ኢየሱስ ክርስቶስ—መልእክቱ የሰዎችን ሕይወት ምን ያህል ለውጧል?
ኢየሱስ ክርስቶስ—መልእክቱ የሰዎችን ሕይወት ምን ያህል ለውጧል?
“ለቅፍርናሆሙ ጠቢብ ሰው ከሁሉ ይበልጥ ሕያው ምሥክር የሚሆንለት አሁንም ድረስ የብዙዎችን ልብና አእምሮ መማረክ መቻሉ ነው።” *—ደራሲ ግሬግ ኢስተርብሩክ
ቃላት ከፍተኛ ኃይል አላቸው። ታስቦባቸው የተነገሩ ጥበብ ያዘሉ ቃላት ብዙዎችን ለሥራ ሊያነሳሱ፣ ተስፋ ሊፈነጥቁ እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት ሊለውጡ ይችላሉ። ኃይል ያላቸው ቃላትን በመናገር ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚተካከለው የለም። የተራራው ስብከት በመባል የሚታወቀውን የኢየሱስ ንግግር ያዳመጠ አንድ ሰው “ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ” በማለት ከጊዜ በኋላ ጽፏል።—ማቴዎስ 7:28
ኢየሱስ የተናገራቸው አብዛኞቹ ነገሮች ዛሬም በዓለም ዙሪያ ይታወቃሉ። ጥልቅ ትርጉም ያላቸውን አንዳንድ አባባሎች እስቲ እንመልከት።
“ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።”—ማቴዎስ 6:24
“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።”—ማቴዎስ 7:12
“የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ።”—ማቴዎስ 22:21
“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሲታወሱ የሚኖሩ አባባሎችን ብቻ በመናገር አልተወሰነም። ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ስለ አምላክ እውነቱን ስለሚገልጽ፣ ሰዎች የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም እንዲያውቁ ስለሚረዳ እንዲሁም የሰው ልጆች ለሚደርስባቸው ሥቃይ መፍትሔው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ በግልጽ ስለሚጠቁም ታላቅ ኃይል አለው። በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ ይህንን መልእክት ስንመረምር ኢየሱስ አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን “ልብና አእምሮ መማረክ” የቻለው ለምን እንደሆነ እንረዳለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]