የገለዓድ በለሳን—ፈዋሽ የሆነው ቅባት
የገለዓድ በለሳን—ፈዋሽ የሆነው ቅባት
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ዮሴፍ ወደ ግብፅ ይጓዙ ለነበሩ እስማኤላውያን ነጋዴዎች በገዛ ወንድሞቹ እንደተሸጠ የሚናገር አንድ የታወቀ ታሪክ አለ። ነጋዴዎቹ ከገለዓድ ተነስተው በግመሎቻቸው በለሳንና ሌሎች ሸቀጦችን በመጫን ወደ ግብፅ ይጓዙ ነበር። (ዘፍጥረት 37:25) ይህ አጭር ታሪክ ከገለዓድ ወይም ከጊልያድ የሚመጣው በለሳን በዚያን ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ እጅግ ተፈላጊ እንደነበረና ልዩ በሆነው የፈዋሽነት ባሕርይው ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠው እንደነበረ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኤርምያስ “በጊልያድ የበለሳን ቅባት የለም?” በማለት በሐዘን ጠይቆ ነበር። (ኤርምያስ 8:22 NW) ኤርምያስ እንዲህ ያለ ጥያቄ እንዲጠይቅ ያነሳሳው ምን ነበር? በለሳን ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜስ ፈዋሽ የሆነ በለሳን ይገኛል?
በለሳን—በጥንት ዘመን
በለሳን የሚለው ቃል ከተለያዩ እፅዋትና ቁጥቋጦዎች የሚገኙ ጥሩ መዓዛ ያላቸውን እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ዘይትነትና ሙጫነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ለማመልከት ያገለግላል። በጥንት ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ በአብዛኛው ለሰንደልና ለሽቶ መቀመሚያነት ያገለግል የነበረው የበለሳን ዘይት ከቅንጦት ዕቃዎች አንዱ ነበር። እስራኤላውያን ከግብፅ እንደወጡ ብዙም ሳይቆይ በመገናኛው ድንኳን ይጠቀሙበት የነበረውን ቅብዓ ቅዱሱንና ዕጣኑን ለመቀመም ያገለግሉ ከነበሩ ቅመሞች አንዱ እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፀአት 25:6፤ 35:8 NW) በተጨማሪም የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰለሞን ካመጣቻቸው ውድ ሥጦታዎች መካከል የበለሳን ዘይት ይገኝበት ነበር። (1 ነገሥት 10:2, 10 NW) አስቴር የፋርሳውያን ንጉሥ ወደነበረው ወደ ጠረክሲስ ከመቅረቧ በፊት ውበቷን ለመጠበቅ ‘ለስድስት ወር ያህል በባልሳም’ ወይም በበለሳን ዘይት ታሽታ ነበር።—አስቴር 1:1፤ 2:12 የ1980 ትርጉም
የበለሳን ዘይት ከተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ ክፍሎች ይመጣ የነበረ ቢሆንም የገለዓድ በለሳን ግን ከተስፋይቱ ምድር ይኸውም ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው የገለዓድ ምድር ይበቅል ነበር። ያዕቆብ በለሳንን “ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች” መካከል አንዱ እንደሆነ በመቁጠር በስጦታ ወደ ግብፅ ልኮ ነበር። (ዘፍጥረት 43:11) ነቢዩ ሕዝቅኤል ይሁዳና እስራኤል ወደ ጢሮስ ከሚልኳቸው ሸቀጦች መካከል በለሳንን ጠቅሷል። (ሕዝቅኤል 27:17) በለሳን በተለይ በፈዋሽነቱ የታወቀ ነበር። የጥንት ጽሑፎች የዚህን ቅባት ፈዋሽነትና መድኃኒትነት በተለይም ቁስል በማዳን ረገድ ያለውን ኃይል ብዙ ጊዜ ጠቅሰዋል።
ለታመመ ብሔር የሚሆን በለሳን
ታዲያ ኤርምያስ “በጊልያድ የበለሳን ቅባት የለም?” የሚል ጥያቄ ያነሳው ለምንድን ነው? ይህን ለመረዳት የእስራኤል ብሔር በዚያ ዘመን የነበረበትን ሁኔታ መመልከት ይኖርብናል። ቀደም ሲል ነቢዩ ኢሳይያስ ሕዝቡ የነበረበትን አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት በሥዕላዊ መንገድ ገልጾት ነበር፦ “ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጕራችሁ ጤና የላችሁም፤ ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም።” (ኢሳይያስ 1:6) ብሔሩ፣ ይገኝበት የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ ተገንዝቦ መድኃኒት ከመፈለግ ይልቅ የተሳሳተ አካሄድ መከተሉን ቀጥሎ ነበር። በዚህ ጊዜ ኤርምያስ “የእግዚአብሔርን ቃል ተቃውመው፣ ምን ዐይነት ጥበብ ይኖራቸዋል?” ብሎ በምሬት ከመናገር ሌላ ሊያደርግ የሚችለው ነገር አልነበረም። ይሖዋ ሊፈውሳቸው የሚችለው ወደ እሱ ከተመለሱ ብቻ ነው። “በጊልያድ የበለሳን ቅባት የለም?” የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚስብ ነው።—ኤርምያስ 8:9
