በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኃጢአትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

ኃጢአትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

ኃጢአትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

አንድ የታመመ ሰው ትኩሳት እንደሌለው የሚያረጋግጠው የሙቀት መለኪያ መሣሪያውን በመስበር ነው? እንዳልሆነ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም ብዙ ሰዎች አምላክ ስለ ኃጢአት ያለውን አመለካከት ስላልተቀበሉ ኃጢአት የለም ማለት አይደለም። ቃሉ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በሚመለከት ብዙ የሚናገረው ነገር አለ። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት የሚያስተምረው ምንድን ነው?

ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል

ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ‘የሚመኘውን መልካም ነገር እንደማያደርግ ከዚህ ይልቅ የማይፈልገውን መጥፎ ነገር የማድረግ ልማድ እንዳለው’ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተናግሯል። (ሮም 7:19) ሐቀኞች ከሆንን ሁላችንም ተመሳሳይ ችግር እንዳለብን አምነን እንቀበላለን። ምናልባት በአሥርቱ ትእዛዛት ወይም በሌሎች የሥነ ምግባር ሕጎች መመራት ፍላጎት ይኖረን ይሆናል፤ ሆኖም ወደድንም ጠላንም ሕጉን ሙሉ በሙሉ መፈጸም አንችልም። ይህ የሚሆነው ሆነ ብለን ሕጉን ስለምንጥስ ሳይሆን ሁላችንም ደካሞች በመሆናችን ነው። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ጳውሎስ ራሱ መልሱን እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “እንግዲህ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን በውስጤ የሚኖረው ኃጢአት ነው።”—ሮም 7:20

እንደ ጳውሎስ ሁሉ መላው የሰው ልጅ በዘር የወረሰው ድክመት አለበት፤ ይህ ደግሞ በዘር የሚወረስ ኃጢአትና አለፍጽምና እንዳለ ማስረጃ ይሆናል። ሐዋርያው “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ብሏል። ታዲያ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 3:23፤ 5:12

ብዙ ሰዎች የመጀመሪያ ወላጆቻችን የሠሩት ኃጢአት ከአምላክ እንድንርቅ እንዲሁም ፍጽምናን እንድናጣ አድርጎናል የሚለውን ሐሳብ ባይቀበሉትም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ይህንን ነው። ኢየሱስ ከዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ በመጥቀስ ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ታሪክ እንደሚያምንበት አሳይቷል።—ዘፍጥረት 1:27፤ 2:24፤ 5:2፤ ማቴዎስ 19:1-5

መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው ዋና ዋና ትምህርቶች መካከል ኢየሱስ በእሱ የሚያምኑ ሰዎችን ከኃጢአት ለማዳን ወደ ምድር እንደመጣ የሚናገረው ትምህርት ይገኝበታል። (ዮሐንስ 3:16) የወደፊቱ ሕይወታችን የተመካው ይሖዋ አድናቂ የሆኑ የሰው ልጆችን ከቁጥጥራቸው ውጪ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት በመቀበላችን ላይ ነው። ይሁንና አምላክ ኃጢአትን በሚመለከት ስላለው አመለካከት ግልጽ የሆነ እውቀት ከሌለን አምላክ እኛን ከኃጢአት ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ልንረዳ አንችልም።

የኢየሱስ መሥዋዕትና አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት

ይሖዋ ለመጀመሪያው ሰው ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቶት ነበር። አዳም ይህን አስደናቂ ተስፋ ሊያጣ የሚችለው በአምላክ ላይ ካመፀ ብቻ ነበር። አዳም በአምላክ ላይ ያመፀ ሲሆን በዚህም ምክንያት ኃጢአተኛ ሆነ። (ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:6) አዳም ከአምላክ ፈቃድ ተቃራኒ የሆነ ነገር በማድረጉ ፍጽምናውን አጣ፤ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና ተበላሸ። መለኮታዊውን ሕግ በመጣስ ኃጢአት በመፈጸሙ ምክንያት ማርጀት ጀመረ፤ በመጨረሻም ሞተ። የሚያሳዝነው ግን እኛን ጨምሮ ሁሉም የአዳም ዘሮች የሚወለዱት ኃጢአተኞች ሆነው ነው፤ በዚህ የተነሳ ሁላችንም ለሞት ተዳርገናል። ግን ለምን?

