በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አለ?

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አለ?

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አለ?

ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ ብርሃን በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጥርት ያለውን ሰማይ ስንመለከት በሺዎች የሚቆጠሩ ከዋክብት በጥቁር ከፋይ ጨርቅ ላይ የተረጩ ጥቃቅን የአልማዝ ፈርጦች መስለው ይታያሉ። የሰው ልጅ ከዋክብት ምን ያህል ግዙፍ እንደሆኑና በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኙ ማወቅ የጀመረው ከዛሬ 350 ዓመታት ወዲህ ነው። አስደናቂ የሆነውን አጽናፈ ዓለማችንን ስለሚያንቀሳቅሱት እጅግ ታላላቅ ኃይላት መረዳት የጀመርነው ገና አሁን ነው ማለት ይቻላል።

የሰው ልጅ፣ የጠፈር አካላት በምሽት ሰማይ ላይ ዝንፍ የማይል እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉና በየወቅቱ ቦታ እንደሚቀያይሩ ያስተዋለው ከጥንት ጀምሮ ነው። (ዘፍጥረት 1:14) የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ከ3,000 ዓመታት በፊት “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?” በማለት ጽፎ ነበር፤ ዛሬም ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት አላቸው።—መዝሙር 8:3, 4

ይሁን እንጂ ተገነዘብነውም አልተገነዘብነው የጠፈር አካላትና እነሱ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተጨባጭ በሆኑ በርካታ መንገዶች በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የሰው ልጅ ጊዜን ለመቁጠር የሚጠቀምባቸው መሠረታዊ መለኪያዎች ማለትም የቀንና የዓመት ርዝመት የተመካው ምድራችን በምትዞራትና በቅርባችን በምትገኘው ኮከብ ይኸውም በፀሐይ ላይ ነው። ጨረቃ ‘ወቅቶችን ለመለየት’ ወይም “የወሮች መለኪያ” ሆና ታገለግላለች። (መዝሙር 104:19 የ1980 ትርጉም) የባሕር ተጓዦች አቅጣጫቸውን ለማወቅ አልፎ ተርፎም ጠፈርተኞች የመንኮራኩራቸውን አቅጣጫ ለማስተካከል አስተማማኝ መሠረት የሚያደርጉት ከዋክብትን ነው። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች ከዋክብት ጊዜንና ወቅትን ከማሳወቅ እንዲሁም ለአምላክ የእጅ ሥራዎች ያለንን አድናቆት ከማሳደግ በተጨማሪ የሚያደርጉልን ነገር ይኖር ይሆን? ብለው ይጠይቃሉ። የወደፊት ዕጣችንን ሊያሳውቁን ወይም ከሚመጣብን ጥፋት ሊያስጠነቅቁን ይችላሉ?

የኮከብ ቆጠራ አመጣጥና ዓላማ

ሰዎች በምድር ላይ ለሚከናወኑ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች ከሰማይ አካላት መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የጀመሩት በጥንቷ መስጴጦምያ ምናልባትም በሦስተኛው ሺህ ዓመት ዓ.ዓ. ሳይሆን አይቀርም። የጥንቶቹ ኮከብ ቆጣሪዎች የጠፈር አካላትን በጥንቃቄ ይከታተሉ ነበር። የሰማይ አካላት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴና የከዋክብትን አቀማመጥ ንድፍ ለማውጣት እንዲሁም የቀን መቁጠሪያ ለማዘጋጀት ብሎም ግርዶሽ የሚከሰትበትን ጊዜ ለመተንበይ ባደረጉት ጥረት የከዋክብት ጥናት ወይም የአስትሮኖሚ ሳይንስ ተወለደ። ይሁን እንጂ ኮከብ ቆጠራ ወይም አስትሮሎጂ ፀሐይና ጨረቃ በአካባቢያችን ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ በመከታተል ላይ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ከዚህ ይልቅ ኮከብ ቆጣሪዎች የፀሐይ፣ የጨረቃ፣ የፕላኔቶች፣ የከዋክብት እንዲሁም የኅብረ ከዋክብት አቀማመጥና ቦታ በዋና ዋና የምድር ክንውኖች ላይ ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ሕይወት ላይም ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያምናሉ። እንዴት?

