በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ከዚህ ቀደም የወሮበሎች ቡድን አባልና የማሪዋና ሱሰኛ የነበረ ሰው ጎጂ ልማዶቹን ለማስወገድ የትኞቹን እርምጃዎች ወስዷል? የአንድ ባንድ አባል የነበረ ሰው ረጅም ፀጉሩን እንዲቆረጥና የሚወደውን ሙዚቃ በተመለከተ ያለውን ዝንባሌ እንዲለውጥ የረዳው ምንድን ነው? የሃይማኖትና የፖለቲካ ሰዎችን ሥልጣን የማይቀበል አንድ ሰው በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የአምላክ አገልጋይ እንዲሆን ያነሳሳው ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።

“ከሱሴ ተላቀቅኩ።”—ፒተር ካውሳንጋ

ዕድሜ፦ 32

የትውልድ አገር፦ ናሚቢያ

የኋላ ታሪክ፦ የወሮበሎች ቡድን አባልና የማሪዋና ሱሰኛ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት በሩንዱ ከተማ ትላልቅ ከሆኑት አራት መንደሮች ውስጥ ከሙ በሚባለው መንደር ነው። በዚህ መንደር የሚኖሩ ሰዎች የሚተዳደሩት ማሽላ፣ እንጨትና ከሰል በመሸጥ ነው።

ገና የሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ስለሞተች ያደግኩት ከአያቴ ጋር ነበር። ቀለል ያለ ኑሮ እንኖር ነበር። በተፈጥሮዬ ዓመፀኛ ባልሆንም በእኩዮች ተጽዕኖ ምክንያት ችግር ውስጥ ገባሁ። በትምህርት ቤት ሳለሁ የአንድ ወረበሎች ቡድን አባል ሆንኩ። በዚህ ምክንያት በየመንገዱ እደባደብ፣ እሰርቅና አልማዞችን በድብቅ አስገባ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጉልበተኛ እንዲሁም የአልኮልና የዕፅ ሱሰኛ ነበርኩ። ሁለት ጊዜ በሌብነትና በማጭበርበር ወንጀል ተይዤ ታስሬያለሁ።

አሥረኛ ክፍል እያለሁ ትምህርቴን አቋርጬ የምኖርበትን ከተማና የወሮበሎቹን ቡድን ትቼ ሄድኩ። ሕይወቴን የመለወጥ ፍላጎት ነበረኝ። ያም ሆኖ ከማሪዋና ሱስ መላቀቅ አልቻልኩም። አንዳንድ ጊዜ የማሪዋና ሲጋራ ለማግኘት ስል ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግሬ እጓዝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1999 መጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች በመንገድ ላይ ጽሑፎችን ሲያበረክቱ አገኛቸው ነበር። ያነጋግሩኝ የነበረው በአክብሮት ስለነበር ይህ ሁኔታ ልቤን በጥልቅ ነካው። በጽሑፎቹ ላይ ያነበብኩት ነገር እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እንዳምን አደረገኝ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት የጀመርኩ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ አምላክን ማስደሰት ከፈለግኩ አኗኗሬን መለወጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።

ማጨሴን ለማቆምና ከዚያ ጋር የተያያዙ ዕቃዎችን በሙሉ ለማስወገድ ቀን ወሰንኩ። ጓደኞቼንም ሲጋራ እንዳይሰጡኝና አጠገቤ ሆነው እንዳያጨሱ ነገርኳቸው። ይህን ሁሉ ባደርግም ነገሮች እንዳሰብኩት አልሆኑም። በሲጋራና በማሪዋና ሱስ ሁለት ጊዜ ተሸንፌያለሁ። ያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጥኩም። በምሳሌ 24:16 ላይ የሚገኘውን “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ሁልጊዜ አስታውስ ነበር። በመጨረሻም ከሱሴ ተላቀቅኩ።

ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅኩ መጠን እሱን ወዳጅ የማድረግ ፍላጎት አደረብኝ። ልቤን ከነኩት ጥቅሶች መካከል አንዱ በመዝሙር 27:10 ላይ የሚገኘው “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” የሚለው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናቴን ስቀጥል የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወቴ ማየት ችያለሁ። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ ተንከባካቢ አባት እውን ሆኖልኛል።

