በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሰው እንዴት እዚህ አካባቢ ያቆማል?”

“ሰው እንዴት እዚህ አካባቢ ያቆማል?”

ከደቡብ አፍሪካ የተላከ ደብዳቤ

“ሰው እንዴት እዚህ አካባቢ ያቆማል?”

ወደ አንድ ገጠራማ አካባቢ በሚወስድ ጠባብ መንገድ ዳር “ዘራፊዎችና ዝሙት አዳሪዎች የበዙበት አደገኛ ቦታ” የሚል ጽሑፍ ይታያል። እኛም ይህን መንገድ አለፍ ብለን በጣም ውድ የሆነ የመዝናኛ ቦታ ያለበትን ስፍራ የሚያሳይ የማስታወቂያ ሰሌዳ አጠገብ ቆመው ከሚጠብቁ ሌሎች መኪኖች ጋር ለመቀላቀል ወደ አቧራማው የመንገዱ ዳር ወጣ ብለን መኪናችንን አቆምን። በጣም ውድ በሆኑ መኪኖች እየከነፉ የሚያልፉት ሰዎች በፊታቸው ላይ ‘ሰው እንዴት እዚህ አካባቢ ያቆማል?’ የሚል የመገረም ስሜት ይነበብባቸው ነበር።

መኪናችንን ካቆምን በኋላ ወርደን በማስታወቂያ ሰሌዳው ጥላ ሥር ተሰብስበው ከቆሙት ሥርዓታማ አለባበስ ካላቸው ሰዎች ጋር ተቀላቀልን። ቡድናችን የተለያየ ዘርና ባሕል ካላቸው ሰዎች የተውጣጣ ነበር፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን እንኳ እምብዛም በደቡብ አፍሪካ አይታይም። ከጆሃንስበርግ ከተማ ሰሜናዊ ምዕራብ ወደሚገኘው ወደዚህ ገጠራማ አካባቢ ወደ 100 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘን የመጣነው በዚያ ለሚኖሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማካፈል ነው።

በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ለመወያየትና ከቤት ወደ ቤት ለምናደርገው ስብከት አንዳንድ ዝግጅቶችን ለማድረግ በመንገዱ ዳር አጭር ስብሰባ አደረግን። ከጸለይን በኋላ ወደ መኪኖቻችን ተመለስን። ከሜዳው ባሻገር ቤቶችና ጎጆዎች ተሰበጣጥረው ይታያሉ። እነዚህ ቤቶችና ጎጆዎች ፕላቲኒየም ከሚወጣበት ጉድጓድ ተቆፍሮ ከወጣው የተቆለለ አፈር አንጻር ሲታዩ በጣም ትንንሽ ይመስላሉ። እዚህ አካባቢ ምድር በጉያዋ የያዘችው ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ቢኖርም የአካባቢው ሰው የሚኖረው በከፋ ድህነት ውስጥ ነው።

እኔና ባለቤቴ ከጀርመን ከመጡ ባልና ሚስት ጋር ሆነን የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ የጀመርነው ከቤት ወደ ቤት በማንኳኳት ነበር። እዚህ አካባቢ ከሚኖሩት ነዋሪዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሥራ የሌላቸው ሲሆን ቤቶቹም ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ናቸው። ብዙዎቹ ቤቶች ከቆርቆሮ የተሠሩ ሲሆን ቆርቆሮዎቹ በተወለጋገደ ማገር ላይ የተጠፈጠፈ የቆርኪ ክዳን ባላቸው ምስማሮች ተመትተዋል።

ወደ እያንዳንዱ ቤት ስንደርስ በራፉ ላይ ቆመን ሰላምታ ስንሰጥ ብዙውን ጊዜ የቤቱ እመቤት ወጥታ ታነጋግረናለች። የምናነጋግራቸው ሰዎች ይዘነው የሄድነውን መልእክት ለማዳመጥ የሚጓጉ ሲሆን እንደ ትልቅ እንግዳ በአክብሮት ይቀበሉን ነበር። ኃይለኛው ፀሐይ በጣሪያዎቹ ላይ ሲያርፍ ቤቶቹ በጣም ይሞቃሉ። ልጆች ብዙውን ጊዜ በዛፍ ጥላ ሥር የምንቀመጥባቸውን ወንበሮች ከቤት እንዲያመጡ ይላካሉ፤ ከዚያም በጥላው ሥር እንድንቀመጥ ይጋብዙናል።

ቤተሰቡ ይሰበሰብና በበርጩማዎች ወይም በተገለበጡ የዕቃ መያዣ ሣጥኖች ላይ ይቀመጣሉ። በቤት ውስጥ በተሠሩ መጫወቻዎች እየተጫወቱ ያሉ ትንንሽ ልጆችም እንኳ ሳይቀር እንዲያዳምጡ ይጠሩ ነበር። አንዳንድ ጥቅሶችን የምናነብላቸው ሲሆን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱት ጽሑፎቻችን እንዲያነቡ እንጋብዛቸዋለን። ያገኘናቸው ሰዎች ሁሉ ማለት ይቻላል ጽሑፎቻችንን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን በሌላ ጊዜ መጥተን እንድንጠይቃቸው ጋብዘውናል።

