በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ስለ ኃጢአት ያላቸውን አመለካከት የለወጠው ምንድን ነው?

ሰዎች ስለ ኃጢአት ያላቸውን አመለካከት የለወጠው ምንድን ነው?

ሰዎች ስለ ኃጢአት ያላቸውን አመለካከት የለወጠው ምንድን ነው?

‘በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች በመጀመሪያው ኃጢአት ማለትም ጥንት በተሠራ ከባድ ኃጢአት ምክንያት ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነናል የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። እንዲያውም ኃጢአት የሚባለውን ነገር አይቀበሉም። እንደ አዶልፍ ሂትለርና ዮዜፍ ስታሊን ያሉ ሰዎች ኃጢአት ሠርተው ሊሆን ይችላል፤ ሌሎቻችን የምንሠራው ግን ኃጢአት ሊባል አንችልም።’—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል

ይህ ሐሳብ እንደሚያሳየው ሰዎች ኃጢአትን በተመለከተ ያላቸው አስተሳሰብ በእጅጉ ተለውጧል። ምክንያቱ ምንድን ነው? የተለወጠውስ ምንድን ነው? ይሁንና ሰዎችን የሚያወዛግበው ኃጢአት የሚባለው ነገር ራሱ ምንድን ነው?

ሁለት ዓይነት ኃጢአት አለ፦ አንደኛው በዘር የተወረሰው ኃጢአት ሲሆን ሌላው ደግሞ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የሚፈጽሙት ኃጢአት ነው። የወረስነው ኃጢአት ወደድንም ጠላንም በውስጣችን ያለ ሲሆን ሁለተኛው ግን ሆን ብለን የምንፈጽመው ኃጢአት ነው። እስቲ እያንዳንዱን በዝርዝር እንመልከት።

በእርግጥ የመጀመሪያው ኃጢአት ተጽዕኖ አድርጎብናል?

መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የፈጸሙት የመጀመሪያው ኃጢአት ለሰው ዘሮች ሁሉ እንደተላለፈ ይናገራል። በመሆኑም ሁላችንም ፍጽምና ጎድሎን ተወልደናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ ያልሆነ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው” ይላል።—1 ዮሐንስ 5:17

ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ ብዙ ሰዎች እነሱ በማያውቁትና ሊጠየቁበት በማይገባ ጥንት በተሠራ ኃጢአት ሳቢያ ‘ሰዎች ሁሉ ፍጽምና ጎድሏቸው ተወልደዋል’ የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ የማይገባቸውና የማይቀበሉት ነው። የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ኤድዋርድ ኦክስ ይህን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል፦ “አብዛኞቹ ሰዎች ይህ ዓይነቱ ትምህርት ያሳፍራቸዋል፣ ሌሎች ወዲያውኑ ይቃወሙታል፤ አንዳንዶች ደግሞ አስተሳሰቡን ፊት ለፊት ባይቃወሙትም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ በትክክል ስለማያውቁ ለአፋቸው ያህል ይቀበሉታል።”

ብዙዎች የመጀመሪያው ኃጢአት የሚለውን ሐሳብ መቀበል እንዲከብዳቸው የሚያደርገው አንደኛው ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት ኃጢአትን በሚመለከት የሚያስተምሩት ትምህርት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቤተ ክርስቲያን በትሬንት ጉባኤ ላይ (1545-1563) አንድ አራስ ልጅ ከኃጢአቱ ለመንጻት መጠመቅ አለበት የሚለውን ሐሳብ የሚቃወሙ ሰዎችን አውግዛ ነበር። የሃይማኖት አስተማሪዎች አንድ ሕፃን ከመጠመቁ በፊት ቢሞት ከኃጢአቱ ስላልነጻ አምላክ ወደሚገኝበት ወደ ሰማይ ለዘላለም መግባት አይችልም የሚል ትምህርት ያስተምሩ ነበር። ካልቪን ደግሞ ሕፃናት ‘ከእናታቸው ማህፀን ኩነኔያቸውን ይዘው ይወጣሉ’ በማለት አስተምሮ ነበር። እንዲያውም ይዘውት የሚወለዱት ኃጢአት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ‘አምላክ ይጸየፋቸዋል’ የሚል አመለካከት ነበረው።