በተጨማሪም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አዘውትሬ መሰብሰብ ጀመርኩ። በመካከላቸው እውነተኛ ወዳጅነት እንዳለና እርስ በርሳቸው እንደሚዋደዱ መመልከት ችያለሁ። ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ፈጽሞ አይቼ አላውቅም ነበር።

ያገኘሁት ጥቅም፦ በይሖዋና በይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ በአለባበሴ፣ በፀጉር አያያዜ፣ በባሕርዬና በአነጋገሬ ማሻሻያ አድርጌያለሁ። መለስ ብዬ ሳስበው ሕይወቴ ከአንድ አስቀያሚ አባጨጓሬ ወደ የሚያምር ቢራቢሮ እንደተለወጠ ያህል ሆኖ ይሰማኛል። ዘመዶቼ ባደረግኩት ለውጥ ከመደሰታቸውም ሌላ አሁን የእነሱን አመኔታ ማግኘት ችያለሁ። በአሁኑ ጊዜ ያገባሁ ሲሆን ለባለቤቴ አፍቃሪ ባልና ለልጆቼ ተንከባካቢ አባት ለመሆን እየጣርኩ ነው።

“የሕይወትን እውነተኛ ዓላማ አገኘሁ።”—ማርኮስ ፓውሉ ደ ሶዘ

ዕድሜ፦ 29

የትውልድ አገር፦ ብራዚል

የኋላ ታሪክ፦ የትራሽ ሜታል ባንድ አባል

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ቤተሰቦቼ የሚኖሩት በሳኦ ፓውሎ፣ በዣግዋሪዩና ከተማ ውስጥ ነበር። ወላጆቼ አክራሪ ካቶሊኮች ስለነበሩ ወጣት ሳለሁ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገለግል ነበር። በመሆኑም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አብሬያቸው የምማር ልጆች አባ የሚል ቅጽል ስም አውጥተውልኝ ነበር። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ሄቪ ሜታል የሚባል የሮክ ሙዚቃ መስማት ጀመርኩ። ከሮክ ሙዚቃ አቀንቃኞች ጋርም ወዳጅነት መሠረትኩ። ፀጉሬን ማሳደግ ጀመርኩ። በ1996 በአባቴ እርዳታ ሙሉ የታምቡር መሣሪያዎችን መግዛት ቻልኩ።

በ1998 ትራሽ ሜታል የሚባል የሮክ ሙዚቃ የሚጫወት የአንድ ባንድ አባል ሆንኩ። የምንጫወተው ሙዚቃ ሰይጣናዊ አስተሳሰቦችን፣ ጸያፍ ምግባሮችንና ዓመፅን የሚያበረታታ ነበር። ይህ ሙዚቃ በአስተሳሰቤ፣ በባሕርዬና በዝንባሌዬ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረብኝ። በመሆኑም አፍራሽ አስተሳሰብ የተጠናወተኝና ቁጡ ሰው ሆንኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ለመጀመሪያ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ያገኘሁት በ1999 ነበር። ያን ያህል ፍላጎት ባይኖረኝም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ያቀረቡልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ይሁንና የተማርኩት ነገር ለሕይወት ያለኝን አመለካከት ለወጠው።

“ባለ ረጅም ፀጉሩ፣” “የሮክ ኮከብ” ወይም “ታምቡር መቺው” በመባል እታወቅ ነበር። በባንዱ ውስጥ መጫወቴ ስለራሴ ብቻ እንዳስብና የፉክክር መንፈስ እንዳሳደረብኝ ተገነዘብኩ፤ በነበረኝ ስምም አልደሰትም ነበር። እንደ አምላክ እመለከታቸው የነበሩ ዘፋኞች እውነተኛ ዓላማ እንደሌላቸው ተገነዘብኩ። ይሖዋ አምላክን ማስደሰት ከፈለግኩ የሄቪ ሜታል ሙዚቃን ብሎም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያለውን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗርና ጣዖት አምልኮ መተው እንዳለብኝ ውሎ አድሮ ተረዳሁ።