እኩለ ቀን ላይ ከዚህ በፊት ያነጋገርናቸውን ሰዎች ተመልሰን ለመጠየቅ ከመሄዳችን በፊት የያዝነውን ቀለል ያለ ምግብ ለመብላትና ቀዝቀዝ ያለ ነገር ለመጠጣት አገልግሎታችንን አቆምን። ከዚያ በኋላ በአካባቢው ካሉት የፕላቲኒየም ማዕድን ማውጫዎች ውስጥ በአንዱ የሚሠራውን ከማላዊ የመጣ ጂሚ የሚባለውን ሰው ለመጠየቅ ሄድን። ጂሚን ላለፉት ብዙ ወራት ስናነጋግረው ቆይተናል። ሁልጊዜ የሚቀበለን በደስታ ሲሆን ከእሱ ጋርም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እየተወያየን ጥቂት ጊዜ እናሳልፍ ነበር። ጂሚ በአካባቢው የሚኖሩ የሴፅዋና ጎሣ ተወላጅ የሆነች ሴት አግብቶ ሁለት ደስ የሚሉ ልጆች ወልደዋል። ባለፈው ጉብኝታችን ስላላገኘነው እሱን ለማግኘት ጓጉተን ነበር።

አነስተኛ ወደሆነው የጂሚ ቤት ስንቀርብ አንድ ችግር እንዳለ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብንም። ለወትሮው በደንብ ይያዝ የነበረው የጓሮ አትክልቱ ተመሰቃቅሎ፣ የዘራው በቆሎ ጠውልጎ የነበረ ከመሆኑም በላይ ጥሬ ፍለጋ መሬቱን ሲጭሩ ይታዩ የነበሩት ዶሮዎች የሉም። በሩ ከውጭ በኩል በትልቅ ሰንሰለት ተቆልፏል። የእኛን መምጣት ያስተዋለች አንዲት ጎረቤቱ ብቅ አለች። እኛም ጂሚ የት እንደሄደ ታውቅ እንደሆነ ጠየቅናት። እሷም አስደንጋጭ ዜና አረዳችን፤ ጂሚ እንደሞተ እንዲሁም ባለቤቱና ልጆቹ ከእሷ ቤተሰቦች ጋር ለመኖር እንደሄዱ ነገረችን።

ነገር ማውጣጣት እንደ ድፍረት የሚቆጠር ቢሆንም በዝርዝር ስለ እሱ ጠየቅናት። “አሞት ነበር በኋላም ሞተ። በዛሬው ጊዜ በሽታው በዝቷል። ብዙ ሰዎች እየሞቱ ነው” አለችን። ምንም እንኳ ሴትየዋ በምን በሽታ እንደሞተ ባትነግረንም፣ የተናገረችው ነገር እውነት ለመሆኑ በአካባቢው ባለው የቀብር ቦታ ላይ በመደዳ የተደረደሩት አዳዲስ መቃብሮች ጉልህ ምሥክር ናቸው። ከሴትዮዋ ጋር ስለ ትንሣኤ ተስፋ ጥቂት ከተወያየን በኋላ እያዘንን ከዚያ በፊት ወዳነጋገርነው ወደሌላ ሰው ቤት ሄድን።

ከዚያም ወደ ሌላ መንደር ገብተን በመደዳ እስከተሠሩት እስከ መጨረሻዎቹ ቤቶች ድረስ እየነዳን ሄድን፤ ቤቶቹ አካባቢ ከማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ወጥቶ የተቆለለ አፈር ይገኛል። የመንገዱ መጨረሻ ላይ ስንደርስ ታጥፈን ወደምንፈልገው ቤት ሄድን። በአትክልቱ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ድንጋይ ላይ “ለውሳኔ መወላወል የጊዜ ሌባ ነው፤ ዛሬ ነገ ማለት ደግሞ ዋና ግብረ አበሩ ነው” የሚል ትርጉም ያላቸው ቃላት በደማቅ ቀለም ተጽፈዋል። ምልክቱን የጻፈው ዴቪድ * ከድሮ ቮልስዋገን መኪናው ሞተር ኋላ ራሱን ብቅ አደረገ። እሱም የምትጠልቀው ፀሐይ በፈጠረችው ብርሃን ምክንያት ዓይኖቹን ሸብሸብ አድርጎ ሲመለከት እኛ መሆናችንን አወቀ፤ ከዚያም ፈገግ ሲል የፊቱ የወርቅ ጥርሶች አንጸባረቁ። እጁን እየጠራረገ ሰላም ሊለን ወደ እኛ መጣ።

“እንደምን ናችሁ ወዳጆቼ! የት ጠፋችሁ?” አለን። ዴቪድን እንደገና ስላገኘነው ደስ አለን። ባለፈው ካገኘነው በኋላ በማዕድን ማውጫ ድርጅት ውስጥ ሥራ ስላገኘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሥራ ስለሚመለስ ከእኛ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እንደማይችል ነግሮን ይቅርታ ጠየቀን። በውይይታችን ወቅት ሁሉ ዴቪድ ከፊቱ ላይ ፈገግታ አልተለየውም። “ለመጀመሪያ ጊዜ እናንተን ካገኘሁ ወዲህ ሕይወቴ ተለውጧል! እውነቴን ነው የምላችሁ፣ እናንተ ባትመጡ ኖሮ እስከ ዛሬ ምን ልሆን እንደምችል አላውቅም” በማለት በደስታ ስሜት ነገረን።

ደስ እያለን ዴቪድን ተሰናብተን ሄድን። ፀሐይዋ ለመጥለቅ ወደ አድማሷ ስታሽቆለቁል መኪናችንን አስነስተን ወደ ቤታችን አቀናን። በሚቦነው አቧራ የተነሳ ደብዘዝ ባለው ብርሃን ውስጥ ሜዳውን ለመጨረሻ ጊዜ አሻግረን ስንመለከት ‘እነዚህ ሁሉ ሰዎች ምሥራቹ የሚደርሳቸው እንዴት ይሆን? ብለን አሰብን። ኢየሱስ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው” በማለት የተናገረው ለምን እንደሆነ ገባን።—ሉቃስ 10:2

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ስሙ ተለውጧል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በደቡብ አፍሪካ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ፈቃድ የወጣ