ብዙ ሰዎች ሕፃናት ንጹሐን እንደሆኑ ስለሚሰማቸው በወረሱት ኃጢአት ምክንያት ሊሠቃዩ ይገባል የሚለው አስተሳሰብ ለሰው አእምሮ የሚከብድ ሐሳብ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሰዎች ስለ መጀመሪያው ኃጢአት የተዛባ አመለካከት ሊኖራቸው የቻለው እንዲህ ባሉ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያልተጠመቁ ሕፃናት ገሃነመ እሳት ውስጥ ይገባሉ የሚል አቋም የላቸውም። ይሁንና እነዚህ አስተማሪዎች ሕፃናት ከሞቱ በኋላ የሚሄዱበት ቦታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ይህ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ ውስጥ ባይታቀፍም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‘ያልተጠመቁ ንጹሕ ነፍሳት በገነትና በገሃነም መካከል በሚገኝ ሊምቦ * በሚባል ምንነቱ በማይታወቅ ስፍራ ይኖራሉ’ በማለት ለብዙ ዘመናት ስታስተምር ቆይታለች።

ሰዎች ስለ መጀመሪያው ኃጢአት የሚነገረውን ሐሳብ መቀበል እንዲከብዳቸው ያደረገው ሌላው ምክንያት በ19ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶችና የሃይማኖት አስተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ዘገባዎችን ትክክለኝነት መጠራጠር መጀመራቸው ነው። የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ብዙ ሰዎች የአዳምና የሔዋን ታሪክ አፈ ታሪክ ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ፣ መለኮታዊ ምንጭ ያለው ሳይሆን የጸሐፊዎቹን አስተሳሰብና ባሕል የሚያንጸባርቅ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ።

ታዲያ ይህ አስተሳሰብ ሰዎች ስለ መጀመሪያው ኃጢአት ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ ሰዎች አዳምና ሔዋን በገሃዱ ዓለም ያልነበሩ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው ካመኑ የመጀመሪያው ኃጢአት ተፈጽሟል ብለው እንደማያምኑ የታወቀ ነው። የሰው ዘር እንከን እንዳለበት አምነው የሚቀበሉ ሰዎች እንኳ የመጀመሪያው ኃጢአት የሚለውን ሐሳብ የሚያዩት ሰው ፍጽምና ይጎድለዋል የሚል ትርጉም እንዳለው አድርገው ነው።

ስለ መጀመሪያው ኃጢአት ይህን ያህል ከተነጋገርን በውርስ ከሚገኘው ኃጢአት ስለሚለየውና አምላክን ስለሚያሳዝነው በግለሰብ ደረጃ ስለሚፈጸመው ኃጢአትስ ምን ማለት ይቻላል?

በእርግጥ ይህ ኃጢአት ነው?

ብዙ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ስለሚፈጸመው ኃጢአት ሲጠየቁ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው መግደልን፣ ታማኝነት ማጉደልን፣ መመኘትን፣ ዝሙትን፣ መስረቅንና የመሳሰሉትን መጥፎ ድርጊቶች የሚከለክለው አሥርቱ ትእዛዛት ነው። አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ኃጢአቶች ሠርቶ ንስሐ ሳይገባ የሞተ ሰው በገሃነመ እሳት * ለዘላለም ይሠቃያል የሚል ትምህርት ለረጅም ዘመን ሲያስተምሩ ቆይተዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ከዚህ ቅጣት መዳን የሚፈልጉ ከሆነ ኃጢአታቸውን የመሰረዝ ሥልጣን ላላቸው ቀሳውስት መናዘዝ እንደሚኖርባቸው ታስተምራለች። ይሁን እንጂ በርካታ ካቶሊኮች የመናዘዝ፣ ኃጢአትን የመፍታትና ንስሐ የመግባት ሥርዓት ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ የጣሊያን ካቶሊኮች ለመናዘዝ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም።

አንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ የሚፈጽመውን ኃጢአትና ኃጢአቱ የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ስታስተምረው የቆየችው ትምህርት ሰዎች ከኃጢአት እንዲቆጠቡ እንዳላደረጋቸው ግልጽ ነው። ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ በርካታ ሰዎች እነዚህ ነገሮች ስህተት ናቸው ብለው አያምኑም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ‘ለአካለ መጠን የደረሱ ሁለት ሰዎች ሌላ ሦስተኛ ሰው እስካልተጎዳ ድረስ የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ምን ችግር አለው?’ ብለው ይናገራሉ።

ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው መሆኑ ስለ ኃጢአት የተማሩትን ትምህርት ከልብ እንደማያምኑበት ያሳያል። በእርግጥም ብዙዎች አፍቃሪ የሆነ አምላክ ሰዎችን ለዘላለም በገሃነመ እሳት ያቃጥላል ብሎ ማመን ይከብዳቸዋል። ምናልባትም እንዲህ ያለው አመለካከት ሰዎች “ኃጢአትን” አክብደው የማያዩት ለምን እንደሆነ በተወሰነ ደረጃ ግልጽ ያደርግልናል። ሰዎች ስለ ኃጢአት ያላቸው ግንዛቤ እንዲዛባ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።

ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ ባሕላዊ እሴቶች ተቀባይነት አጡ

ባለፉት መቶ ዓመታት የተከሰቱ ነገሮች በኅብረተሰቡና በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትለዋል። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች፣ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አነስተኛ ጦርነቶችና የተለያዩ የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች በርካታ ሰዎች ለብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ ባሕላዊ እሴቶች ያላቸውን ጠቀሜታ እንዲጠራጠሩ አድርገዋቸዋል። ‘በቴክኖሎጂ በተራቀቀው በዚህ ዓለም ውስጥ ከዘመናዊው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በራቀ ጥንታዊ መጽሐፍ መመራት ተገቢ ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ። በእምነት ሳይሆን በምክንያት የሚያምኑና ሥነ ምግባርን የሚያጠኑ በርካታ ሰዎች ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ኅብረተሰቡ አንዳንድ ማነቆዎችንና አጉል እምነቶችን አስወግዶ ራሱን በማስተማር እምቅ ችሎታውን መጠቀም የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ብለው ያምናሉ።

ይህ አስተሳሰብ ሰዎች ይበልጥ ከአምላክ እንዲርቁ አድርጓቸዋል። በብዙ የአውሮፓ አገሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ከስንት አንድ ናቸው። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ይህ ነው የሚባል እምነት የላቸውም፤ ብዙዎቹ ደግሞ እርባና የሏቸውም የሚሏቸውን የቤተ ክርስቲያን ደንቦች በግልጽ ይቃወማሉ። ሰዎች የዝግመተ ለውጥና የተፈጥሯዊ ምርጦሽ ውጤት ከሆኑ አንድን የሥነ ምግባር መመሪያ መጣስ ስለሚያስከትለው ነገር ማውራቱ ምን ዋጋ አለው? ብለው ይናገራሉ።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን በምዕራቡ ዓለም ሰዎች ልቅ የሥነ ምግባር አቋም መያዛቸው ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምሮ ኅብረተሰቡን ወደ ፆታ አብዮት መርቶታል። የተማሪዎች ተቃውሞ፣ ወጣ ያሉ ባሕሎችን የመከተል እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች መፈልሰፍ ዘመናት ያስቆጠሩ አስተሳሰቦች ተቀባይነት እንዲያጡ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ቸል መባል ጀመሩ። አዲሱ ትውልድ ኃጢአትን በተመለከተ አዲስ ምግባርና አስተሳሰብ ይዞ ብቅ አለ። አንድ ጸሐፊ እንደተናገሩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ “ብቸኛው ሕግ የፍቅር (የተቃራኒ ፆታ ፍቅር) ሕግ ሆነ”፤ ይህ ደግሞ ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነት ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል።