መልሱ ቀላል ነው። ፍጽምና የጎደላቸው ወላጆች ፍጹም ልጅ ሊወልዱ አይችሉም። ሁሉም የአዳም ልጆች የተወለዱት ኃጢአተኛ ሆነው ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ደግሞ “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው።” (ሮም 6:23) የዚህ ጥቅስ ቀጣዩ ክፍል ግን “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ተስፋ ይሰጠናል። ይህም ሲባል ታዛዥና አድናቂ የሆኑ የሰው ልጆች በኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አማካኝነት አዳም የፈጸመው ኃጢአት ካስከተለው ውጤት ይነጻሉ ማለት ነው። * (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19) ታዲያ ይህ ምን እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይገባል?

የክርስቶስ ፍቅር “ግድ ይለናል”

ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለዚህ ጥያቄ የአምላክን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መልስ ሰጥቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል፤ . . . በሕይወት ያሉት ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) አንድ ሰው የኢየሱስ መሥዋዕት እሱን ከኃጢአት የማንጻት ኃይል እንዳለው ከተገነዘበና ለዚህ ዝግጅት ያለውን አድናቆት ማሳየት ከፈለገ አምላክ የሚጠብቅበትን ነገር ለማድረግ መጣር ይኖርበታል። ይህ ደግሞ አምላክ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ መጣርን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት መሠረት ሕሊናውን ማሠልጠንና ከእነዚህ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጨምራል።—ዮሐንስ 17:3, 17

ኃጢአት ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል። ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ምንዝርም ሆነ ባሏን ማስገደሉ ከባድ ኃጢአት መሆኑን ሲገነዘብ በጣም አፍሮ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ሆኖም በጣም አስጨንቆት የነበረው ነገር በሠራው ኃጢአት አምላክን ያሳዘነ መሆኑ ነው፤ ደግሞም ሊያስጨንቀው የሚገባው ይህ ነበር። ዳዊት በሁኔታው በጣም እንዳዘነ ለይሖዋ “አንተን፣ በእርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ” በማለት ገልጿል። (መዝሙር 51:4) በተመሳሳይም ዮሴፍ ዝሙት እንዲፈጽም ሲፈተን ሕሊናው “እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” በማለት እንዲጠይቅ አነሳስቶታል።—ዘፍጥረት 39:9

እንግዲያው ኃጢአት አንድ ስህተት ከሠራን በኋላ ሲታወቅብን የማዘን ጉዳይ ብቻ አይደለም። ምናልባት አንድ ስህተት ከሠራን በኋላ ለሕዝብ ወይም ለኅብረተሰቡ መልስ የመስጠት ጉዳይ ብቻም አይደለም። አምላክ ከፆታ ግንኙነት፣ ከሐቀኝነት፣ አክብሮት ከመስጠት፣ ከአምልኮ እንዲሁም እነዚህን ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር በተያያዘ ያወጣውን ሕግ ብንጥስ ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ይበላሻል። ሆነ ብለን ኃጢአት የምንሠራ ከሆነ ራሳችንን የአምላክ ጠላቶች እያደረግን ነው። ትኩረት ሰጥተን ልናስብበት የሚገባ እውነታ ይህ ነው።—1 ዮሐንስ 3:4, 8

ታዲያ ኃጢአትን በተመለከተ የተለወጠ ነገር ይኖር ይሆን? ሰዎች የኃጢአትን ክብደት ለመቀነስ ሲሉ ለኃጢአት የተለያየ ስያሜ መስጠት ጀመሩ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም። ብዙዎች ሕሊናቸውን አደንዝዘውታል አሊያም የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ቸል ይላሉ። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲህ ዓይነቱን ዝንባሌ መዋጋት ይገባቸዋል። ቀደም ሲል እንዳየነው ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ የሕሊና ጠባሳ ወይም ኃፍረት ብቻ ሳይሆን ሞት ነው። ኃጢአት የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው።

ደስ የሚለው ነገር ለሠራነው ኃጢአት ከልብ በመነጨ ስሜት ንስሐ ከገባንና ያንን ኃጢአት መሥራት ካቆምን የኢየሱስ መሥዋዕት ያለው ኃጢአትን የማስተሰረይ ኃይል ይቅርታ ያስገኝልናል። ጳውሎስ “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው፤ ይሖዋ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል።—ሮም 4:7, 8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን የሚያድናቸው እንዴት እንደሆነ የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 47 እስከ 54 ተመልከት።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሃይማኖታዊ ትምህርት ረገድ የተደረገ ሥር ነቀል ለውጥ

ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ አብዛኞቹ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በገነትና በገሃነም መካከል ይገኛል ተብሎ ስለሚታሰበው ሊምቦ ስለሚባለው ስፍራ ግልጽ የሆነ እውቀት ኖሯቸው አያውቅም። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ማስተማር ቀስ በቀስ ስለቀረ አሁን አሁን በካቶሊክ የሃይማኖት ማስተማሪያ ጽሑፎች ውስጥ አይካተትም። በ2007 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ከሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ሥነ ሥርዓቶች አንጻር ሲታይ፣ ሳይጠመቁ የሚሞቱ ሕፃናት ሊድኑና ወደ ዘላለማዊ ደስታ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ምክንያት” እንዳለ በሚገልጽ ሰነድ ላይ ሊምቦ እንዳከተመለት በሚያሳውቅ “የሞት ሰርተፊኬት” ላይ በይፋ ፈርማለች።—ኢንተርናሽናል ቲኦሎጂካል ኮሚሽን

የሃይማኖት አስተማሪዎች እንዲህ ያለ ሥር ነቀል ለውጥ ያደረጉት ለምንድን ነው? ኦንሪ ቴንክ የተባለ ፈረንሳዊ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ ይህ ትምህርት “ለመሸከም የሚያስቸግር ከባድ ውርስ” ብሎ ከጠራውና “ያሻትን የምታደርገው ቤተ ክርስቲያን ከመካከለኛው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ ስትከራከርለትና ወላጆች ልጆቻቸውን በተቻለ ፍጥነት እንዲያስጠምቁ ለማስፈራራት በሰፊው ስትጠቀምበት ከነበረው ከሊምቦ ትምህርት” ነፃ እንድትሆን አድርጓታል። ይሁንና በሊምቦ ትምህርት ላይ የተደረገው ለውጥ ሌሎች ጥያቄዎችን አስነስቷል።

ወግ ወይስ የአምላክ ቃል? የሊምቦ ትምህርት የተጀመረው በ12ኛው መቶ ዘመን በሃይማኖታዊ አስተማሪዎች መካከል ስለ መንጽሔ ክርክር በተነሳበት ወቅት ነው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች ብላ ታስተምራለች፤ በመሆኑም ሳይጠመቁ በመሞታቸው ምክንያት ወደ ሰማይ የማይሄዱ ሆኖም ገሃነም የማይገባቸው ልጆች ነፍሳቸው የምትሄድበት አንድ ቦታ መኖር አለበት የሚል ሐሳብ መጣ። የሊምቦ ትምህርት የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ መኖሯን ትቀጥላለች ብሎ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ኃጢአት የሠራች የሰው ነፍስ ዘላለማዊ ሳትሆን ‘እንደምትጠፋ’ ወይም ‘እንደምትሞት’ በግልጽ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 3:23 አዲሱ መደበኛ ትርጉም፤ ሕዝቅኤል 18:4) ነፍስ ሟች ስለሆነች ሊምቦ የሚባል ቦታ ሊኖር አይችልም። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በአካባቢያችን የሚከናወነውን ነገር ከማናውቅበት ከእንቅልፍ ጋር ያመሳስለዋል።—መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 11:11-14

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ልጆችን በክርስቲያን ወላጆቻቸው ምክንያት ቅዱስ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:14) ሕፃናት ለመዳን መጠመቃቸው የግድ አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ ይህ ጥቅስ ትርጉም አይኖረውም ነበር።

የሊምቦ ትምህርት አምላክን እንደ ፍትሐዊና አፍቃሪ አባት ሳይሆን ንጹሐንን እንደሚቀጣ ጨካኝ የሆነ አምባገነን አድርጎ ስለሚገልጸው ይህን ትምህርት ማስተማር እሱን ከመሳደብ ተለይቶ አይታይም። (ዘዳግም 32:4፤ ማቴዎስ 5:45፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር የሚጋጨው ይህ ትምህርት ቅን ለሆኑ ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን ምክንያታዊ ሆኖ የማይታያቸው ለዚህ ነው።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአምላክ ቃል በሚናገረው መሠረት የምንኖር ከሆነ ከአምላክ ጋርም ሆነ ከሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ይኖረናል