በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ስለ ራሱ ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ስለ ራሱ ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ስለ ራሱ ምን አስተምሯል?

“ኢየሱስ ማን እንደሆነ፣ ከየት እንደመጣ፣ ወደ ምድራችን ለምን እንደመጣ እንዲሁም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀው ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበረውም።”—ደራሲ ኸርበርት ሎክየር

ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች ከመቀበላችንና በእነዚህ ላይ እምነት ከማሳደራችን በፊት ስለ እሱ ማወቅ የሚያስፈልገን ነገር አለ። ኢየሱስ ማን ነበር? የመጣው ከየት ነበር? ወደ ምድር የመጣበት ዓላማስ ምን ነበር? ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በጻፏቸው የወንጌል ዘገባዎች ላይ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከራሱ ከኢየሱስ አንደበት መስማት እንችላለን።

ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሕይወት ይኖር ነበር። ኢየሱስ “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” በማለት በአንድ ወቅት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:58) አብርሃም፣ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የኖረ ሰው ነው። ሆኖም ይህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊትም እንኳ ኢየሱስ በሕይወት ነበር። ታዲያ ኢየሱስ የሚኖረው የት ነበር? “ከሰማይ [ነው] የመጣሁት” በማለት መልሱን ሰጥቶናል።—ዮሐንስ 6:38

የአምላክ ልጅ። ይሖዋ መላእክት የሆኑ ብዙ ልጆች አሉት። ኢየሱስ ግን ከሁሉም ልዩ ነው። ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲናገር ‘የአምላክ አንድያ ልጅ’ እንደሆነ ገልጿል። (ዮሐንስ 3:18) ይህ አባባል አምላክ በቀጥታ የፈጠረው ኢየሱስን ብቻ እንደሆነ ያሳያል። አምላክ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ የፈጠረው በአንድያ ልጁ በኩል ነው።—ቆላስይስ 1:16

“የሰው ልጅ።” ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲናገር በብዛት የተጠቀመው በዚህ አገላለጽ ነው። (ማቴዎስ 8:20) በዚህ መንገድ ራሱን መጥራቱ፣ ሥጋ የለበሰ መልአክ ወይም በሰው አምሳል የመጣ አምላክ እንዳልሆነ ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ ሰው ነበር። አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት በሰማይ የሚኖረውን የልጁን ሕይወት ማርያም ወደተባለች ድንግል ማህፀን አዘዋወረው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለው ፍጹም ሰው ሆኖ በምድር ላይ ተወለደ።—ማቴዎስ 1:18፤ ሉቃስ 1:35፤ ዮሐንስ 8:46

ተስፋ የተደረገበት መሲሕ። አንዲት ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን “መሲሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ” ብላው ነበር። እሱም “እያነጋገርኩሽ ያለሁት እኔ እሱ ነኝ” በማለት መልሶላታል። (ዮሐንስ 4:25, 26) “መሲሕ” የሚለው ቃል “ክርስቶስ” እንደሚለው ቃል “የተቀባ” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ልዩ ሚና እንዲጫወት በአምላክ ተቀብቷል ወይም ተሹሟል።

የመጣበት ዋና ዓላማ። ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ለተቸገሩ ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን ያደረገ ቢሆንም በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የያዘው ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩ ሥራ ነበር። ስለዚህ መንግሥት ምን እንዳስተማረ በኋላ ላይ እንመለከታለን።

እስካሁን ካየናቸው ነጥቦች በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተራ ሰው አልነበረም። * ቀጥሎ ባሉት ርዕሶች ላይ እንደምንመለከተው ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሌሎችን በተሻለ መንገድ ለማስተማር የረዳው በሰማይ ያሳለፈው ሕይወት ነው። በእርግጥም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚነካ መልእክት መስበኩ ምንም አያስደንቅም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ስለ ኢየሱስም ሆነ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 4⁠ን ተመልከት።