ሙዚቃ በመጫወቴና ፀጉሬን በማስረዘሜ እደሰት ነበር። ያለ እነዚህ ነገሮች መኖር የምችል አይመስለኝም ነበር። ግልፍተኛ ስለነበርኩም ይህን ባሕርዬን ማሸነፍ እንዳለብኝ ተረዳሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ አማካኝነት ይሖዋን ይበልጥ እየወደድኩት መጣሁ። ስለ አምላክ ፍቅር፣ ትዕግሥትና ምሕረት መማሬ ወደ እሱ እንድቀርብ አደረገኝ። ለውጥ ማድረግ እንድችል እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ የጸለይኩ ሲሆን እሱም ረድቶኛል። የዕብራውያን 4:12⁠ን ጥቅስ እውነተኝነት በራሴ ሕይወት ተመልክቼዋለሁ። ጥቅሱ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” ይላል።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ስጀምር የተለዩ ሰዎች መሆናቸውን ተገነዘብኩ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ፍቅር ተመለከትኩ። በተለይ ይህን ፍቅር በይሖዋ ምሥክሮች ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ተመልክቻለሁ። በዚህ ስብሰባ ላይ ለሌሎች ጥቅም ሲሉ በቅንዓት የሚሠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች አስገርመውኛል።

ያገኘሁት ጥቅም፦ በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ እርዳታ ንዴቴን መቆጣጠር ችያለሁ። አሁን ስለራሴ ብቻ የማስብና ኩራተኛ መሆኔን ያቆምኩ ይመስለኛል።

ለጥቂት ጊዜ የቀድሞ አኗኗሬ ይናፍቀኝ እንደነበር አልክድም፤ አሁን ግን ትዝ አይለኝም። በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ የሕይወት ዓላማ አለኝ። ስለ ሌሎች ሰዎች ፍላጎትና ደኅንነት ማሰብ የተማርኩ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።

“ሌሎች ሰዎችን በመርዳት ደስታ አገኘሁ።”—ጄፍሪ ኖበል

ዕድሜ፦ 59

የትውልድ አገር፦ ዩናይትድ ስቴትስ

የኋላ ታሪክ፦ የሃይማኖትና የፖለቲካ ሰዎችን ሥልጣን የማይቀበል

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት በኢፕስዊች፣ ማሳቹሴትስ የባሕር ዳርቻ አካባቢ በሚኖር አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ነው። ወጣት ሳለሁ ቨርሞንት በሚባል አንድ ገለልተኛ አካባቢ መኖር ጀመርኩ። ከሰሜን አሜሪካ ነዋሪዎች አንጻር እኔና የሴት ጓደኛዬ የመረጥነው ሕይወት በጣም ቀላል ነበር። ኤሌክትሪክ ስላልነበረን ቤታችንን የምናሞቀውና ምግብ የምንሠራው ከጫካ ውስጥ በምንለቅመው እንጨት ነበር። መጸዳጃ ቤታችን ከቤት ውጭ የተቆፈረ ጉድጓድ ሲሆን ዓመቱን ሙሉ ማለት ይቻላል ውኃ አይኖረንም ነበር። አለባበሳችንና አበጣጠራችን በዚያን ጊዜ የነበረውን ኅብረተሰብ እንደማንቀበል የሚያንጸባርቅ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ፀጉሬን ለስድስት ወር ባለማበጠሬ ኩራት ተሰምቶኝ ነበር።

በዚያን ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ከቬትናም ጋር እየተዋጋች ነበር። ይህ ደግሞ ለሥልጣን ባለኝ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አደረገብኝ። እንዲሁም በመንግሥትና በሃይማኖት ውስጥ ያለውን ግብዝነት ተመለከትኩ። ከእነዚህ ተቋማት ምንም መፍትሔ እንደማይገኝና እያንዳንዱ ሰው ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት በራሱ መወሰን እንዳለበት ተሰማኝ። በመሆኑም የምፈልገውን ነገር ብሰርቅ ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማኝ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? እኔና የሴት ጓደኛዬ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የጀመርን ቢሆንም ምንም ትርጉም ሊሰጠን አልቻለም። ዕፅ ስለምወስድ ለማቆም ጥረት አደርግ ነበር። የሴት ጓደኛዬ ተጋብተን ልጆች እንድንወልድ ትፈልግ ነበር። በዚህ ጊዜ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤታችን የመጣች ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስንም ታስጠናን ጀመር።