ሰዎችን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሃይማኖታዊ ባሕል

ኒውስዊክ የተባለው መጽሔት በዩናይትድ ስቴትስ ስላለው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ምዕመናንን የመሳብ ገበያ በደራበት የፉክክር ዓለም ውስጥ በርካታ ቀሳውስት ብቻቸውን መቅረት እንደማያዋጣ ይሰማቸዋል።” ‘አድማጮቻችንን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲከተሉ ከጠየቅን ምዕመናኖቻችንን እናጣለን’ ብለው ይፈራሉ። ሰዎች ትሕትናን እንዲያዳብሩ ራሳቸውን እንዲገሥጹና ጨዋዎች እንዲሆኑ ወይም እረፍት የሚነሳ ሕሊናቸውን እንዲሰሙና ከኃጢአታቸው ንስሐ እንዲገቡ የሚነግራቸውን ሰው መስማት አይፈልጉም። በመሆኑም በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ “ወንጌልን ወደጎን ገሸሽ አድርጎ ዘና የሚያደርግ፣ ብዙኃኑን የሚጠቅም አልፎ ተርፎም ‘ስለ እኔ ብቻ’ የሚል ራስን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ክርስቲያናዊ ስብከት” በማለት ቺካጎ ሰን-ታይምስ የገለጸው ዓይነት አዝማሚያ እየታየ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት መስፋፋቱ ለአምላክ የራሱን ፍቺ የሚሰጥ እንዲሁም ለአምላክና እሱ ከሰዎች ለሚፈልገው ነገር ሳይሆን ለሰዎችና ለግለሰቦች ክብር ለሚጨምር ነገር የበለጠ ትኩረት የሚሰጥ ሃይማኖታዊ ባሕል እንዲዳብር ምክንያት ሆኗል። ዋና ዓላማቸው የጉባኤያቸውን ፍላጎት ማሟላት ነው። ይህ ደግሞ ሃይማኖታቸውን መሠረተ ትምህርት የሌለው እንዲሆን አድርጎታል። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል “የክርስትና የሥነ ምግባር መመሪያ ችላ በመባሉ ምክንያት የተፈጠረው ክፍተት በምን ይሞላ?” በማለት ጠይቋል። አክሎም “ብቸኛው የሥነ ምግባር መመሪያ ሩኅሩኅ መሆን ነው፤ አንድ ሰው ‘ጥሩ ከሆነ’ ማንኛውም ስህተት ይቅር ይባልለታል” ብሏል።

እንዲህ ያለው ዝንባሌ ‘ሰዎችን ደስ የሚያሰኝ ማንኛውም ሃይማኖት ጥሩ ነው’ የሚል አመለካከት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደገለጸው እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያለው ማንኛውም ሰው “አንድ ሃይማኖት ተከታዮቹ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን እንዲከተሉ እስካልጠየቀ እንዲሁም የሚኮንን ሳይሆን የሚያጽናና እስከሆነ ድረስ የትኛውንም ሃይማኖት መያዝ ይችላል።” አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በበኩላቸው ከሥነ ምግባር አኳያ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይጠይቁ “ሰዎችን ከነአመላቸው” ለመቀበል ፈቃደኛ ናቸው።

እስከ አሁን የተመለከትነው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎችን ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የጻፈውን ትንቢት ሳያስታውሳቸው አይቀርም። እንዲህ ብሏል፦ “ጤናማውን ትምህርት የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ፤ እንዲሁም እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

