውን ደብዳቤዎች ከጠቀሰ በኋላ እነዚህ ደብዳቤዎች ‘ከሌሎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት’ ጋር በእኩል ዓይን እንደሚታዩ ጠቁሟል። (2 ጴጥሮስ 3:15, 16) ጳውሎስም በበኩሉ ሐዋርያትና ሌሎቹ ክርስቲያን ነቢያት በአምላክ መንፈስ እንደተመሩ ገልጿል።—ኤፌሶን 3:5
ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው የወንጌል ዘገባዎች እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉና ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ አለ። አፈ ታሪክና ተረት አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ወንጌሎች፣ የዓይን ምሥክሮችን መሠረት በማድረግ በጥንቃቄ የተጻፉ የታሪክ ዘገባዎች ሲሆኑ ጸሐፊዎቹም ዘገባውን ያሰፈሩት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተመርተው ነው።
ቀኖናውን ያዘጋጀው ማን ነው?
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ የሚካተቱት መጻሕፍት የተመረጡት ከተጻፉ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ሲሆን ይህን ያደረገችውም በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ አመራር ሥር የነበረችውና ኃይል የነበራት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች አንዳንድ ጸሐፊዎች ይናገራሉ። ይሁንና ሐቁ ከዚህ የተለየ ነው።
ለምሳሌ ያህል፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ኦስካር ስካርሳውን እንዲህ ብለዋል፦ “የትኞቹ መጻሕፍት በአዲስ ኪዳን ውስጥ መካተት እንዳለባቸውና የትኞቹ መካተት እንደሌለባቸው የተወሰነው በየትኛውም የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ወይም በማንኛውም ግለሰብ አይደለም፤ . . . መሥፈርቱ ግልጽና ምክንያታዊ ነበር፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በሐዋርያት ወይም በሥራ ባልደረቦቻቸው እንደተጻፉ የሚታመኑት መጻሕፍት ትክክለኛ እንደሆኑ ይቆጠሩ ነበር። ከዚያ በኋላ የተጻፉ ሌሎች መጻሕፍት፣ ደብዳቤዎች ወይም ‘ወንጌሎች’ . . . በአዲስ ኪዳን ውስጥ አልተካተቱም። ይህ ሂደት የተጠናቀቀው ከቆስጠንጢኖስ ዘመን እንዲሁም እሱ ሥልጣን የሰጣት ቤተ ክርስቲያን ከመቋቋሟ ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር ማለት ይቻላል።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚካተቱት መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ የወሰነችው የሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን [በእምነታቸው የተሰደዱት ክርስቲያኖች] ናት እንጂ ኃይል የነበራት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም።”በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ኬን በርዲንግ የተባሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር የቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና እንዴት እንደተዘጋጀ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ቤተ ክርስቲያን እሷ እንደምትፈልገው በቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ የሚካተቱትን መጻሕፍት አልመረጠችም፤ ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖች ምንጊዜም የአምላክ ቃል እንደሆኑ አድርገው ተቀብለዋቸው ለነበሩት መጻሕፍት እውቅና እንደሰጠች አድርጎ መናገሩ ይበልጥ ተገቢ ይሆናል።”
ይሁን እንጂ ቀኖናውን ያዘጋጁት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ትልቅ ቦታ የማይሰጣቸው ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው? ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ ያደረገ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ኃያል የሆነ ነገር እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ለክርስቲያኖች ከተሰጧቸው ተአምራዊ ስጦታዎች አንዱ “በመንፈስ መሪነት የተነገረን ቃል የመረዳት” ችሎታ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 12:4, 10) በመሆኑም ከእነዚያ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ በትክክል በአምላክ መንፈስ መሪነት የተነገረን ቃል በአምላክ መንፈስ ካልተነገረው ለመለየት የሚያስችል ተአምራዊ ችሎታ ነበራቸው። ከዚህ አንጻር በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት ቅዱሳን መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