መጥፎ ልማዶቼን ለማቆም ጊዜ አልወሰደብኝም፤ ይሁንና ለሥልጣን ያለኝን አመለካከት ማስተካከል አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ሁሉንም ነገር የመጠራጠር ልማድ ነበረኝ። አስተዳደጌ ቁጥጥር ስላልነበረው የፈለግኩትን ማድረግ እችል ነበር፤ በመሆኑም በሌላ ሰው መመሪያ ሥር መኖር የሚለውን ሐሳብ መቀበል ለእኔ አስቸጋሪ ሆነብኝ።

ፈጣሪ እንዳለ ባምንም ስለ እሱ ግልጽ የሆነ እውቀት አልነበረኝም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር የይሖዋ አምላክ ባሕርያት ግልጽ እየሆኑልኝ መጡ። ከእኔ ምን እንደሚፈልግ የሚናገር በግልጽ የሰፈረ ነገር እንዳለ ተገነዘብኩ። ቀጥተኛና ግልጽ የሆኑ መመሪያዎች እንዳሉት ተማርኩ። በተጨማሪም ምድርን ገነት የማድረግ ግልጽ የሆነ ዓላማ እንዳለው አወቅኩ። (2 ጴጥሮስ 3:13) እነዚህ እውነታዎች አምላክን ማገልገል እንድችል መለወጥ እንዳለብኝ እንዳምን አደረጉኝ።

በተለይ የገረመኝ ነገር የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ማወቄ ነበር። እኔ ከማውቃቸው በዓለም ላይ ካሉ ሃይማኖቶች መካከል አንዱም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ይህን መመሪያ የሚከተል የለም።

ይሖዋን ማገልገል ከፈለግኩ አለባበሴንና የፀጉር አያያዜን ማስተካከል እንዳለብኝ አውቅ ነበር። መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን የአለባበስ ሥርዓት መከተል ከብዶኝ ነበር። እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ለስብሰባ የሚሆን ሸሚዝ፣ ሱሪ ወይም ጫማ አልነበረንም። ክራቫትማ ኖሮኝ አያውቅም! ይሁንና ፀጉሬን የተቆረጥኩ ሲሆን አለባበሴንም አስተካከልኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ለስብከት ከቤት ወደ ቤት ስሄድ የነበረውን ሁኔታ አስታውሳለሁ። አዲሱን አለባበሴን ለማየት መስታወት ፊት ቆምኩ። ከዚያም በመገረም ‘ምንድን ነው ያደረግኩት?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ብዙም ሳይቆይ አለባበሴን እየለመድኩት መጣሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ የሴት ጓደኛዬን ያገባኋት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በደስታ እየኖርን ነው። ሦስት ልጆቻችንን ይሖዋን የሚወዱና የሚያገለግሉ እንዲሆኑ አድርገን ማሳደግ ችለናል። ሕይወቴን እንድለውጥ የረዳኝን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች ሰዎች በማሳወቅም እደሰታለሁ።

ኩሩ ስለነበርኩ ሌሎች ምንም ያስቡ ምን ግድ አይሰጠኝም ነበር። አሁን ግን ስለ ሌሎች ሰዎች በማሰብና ሌሎች ሰዎች ስለ እኔ በማሰባቸው የሚገኘውን ደስታ በመቅመሴ አመስጋኝ ነኝ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የማሪዋና ሲጋራ ለማግኘት ስል ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግሬ እጓዝ ነበር”

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር ለሕይወት ያለኝን አመለካከት ለወጠው”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን የአለባበስ ሥርዓት መከተል ከብዶኝ ነበር”