የሃይማኖት መሪዎች ኃጢአትን ችላ ብለው ሲያልፉ፣ መኖሩን እንኳ ሲክዱ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ከማስተማር ይልቅ አድማጮቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ በመናገር የምዕመናኖቻቸውን ‘ጆሮ ሲኮረኩሩ’ ለምዕመናኖቻቸው መቃብር እየቆፈሩላቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ መልእክት ሐሰት ከመሆኑም በላይ አደገኛ ነው። እንዲሁም መሠረታዊ ከሆነው የክርስትና ትምህርት ጋር ይጋጫል። ኃጢአትና ምሕረት ማድረግ ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ ያስተማሩት ምሥራች አቢይ ክፍል ናቸው። የዚህን አባባል እውነተኝነት ለመረዳት የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ሊምቦ ብዙ ሰዎችን ግራ የሚያጋባ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው ትምህርት ነው፤ ምናልባትም ቃሉ በቅርብ ጊዜ በሚወጡ የካቶሊክ ማስተማሪያ ጽሑፎች ውስጥ ያልተካተተው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። “በሃይማኖታዊ ትምህርት ረገድ የተደረገ ሥር ነቀል ለውጥ” የሚለውን በገጽ 10 የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.14 በገሃነመ እሳት ለዘላለም መሠቃየት የሚለው ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በሚለው መጽሐፍ ላይ “ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ምዕራፍ 6⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰዎችን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሃይማኖታዊ ባሕል መጥፎ ፍሬ ያፈራል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኃጢአት ‘ሊያስጨንቀን የማይገባ ጉዳይ’ ሆኗል?

▪ “በዛሬው ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ እንቅፋት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ራሳችንን ይቅርታ የሚያስፈልገን ‘ኃጢአተኞች’ አድርገን መመልከት አቁመናል። ድሮ ኃጢአት ያሳስበን ነበር፤ አሁን ግን ሊያስጨንቀን የሚገባ ነገር አይደለም። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ለኃጢአት ችግር መፍትሔ ስታገኝ በብዙ አሜሪካኖች ዘንድ ግን ኃጢአት እንደ ችግር ቢያንስ እንደ ከባድ ችግር መታየቱ ቀረ።”—ጆን ስቱድቤከር ጁኒየር፣ የሃይማኖት ርዕሰ ጉዳዮች ጸሐፊ

▪ “ሰዎች እንደሚከተለው ሲሉ ይደመጣል፦ ‘ከራሴም ሆነ ከሌሎች ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም እጠብቃለሁ፤ ሆኖም ሁላችንም ሰዎች መሆናችንን ስለማውቅ አማካይ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ።’ ከሥነ ምግባር አኳያ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለን እንዲሰማን መካከለኛ የሥነ ምግባር ደረጃ እንዲኖረን እንፈልጋለን። . . . ሆኖም ከኃጢአት ጋር ስለሚያያዙት ትላልቅ ርዕሰ ጉዳዮች ማሰብ አንፈልግም።”—አልበርት ሞለር፣ የሳውዘርን ባፕቲስት ቲኦሎጂካል ሴሚናር ፕሬዚዳንት

▪ “ሰዎች ከዚህ በፊት አሳፋሪ ተደርገው ይታዩ በነበሩ ነገሮች [ለምሳሌ፣ በሰባቱ ቀሳፊ ኃጢአቶች] መኩራራት ጀምረዋል፦ ወላጆች ልጆቻቸው ለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል በሚል ስሜት ኩሩዎች እንዲሆኑ ያበረታቷቸዋል፤ ራሳቸውን የሚኮፍሱ አንዳንድ የፈረንሳይ የወጥ ቤት ሠራተኞች ሆዳምነት እንደ ኃጢአት እንዳይቆጠር ቫቲካንን ጠይቀዋል። ሰዎች በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ታዋቂ ሰዎችን ሕይወት እንዲኮርጁ የሚያነሳሳቸው ቅናት ነው። ምኞት ዓይነተኛ የማስታወቂያ መሣሪያ ነው፤ አንድ ሰው ከተናደደ መቆጣቱ ያለ ነገር ነው። አንዳንዴ ቀኑን ሰነፍ ሆኜ ባሳልፈው ደስ ይለኛል።”—ናንሲ ጊብስ፣ ታይም መጽሔት

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ታሪክ እንደ አፈ ታሪክ ይመለከቱታል