ከዚህ ለመመልከት እንደሚቻለው የቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና የተዘጋጀው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሲሆን ይህም የሆነው ክርስትና በተቋቋመበት ጊዜ አካባቢ ነው። ከሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በኋላ ባሉት ዓመታት አንዳንድ ጸሐፊዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ የሚካተቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በተመለከተ ሐሳብ ሰጥተው ነበር። ይሁንና በቀኖናው ውስጥ የሚካተቱትን መጻሕፍት የወሰኑት እነዚህ ጸሐፊዎች አይደሉም፤ እነሱ ያደረጉት ነገር ቢኖር አምላክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ስለመሆናቸው በመንፈሱ በሚመሩት ወኪሎቹ አማካኝነት ያረጋገጣቸውን መጻሕፍት ትክክለኛነት መመሥከር ብቻ ነው።
በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎችም በዛሬው ጊዜ ተቀባይነት ያገኘው የቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና ትክክለኛ ስለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ ይሰጣሉ። መጀመሪያ በተጻፉበት ቋንቋ የሚገኙ ከ5,000 የሚበልጡ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ቅጂዎች በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጁ ናቸው። በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት ትክክለኛ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩትና እየተገለበጡ በስፋት የተሰራጩት እነዚህ መጻሕፍት እንጂ የአዋልድ መጻሕፍት አይደሉም።
ይሁንና በቀኖና ውስጥ መካተት ስላለባቸው መጻሕፍት ከሁሉ የላቀውን ማስረጃ ማግኘት የምንችለው ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ የሚካተቱት መጻሕፍት በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ከምናገኘው ‘የጤናማ ቃላት ንድፍ’ ጋር ይስማማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) እነዚህ መጻሕፍት አንባቢዎቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ፣ እንዲያመልኩና እንዲያገለግሉ የሚያበረታቱ ሲሆን ከአጉል እምነት እንዲሁም አጋንንትንና ፍጥረታትን ከማምለክ እንዲርቁ ያሳስባሉ። ከታሪክ አንጻር ትክክለኛ ከመሆናቸውም በላይ እውነተኛ ትንቢቶችን ይዘዋል። በተጨማሪም አንባቢዎቻቸው ሰዎችን እንዲወዱ ያበረታታሉ። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በእነዚህ ነገሮች ተለይተው ይታወቃሉ። ስለ አዋልድ መጻሕፍትስ እንዲህ ማለት ይቻላል?
የአዋልድ መጻሕፍት የተለዩ የሆኑት በምንድን ነው?
በአዋልድ መጻሕፍትና በቅዱሳን መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ በተካተቱት መጻሕፍት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። የአዋልድ መጻሕፍት የተዘጋጁት በቀኖና ውስጥ የተካተቱት መጻሕፍት ከተዘጋጁ ከረጅም ጊዜ በኋላ ማለትም ከሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ስለ ኢየሱስም ሆነ ስለ ክርስትና የሚሰጡት ማብራሪያም ቢሆን በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር አይስማማም።
ለምሳሌ ያህል፣ ከአዋልድ መጻሕፍት አንዱ የሆነው የቶማስ ወንጌል ማርያም ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንድትችል ኢየሱስ ወደ ወንድነት እንደሚቀይራት የሚገልጸውን ጨምሮ ስለ ኢየሱስ ግራ የሚያጋቡ በርካታ ትምህርቶችን ያስተምራል። ዚ ኢንፋንሲ ጎስፕል ኦቭ ቶማስ የተባለው መጽሐፍ ኢየሱስ ሆን ብሎ አንድ ልጅ እንዲሞት ያደረገ ጨካኝ ልጅ እንደነበረ ይገልጻል። የጳውሎስ ሥራ እና የጴጥሮስ ሥራ የተባሉት የአዋልድ መጻሕፍት ከፆታ ግንኙነት ፈጽሞ መራቅን የሚያበረታቱ ከመሆኑም ሌላ ሴቶች ከባሎቻቸው እንዲለያዩ ሐዋርያት ይመክሩ እንደነበር ይገልጻሉ። የይሁዳ ወንጌል፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በምግብ ሰዓት በመጸለያቸው ኢየሱስ እንደሳቀባቸው ይናገራል። እንዲህ ያሉ እምነቶች፣ ተቀባይነት ባገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙት ትምህርቶች ጋር የማይስማሙ ናቸው።—ማርቆስ 14:22፤ 1 ቆሮንቶስ 7:3-5፤ ገላትያ 3:28፤ ዕብራውያን 7:26