አንዳንድ ሰዎች፣ ኮከብ ቆጠራን ስለወደፊቱ ጊዜ ምልክት ወይም ማስጠንቀቂያ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ሲሆን ያገኙትን ምልክት በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ኮከብ ቆጠራ እኛ ምን እንደምናደርግ አስቀድሞ የተወሰነልንን ወይም አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ወይም ተግባሮችን መቼ ብንጀምር ስኬታማ እንደምንሆን ለማወቅ እንደሚያስችል ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው መረጃ የሚገኘው ቁልፍ የሆኑ የጠፈር አካላትን አቀማመጥ በመመልከትና እነዚህ አካላት እርስ በርሳቸውና ከምድር ጋር ያላቸውን መስተጋብር “በማስላት” እንደሆነ ይነገራል። በአንድ ግለሰብ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የሚወሰነው ግለሰቡ በተወለደበት ጊዜ በሚኖረው የጠፈር አካላት አቀማመጥ እንደሆነ ይታመናል።

የጥንቶቹ ኮከብ ቆጣሪዎች ምድር የአጽናፈ ዓለሙ እምብርት ወይም ማዕከል እንደሆነችና ፕላኔቶችና ከዋክብት በምድር ዙሪያ በሚሽከረከሩና እየሰፉ በሚሄዱ ክብ ነገሮች ውስጥ የታጠሩ ናቸው ብለው ያስቡ ነበር። በተጨማሪም ፀሐይ በሰማይ ውስጥ አንድን መስመር ተከትላ ከዋክብትንና ኅብረ ከዋክብትን በማቋረጥ ዓመታዊ ጉዞ ታደርጋለች የሚል እምነት ነበራቸው። ፀሐይ ትጓዝበታለች ብለው የሚያስቡትን መስመር ኤክሊፕቲክ ብለው የሰየሙት ሲሆን ይህን መስመር በ12 ዞን ወይም ምድብ ከፋፈሉት። እያንዳንዱ ምድብ ፀሐይ አቋርጣ በምታልፈው ኅብረ ከዋክብት ስም ተሰይሟል። የዞዲያክ 12 ምልክቶች የተገኙት በዚህ መንገድ ነው። እነዚህ ዞኖች ወይም “የሰማይ ቤቶች” የአማልክት መኖሪያዎች እንደሆኑ ይታመን ነበር። እርግጥ ነው፣ ውሎ አድሮ ሳይንቲስቶች ፀሐይ በምድር ዙሪያ እንደማትዞር ከዚህ ይልቅ ምድር በፀሐይ ዙሪያ እንደምትዞር አውቀዋል። ይህ ግኝት ኮከብ ቆጠራ እንደ ሳይንስ መታየቱን እንዲያከትም አድርጓል።

ኮከብ ቆጠራ ከተወለደበት ከመስጴጦምያ ተነስቶ ወደ አብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች የተስፋፋ ሲሆን በዚያም ዓይነቱን እየለዋወጠ ከፍተኛ ሥልጣኔ በነበራቸው ሕዝቦች ውስጥ ሥር መስደድ ጀመረ። ፋርሳውያን ባቢሎንን ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ኮከብ ቆጠራ ወደ ግብፅ፣ ግሪክና ሕንድ ተስፋፋ። ከሕንድ ደግሞ የቡድሂስት ሚስዮናውያን ወደ ማዕከላዊ እስያ፣ ቻይና፣ ቲቤት፣ ጃፓንና ደቡብ ምሥራቅ እስያ አሰራጩት። ወደ ማያ የደረሰበትን መንገድ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በዚያ የሚገኘው ሕዝብ ከባቢሎናውያን ጋር የሚመሳሰል የኮከብ ቆጠራ ዓይነት በስፋት ይጠቀም ነበር። “ዘመናዊው” ኮከብ ቆጠራ የዳበረው የግሪክ ባሕል ከፍተኛ ተጽዕኖ ባሳደረባት በግብፅ ሲሆን በአይሁድ እምነት፣ በእስልምናና በሕዝበ ክርስትና አመለካከት ላይ ጉልህ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል።

