በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው?

ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው?

▪ በአጭር አነጋገር መልሱ አዎን የሚል ነው። በብዙ ባሕሎች ውስጥ ከአንድ በላይ በሆነ ስም መጠራት የተለመደ ነገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ስሞች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ያዕቆብ፣ እስራኤል ተብሎም ይጠራ ነበር። (ዘፍጥረት 35:10) ሐዋርያው ጴጥሮስም ስምዖን፣ ኬፋ፣ ጴጥሮስና ስምዖን ጴጥሮስ በሚሉት የተለያዩ ስሞች ተጠርቷል። (ማቴዎስ 10:2፤ 16:16፤ ዮሐንስ 1:42፤ የሐዋርያት ሥራ 15:7, 14) ታዲያ ሚካኤል የኢየሱስ ሌላ ስም መሆኑን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች እንመልከት።

ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር የሆነውን አካል የሚያመለክተው ሚካኤል የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምስት ጊዜ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ የሚገኙት በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ነው። ዳንኤል 10:13, 21 ተልእኮ ተሰጥቶት የነበረውን አንድ መልአክ “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ” እንዲሁም “አለቃችሁ” ተብሎ የተጠራው ሚካኤል እንደረዳው ይገልጻል። ዳንኤል 12:1 ደግሞ በፍጻሜው ዘመን “ስለ ሕዝብህ የሚቈመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” ይላል።

ሚካኤል የሚለው ስም የተጠቀሰበት ሌላው ቦታ ራእይ 12:7 ሲሆን ጥቅሱ “ሚካኤልና መላእክቱ” ወሳኝ የሆነ ውጊያ እንዳካሄዱ በውጤቱም ሰይጣን ዲያብሎስና ክፉ የሆኑት የእሱ መላእክት ከሰማይ እንደተባረሩ ይገልጻል።

ከላይ ባሉት ጥቅሶች ሁሉ ላይ ሚካኤል ለአምላክ ሕዝቦች የሚዋጋና እነሱን የሚጠብቅ ተዋጊ መልአክ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹን ሌላው ቀርቶ የይሖዋ ዋነኛ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን ጋር መዋጋቱን ልብ በል።

ይሁዳ ቁጥር 9 ሚካኤልን “የመላእክት አለቃ” በማለት ይጠራዋል። “የመላእክት አለቃ” የሚለው መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ በብዙ ቁጥር አልተሠራበትም። የመላእክት አለቃ የሚለው መጠሪያ ከይሁዳ መጽሐፍ ሌላ ተጠቅሶ የምናገኘው በ1 ተሰሎንቄ 4:16 ላይ ብቻ ሲሆን በዚያ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ከሞት ስለተነሳው ኢየሱስ ሲናገር “ጌታ [ኢየሱስ] ራሱ በትእዛዝ ድምፅ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በአምላክ መለከት ከሰማይ ይወርዳል” ብሏል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመላእክት አለቃ ወይም ዋነኛ መልአክ እንደሆነ ተገልጿል።

ከላይ ከተመለከትናቸው ማስረጃዎች አንጻር ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው። ሚካኤል የሚለው ስም “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” እንዲሁም ኢየሱስ የሚለው ስም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም ያላቸው ሲሆን እነዚህ መጠሪያዎች ኢየሱስ የአምላክን ሉዓላዊነት በዋነኝነት እንደሚደግፍ ያጎላሉ። ፊልጵስዩስ 2:9 “አምላክ [ክብር ለተላበሰው ኢየሱስ] የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው” ይላል።

የኢየሱስ ሕይወት የጀመረው ሰው ሆኖ ሲወለድ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት አንድ መልአክ ወደ ማርያም በመምጣት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንደምትፀንስና የሚወለደውን ልጅ ኢየሱስ ልትለው እንደሚገባ ነግሯት ነበር። (ሉቃስ 1:31) ኢየሱስም በሚሰብክበት ወቅት ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕይወት በተደጋጋሚ ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:13፤ 8:23, 58

ስለዚህ የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ይጠራበት የነበረው ስም ነው። ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላም ዋነኛው መልአክ ሚካኤል በመሆን ማገልገሉን ቀጥሏል፤ ይህም “አባት ለሆነው አምላክ ክብር” ያመጣል።—ፊልጵስዩስ 2:11