በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ ያላቸው ሰዎች ምሕረት በሚፈልጉበት ጊዜ

‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ ያላቸው ሰዎች ምሕረት በሚፈልጉበት ጊዜ

ወደ አምላክ ቅረብ

‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ ያላቸው ሰዎች ምሕረት በሚፈልጉበት ጊዜ

2 ሳሙኤል 12:1-14

ሁላችንም ብዙ ጊዜ ኃጢአት እንሠራለን። በሠራነው ኃጢአት ምንም ያህል ብናዝንም እንኳ እንዲህ ብለን እናስብ ይሆናል፦ ‘ንስሐ ለመግባት ከልብ የማቀርበውን ጸሎት አምላክ ይሰማኝ ይሆን? ይቅር ይለኝስ ይሆን?’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን የሚያጽናና ሐቅ ይነግረናል፦ ይሖዋ ኃጢአትን ችላ ብሎ ባያልፍም ንስሐ የገባን አንድን ኃጢአተኛ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። በ2 ሳሙኤል ምዕራፍ 12 እንደተገለጸው ይህ ሁኔታ የጥንቷ የእስራኤል ንጉሥ በነበረው በዳዊት ላይ በግልጽ ታይቷል።

መቼቱን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ዳዊት ከባድ ኃጢአት ሠርቷል። ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ኃጢአቱን ለመደበቅ ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ሲቀር ባሏን ለማስገደል ዝግጅት አደረገ። በኋላም ዳዊት ኃጢአቱን ደብቆ ለበርካታ ወራት ንጹሕ ሰው በመምሰል ሲመላለስ ቆየ። ይሁንና ይሖዋ ሁኔታውን እየተመለከተ ነበር። ዳዊት የሠራው ኃጢአት ከይሖዋ የተሰወረ አልነበረም። በተጨማሪም ዳዊት ንስሐ ሊገባ እንደሚችል አስተውሎ ነበር። (ምሳሌ 17:3) ታዲያ ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን?

ይሖዋ ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። (ቁጥር 1) ናታን የሚናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለበት ስለተገነዘበ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ንጉሡን በዘዴ አነጋገረው። ዳዊት ራሱን እያታለለ መሆኑንና የፈጸመው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲገነዘብ እንዴት ይረዳው ይሆን?

ዳዊት ራሱን ነፃ ለማድረግ ሰበብ እንዳይፈጥር ሲል ከዚህ ቀደም እረኛ የነበረውን የዳዊትን ልብ እንደሚነካ እርግጠኛ የሆነበትን አንድ ታሪክ ነገረው። ታሪኩ ስለ አንድ ባለጠጋና ስለ አንድ ድሃ የሚናገር ነበር። ባለጠጋው “እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች” የነበሩት ሲሆን ድሃው ግን “አንዲት ጠቦት” ብቻ ነበረችው። ባለጠጋው እንግዳ ስለመጣበት ምግብ ማዘጋጀት ፈለገ። ከራሱ በጎች መካከል ወስዶ ከማዘጋጀት ይልቅ ድሃው ያለችውን አንዲት ጠቦት ወሰደ። ዳዊት የተነገረው ታሪክ እውነት መስሎት መሆን አለበት በጣም ተቆጥቶ “ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!” በማለት ተናገረ። ለምን? ዳዊት ምክንያቱን ሲናገር ‘ሐዘኔታ’ አላሳየም በማለት ገልጿል። *ቁጥር ከ2-6

ናታን የተጠቀመው ምሳሌ ግቡን መትቷል። ዳዊት በተዘዋዋሪ በራሱ ላይ እየፈረደ ነበር። ናታንም በግልጽ “ያ ሰው አንተ ነህ” አለው። (ቁጥር 7) ናታን አምላክን ወክሎ ይናገር ስለነበር ይሖዋ ዳዊት የፈጸመውን ድርጊት በእሱ ላይ እንደተፈጸመ በደል አድርጎ እንደወሰደው ግልጽ ነው። ዳዊት፣ የአምላክን ሕግ በመጣሱ ሕጉን ለሰጠው አካል አክብሮት እንደሌለው አሳይቷል። አምላክም “እኔን አቃለኸኛል” ብሎታል። (ቁጥር 10) ዳዊት በዚህ ከባድ ወቀሳ ልቡ ስለተነካ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” በማለት ኃጢአቱን ተናዟል። ናታን፣ ይሖዋ ይቅር እንደሚለው ለዳዊት አረጋግጦለታል፤ ይሁንና ዳዊት ድርጊቱ ካስከተለበት መዘዝ አያመልጥም።—ቁጥር 13, 14

ዳዊት ኃጢአቱ ገሃድ ከወጣ በኋላ በዛሬው ጊዜ መዝሙር 51 ተብሎ የሚጠራውን መዝሙር ጻፈ። በዚህ መዝሙር ላይ ዳዊት የልቡን አውጥቶ መናገሩ የተሰማውን ከባድ ጸጸት የሚያሳይ ነው። ዳዊት ኃጢአት በመሥራቱ ይሖዋን አቃሏል። ይሁን እንጂ የአምላክን መሐሪነት በሕይወቱ የቀመሰውና ንስሐ የገባው ንጉሥ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም” በማለት ለመናገር ችሏል። (መዝሙር 51:17) የይሖዋን ምሕረት ለሚሻ ንስሐ ለገባ አንድ ኃጢአተኛ ከሚያጽናኑ በርካታ ሐሳቦች መካከል አንዱ ይህ ጥቅስ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በጥንት ጊዜ እንግዳ ሲመጣ ጠቦት ማረድ የተለመደ ነበር። ሆኖም ጠቦት መስረቅ ወንጀል ስለነበር እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የፈጸመ ሰው አራት እጥፍ መክፈል ይጠበቅበታል። (ዘፀአት 22:1) ዳዊት፣ ባለጠጋው ሰው ጠቦቱን ከድሃው መውሰዱ ርኅራኄ የጎደለው ድርጊት እንደፈጸመ የሚያሳይ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ባለጠጋው ከድሃው ሰው ጠቦቱን መውሰዱ ቤተሰቡ የሚያገኘውን ወተት፣ ሱፍ ሌላው ቀርቶ ወደፊት ብዙ በጎችን ሊያረባበት የሚችልበትን አጋጣሚ ሁሉ ያሳጣዋል።