እስራኤላውያን በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ወደ ባቢሎን ከመጋዛቸው በፊት የነበረው ብሔርም እንኳ ኮከብ ቆጠራ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ነፃ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ ታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ “ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት” መሥዋዕት የማቅረብን ልማድ ለማስወገድ ስላደረገው ጥረት ይናገራል።—2 ነገሥት 23:5

የኮከብ ቆጠራ ምንጭ

ኮከብ ቆጠራ፣ ሰዎች ስለ አጽናፈ ዓለም እንቅስቃሴና ቅርጽ ባላቸው እጅግ የተሳሳተ አመለካከት ላይ የተመሠረተ ነው። ስለሆነም ምንጩ አምላክ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የኮከብ ቆጠራ መነሻ ሐሳብ እርግጠኛ ባልሆነ አመለካከት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ስለወደፊቱ ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጠን አይችልም። ውድቅ መሆኑን የሚያሳዩ ትኩረት የሚስቡ ሁለት ታሪካዊ ክንውኖችን እንመልከት።

በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት ጠንቋዮችም ሆኑ ኮከብ ቆጣሪዎች ንጉሡ ያለመውን ሕልም መተርጎም አልቻሉም ነበር። የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ነቢይ የነበረው ዳንኤል ችግሩ ምን እንደነበር ሲናገር እንደሚከተለው ብሏል፦ “አንተ የጠየቅኸውን ምስጢር ጠቢባንም ሆኑ አስማተኞች፤ ጠንቋዮችም ሆኑ ኮከብ ቈጣሪዎች ሊነግሩህ አይችሉም። ነገር ግን ምስጢርን ሁሉ የሚገልጥ አንድ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለአንተ ገልጦልሃል።” (ዳንኤል 2:27, 28 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ ዳንኤል ስለወደፊቱ ጊዜ መረጃ ለማግኘት የፈለገው ‘ምስጢርን ሁሉ ከሚገልጥ’ ከይሖዋ አምላክ እንጂ ከፀሐይ፣ ከጨረቃ ወይም ከከዋክብት አልነበረም፤ ደግሞም ለንጉሡ ትክክለኛውን ትርጉም አስታውቆታል።—ዳንኤል 2:36-45

ፈጽሞ ዝንፍ የማይለው የማያዎች የኮከብ ቆጠራ ስሌት ሥልጣኔያቸውን በዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ከመንኮታኮት አላዳነውም። ኮከብ ቆጠራ ውድቅ መሆኑን የሚያሳዩት እነዚህ ታሪኮች፣ በእርግጥም ውሸት እንደሆነና ምንም ነገር በትክክል ሊተነብይ እንደማይችል የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በላይ እውነተኛ ዓላማው ምን እንደሆነ ያጋልጣሉ፤ ዓላማው ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ወደ አምላክ ዞር እንዳይሉ ማድረግ ነው።

ኮከብ ቆጠራ ትክክለኛ በሆነ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን ማወቃችን ምንጩ ማን እንደሆነ ለይተን ለማወቅም ይረዳናል። ኢየሱስ ስለ ዲያብሎስ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል።” (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን “የብርሃን መልአክ” መስሎ ይቀርባል፤ አጋንንቱ ደግሞ “የጽድቅ አገልጋዮች” ለመምሰል ይሞክራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን ሰዎችን በማታለያ መረባቸው ለማጥመድ የተነሱ አታላዮች ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15) ‘ተአምራት፣ ሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች የሰይጣን አሠራር’ እንደሆኑ የአምላክ ቃል ይናገራል።—2 ተሰሎንቄ 2:9

መራቅ የሚገባህ ለምንድን ነው?