ዛሬ የምንገኝበት ዓለም በብዙ መንገዶች “ቍስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ” ወርሶታል። ሰዎች በድህነትና በፍትሕ መጓደል እየተሠቃዩ ከመሆኑም በላይ ራስ ወዳድነትና ጭካኔ ነግሷል፤ ይህ ሁሉ የመጣው ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር በመቀዝቀዙ ነው። (ማቴዎስ 24:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ብዙ ሰዎች በዘር፣ በጎሣ ወይም በዕድሜ ምክንያት ይገለላሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ረሃብ፣ በሽታ፣ ጦርነትና ሞት በሥቃያቸው ላይ ሌላ ሥቃይ እየጨመረባቸው ነው። ቅን ልብ ያላቸው አምላክን የሚያመልኩ ብዙ ሰዎች ልክ እንደ ኤርምያስ በመከራ የሚሠቃዩ ሰዎች የሚደርስባቸውን ስሜታዊና መንፈሳዊ ቁስል ሊያስር ወይም ሊጠግን የሚችል ‘የጊልያድ የበለሳን ቅባት’ መኖሩን ይጠይቃሉ።
ፈዋሽ የሆነው የምሥራች
በኢየሱስ ዘመንም ቢሆን ትሑት የሆኑ ሰዎች ተመሳሳይ ጥያቄ በአእምሯቸው ይጉላላ ነበር። ጥያቄያቸው ግን መልስ ሳያገኝ አልቀረም። በ30 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ በናዝሬት አንድ ምኩራብ ውስጥ ገብቶ ከኢሳይያስ ጥቅልል ላይ “ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛል። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን . . . ልኮኛል” የሚለውን ሐሳብ አንብቦ ነበር። (ኢሳይያስ 61:1) ከዚያም ኢየሱስ ራሱን የመጽናኛ መልእክት የማድረስ ተልዕኮ የተሰጠው መሲሕ እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ እነዚህ ቃላት በእሱ ላይ ተፈጻሚነታቸውን እንዳገኙ አመልክቷል።—ሉቃስ 4:16-21
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በቅንዓት ሰብኳል። (ማቴዎስ 4:17) በተራራ ስብከቱ ላይ ለተጨቆኑ ሰዎች “አሁን የምታለቅሱ ደስተኞች ናችሁ፤ ምክንያቱም ኋላ ትስቃላችሁ” በማለት ሁኔታቸው እንደሚለወጥ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 6:21) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣ የሚናገረውን የተስፋ መልእክት በመስበክ ‘የተሰበሩትን ጠግኗል።’
በዚህ ዘመንም ቢሆን ሰዎች ‘በመንግሥቱ ምሥራች’ እየተጽናኑ ነው። (ማቴዎስ 6:10፤ 9:35) የሮዤንና የሊልያንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አምላክ ስለሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቁት በጥር 1961 ነበር፤ ይህ ተስፋ ለእነሱ እንደ ማስታገሻ ዘይት ሆኖላቸው ነበር። ሊልያን “የተማርኩትን ነገር ሳስበው ከመደሰቴ የተነሳ ወጥ ቤት ውስጥ እየዞርኩ መደነስ ጀመርኩ” ብላለች። በዚያን ጊዜ የአካል ጉዳት ከደረሰበት አሥር ዓመት ሆኖት የነበረው ሮዤም እንዲህ ብሏል፦ “አስደናቂ ስለሆነው ስለ ትንሣኤ ተስፋ ማወቄ እንዲሁም ሥቃይና ሕመም በሙሉ እንደሚቀር መረዳቴ ትልቅ ደስታ አስገኝቶልኛል፤ በሕይወት በመኖሬም በጣም ተደስቻለሁ።”—ራእይ 21:4
ሮዤና ሊልያን በ1970 የ11 ዓመት ልጃቸውን በሞት አጡ። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ በሐዘን አልተደቆሱም። ይሖዋ ‘ልባቸው የተሰበረውን የሚፈውስና ቍስላቸውን የሚጠግን’ አምላክ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። (መዝሙር 147:3) ያላቸው ተስፋ አጽናንቷቸዋል። አሁን ወደ 50 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም የሚመጣው የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሰላምና እርካታ አስገኝቶላቸዋል።
ወደፊት የሚመጣ ፈውስ
በዛሬው ጊዜስ “በጊልያድ የበለሳን ቅባት” ይገኛል? አዎን፣ በዛሬው ጊዜም መንፈሳዊ በለሳን አለ። ከአምላክ መንግሥት ምሥራች የሚገኘው ማጽናኛና ተስፋ የተሰበሩ ልቦችን መጠገን ይችላል። እንዲህ ያለውን ፈውስ ማግኘት ትፈልጋለህ? ከአንተ የሚፈለገው፣ ከአምላክ ቃል ለሚገኘው አጽናኝ መልእክት ልብህን መክፈትና መላ ሕይወትህን እንዲለውጠው መፍቀድ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን አድርገዋል።
ከዚህ በለሳን የሚገኘው ፈውስ ገና ወደፊት ለሚመጣ ታላቅ ፈውስ መቅድም ሆኗል። ይሖዋ አምላክ ‘ብሔራትን የሚፈውስበት’ ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። ሰዎች የዘላለም ሕይወት በሚያገኙበት በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” ዛሬም ቢሆን “በጊልያድ የበለሳን ቅባት” አለ።—ራእይ 22:2፤ ኢሳይያስ 33:24
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመፈወስ ኃይል ያለው የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዛሬው ጊዜም ልባቸው የተሰበረ ሰዎችን እየጠገነ ነው