አብዛኞቹ የአዋልድ መጻሕፍት ግኖስቲሲዝም የሚባለው ሃይማኖታዊ ቡድን የሚያስፋፋውን አመለካከት የሚያንጸባርቁ ናቸው፤ ግኖስቲኮች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ጥሩ አምላክ እንዳልሆነ ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ትንሣኤ የሚከናወነው ቃል በቃል እንዳልሆነ፤ ቁስ አካል በሙሉ ክፉ እንደሆነ እንዲሁም ጋብቻንና መዋለድን ያመጣው ሰይጣን እንደሆነ ያምናሉ።
አንዳንዶቹን የአዋልድ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች እንደጻፏቸው ለማስመሰል ቢሞከርም ይህ ከእውነታው የራቀ ነው። እነዚህ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳይካተቱ ለማድረግ ተብሎ የተሸረበ ሴራ ይኖር ይሆን? በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ሞንተግዩ ሮድዝ ጄምስ እንዲህ ብለዋል፦ “ማንም ሰው ቢሆን እነዚህን መጻሕፍት ከአዲስ ኪዳን ለማውጣት ጥረት ማድረግ አላስፈለገውም፤ ይህን ያደረጉት ራሳቸው መጻሕፍቱ ናቸው።”
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ክህደት እንደሚነሳ አስጠንቅቀዋል
ተቀባይነት ባላቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤን የሚበክል ክህደት መነሳቱ እንደማይቀር የሚናገሩ በርካታ ማስጠንቀቂያዎችን እናገኛለን። እንዲያውም ይህ ክህደት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጀምሮ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሐዋርያት እንዳይሰራጭ አግደውት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3, 6, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1-3፤ 2 ጴጥሮስ 2:1፤ 1 ዮሐንስ 2:18, 19፤ 4:1-3) እንዲህ ያሉት ማስጠንቀቂያዎች ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ብቅ ማለት ስለጀመሩትና የኢየሱስን ትምህርቶች ስለሚቃረኑት መጻሕፍት ምንነት ለማወቅ ይረዱናል።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ምሑራንና ታሪክ ጸሐፊዎች እነዚህ መጻሕፍት ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ ከመሆናቸው የተነሳ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጣቸው እንደሆኑ ያስቡ ይሆናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ የተወሰኑ ምሑራን በዛሬው ጊዜ ከሚታተሙ ምናልባትም ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ከሚያወጡ መጽሔቶችና ጽንፈኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ከሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች ላይ ያሰባሰቧቸውን እርባና ቢስ ጽሑፎች አንድ ቦታ አስቀመጧቸው እንበል። ጊዜ እያለፈ መሄዱ እነዚህን ጽሑፎች እውነተኛና እምነት የሚጣልባቸው እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል? ከ1,700 ዓመታት በኋላ እነዚህ ጽሑፎች ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ በመሆናቸው ብቻ በውስጣቸው የያዙት ውሸትና እርባና የሌለው ነገር እውነት ሊሆን ይችላል?
ፈጽሞ ሊሆን አይችልም! በተመሳሳይም በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የሚገኙት ኢየሱስ፣ መግደላዊት ማርያምን እንዳገባ የሚገልጹትም ሆኑ በሬ ወለደ ዓይነት ሐሳብ የያዙት ሌሎቹ ሊታመኑ የማይችሉ ነገሮች ዘመናት ያስቆጠሩ ስለሆኑ ብቻ እውነት ሊሆኑ አይችሉም። እምነት የሚጣልባቸው መጻሕፍት በእጃችን እያሉልን እንደነዚህ ዓይነት አስተማማኝ ያልሆኑ ጽሑፎችን ማመን ለምን ያስፈልጋል? አምላክ ስለ ልጁ እንድናውቅ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር እምነት ልንጥልበት በምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል።
^ አን.4 “ቀኖና” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ያላቸውን ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ያመለክታል። የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ለመሆናቸው በሰፊው ተቀባይነት ያገኙት እንዲሁም የአምላክ ቃል ወሳኝ ክፍል የሆኑት መጻሕፍት 66 ናቸው።