ኮከብ ቆጠራ በሐሰት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የእውነት አምላክ በሆነው በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነው። (መዝሙር 31:5) በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ኮከብ ቆጠራን በግልጽ የሚያወግዝ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ከዚህ ተግባር ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖራቸው ያስጠነቅቃል። በ⁠ዘዳግም 18:10-12 ላይ አምላክ በግልጽ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “ሞራ ገ[ላ]ጭ፣ ጠንቋይ . . . መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።”

ከኮከብ ቆጠራ በስተጀርባ ያሉት ሰይጣንና አጋንንቱ በመሆናቸው ከዚህ ድርጊት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ መፍጠር ለሰይጣንና ለአጋንንቱ ጥቃት ያጋልጣል። አንድ ሰው አደንዛዥ ዕፆችን ለሙከራ ያህል እንኳ መውሰዱ በዕፅ አዘዋዋሪዎች እጅ እንዲወድቅ ሊያደርገው እንደሚችል ሁሉ አንድ ሰው ለሙከራ ብሎ አንዳንድ የኮከብ ቆጠራ ድርጊቶችን ቢፈጽም ቀንደኛ አታላይ በሆነው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንዲወድቅ ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም አምላክንና እውነትን የሚወዱ ሁሉ ከኮከብ ቆጠራ ሙሉ በሙሉ መራቅና “ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል ይኖርባቸዋል።—አሞጽ 5:15

ኮከብ ቆጠራ ሊስፋፋ የቻለው ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ፍላጎት ስላላቸው ነው። ታዲያ ስለወደፊቱ ጊዜ ማወቅ ይቻላል? የሚቻል ከሆነስ እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ ነገ፣ በሚቀጥለው ወር ወይም በሚቀጥለው ዓመት በግለሰብ ደረጃ ምን እንደሚደርስብን ማወቅ እንደማንችል ይናገራል። (ያዕቆብ 4:14) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መላው የሰው ዘር በቅርቡ ምን እንደሚያጋጥመው ጠቅለል ያለ መግለጫ ይሰጠናል። የአምላክ ቃል፣ መንግሥትህ ይምጣ ብለን የምንጸልይለት መንግሥት በቅርቡ እንደሚመጣ ይነግረናል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) በተጨማሪም በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰው መከራ በቅርቡ እንደሚያበቃና ወደፊት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዳግመኛ እንደማይከሰት ይናገራል። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:4) አምላክ የሰውን ዕድል ከመወሰን ይልቅ በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ስለ እሱና እሱ ስለሚያደርግላቸው ነገሮች እንዲያውቁ እየጋበዘ ነው። ይህን እንዴት ማወቅ እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እንደሆነ በግልጽ ይናገራል።—1 ጢሞቴዎስ 2:4

በጣም አስደናቂ የሆኑት ሰማያትና በውስጣቸው ያሉት ነገሮች በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ የተፈጠሩ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ስለ ይሖዋ ኃይልና አምላክነቱ የሚመሠክሩ ናቸው። (ሮም 1:20) እነዚህ ፍጥረታት ከሐሰት እንድንርቅና ለተሳካ ሕይወት የሚያስፈልገውን አስተማማኝ መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክና ቃሉ ወደሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ዞር እንድንል ሊያነሳሱን ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 3:5, 6

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የማያ ሕዝቦች በኮከብ ቆጠራ በስፋት ይጠቀሙ ነበር

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ፈጽሞ ዝንፍ የማይለው የማያዎች የኮከብ ቆጠራ ስሌት ሥልጣኔያቸውን ከመንኮታኮት አላዳነውም

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ምስጢርን ሁሉ የሚገልጥ አንድ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለአንተ ገልጦልሃል”

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤል ካራኮል የጠፈር አካላትን መመልከቻ፣ ቺቼን ኢትሳ፣ ዩካታን፣ ሜክሲኮ 750-900 ዓ.ም.

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Pages 18 and 19, left to right: Stars: NASA, ESA, and A. Nota (STScI); Mayan calendar: © Lynx/Iconotec com/age fotostock; Mayan astronomer: © Albert J. Copley/age fotostock; Mayan observatory: El Caracol (The Great Conch) (photo), Mayan/Chichen Itza, Yucatan, Mexico/Giraudon/The Bridgeman Art Library