በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው የከተማ በር ምንድን ነው?

በጥንት ጊዜ አብዛኞቹ ከተሞች በግንብ የታጠሩ ነበሩ። በቅጥሮቹ በሮች አካባቢ ሰዎች እርስ በርስ የሚገናኙባቸው፣ የሚገበያዩባቸውና መልእክት የሚለዋወጡባቸው አደባባዮች ነበሩ። በእነዚህ ቦታዎች ማስታወቂያዎች ይነገሩ ነበር፤ ነቢያትም መልእክቶቻቸውን የሚናገሩት በእነዚህ ቦታዎች ሳይሆን አይቀርም። (ኤርምያስ 17:19, 20) ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ የተባለው ጽሑፍ “ማንኛውም ዓይነት ውል የሚካሄደው በከተማይቱ በር ወይም አቅራቢያ ነበር ማለት ይቻላል” ሲል ተናግሯል። በጥንት እስራኤል የነበሩት የከተማይቱ በሮች በአሁኑ ጊዜ ኅብረተሰቡ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከሚያደርጉባቸው ማዕከሎች ጋር ይመሳሰላሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም “ወደ ከተማው በር በመጡት ኬጢያውያንም ሁሉ ፊት” ኤፍሮን ከተባለ ሰው ለቤተሰቡ የመቃብር ቦታ ገዝቷል። (ዘፍጥረት 23:7-18) ቦዔዝ የቤተልሔም ከተማ አሥር ሽማግሌዎች በከተማይቱ በር አደባባይ እንዲቀመጡ ካደረገ በኋላ እነሱ በተገኙበት አንዲት ሴት ባሏ ሲሞት ዘመዱ እንዲያገባት በሚያዘው ሕግ መሠረት ሩትንም ሆነ የባሏን ንብረት ለመቤዠት ዝግጅት አደረገ። (ሩት 4:1, 2) የከተማዋ ሽማግሌዎች በከተማዋ በር ላይ ለዳኝነት ተቀምጠው ጉዳዮችን ይመለከቱ፣ ውሳኔ ያስተላልፉና ፍርድ ያስፈጽሙ ነበር።—ዘዳግም 21:19

መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ምርጥ ወርቅ ይገኝበታል ብሎ የሚናገርለት ኦፊር የተባለው ቦታ የት ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የኦፊርን ወርቅ’ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢዮብ መጽሐፍ ላይ “ንጹሕ ወርቅ” በማለት ጠርቶታል። (ኢዮብ 28:15, 16) ኢዮብ ከኖረ ከ600 ዓመታት በኋላ ንጉሥ ዳዊት በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ ለመገንባት “የኦፊር ወርቅ” ሰብስቧል። ልጁ ሰለሞንም ከኦፊር ወርቅ አስመጥቶ ነበር።—1 ዜና መዋዕል 29:3, 4፤ 1 ነገሥት 9:28

ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚናገሩት ሰለሞን በቀይ ባሕር ላይ ባለችው በዔጽዮንጋብር ያሠራቸው መርከቦች የነበሩት ሲሆን በእነሱም ከኦፊር ወርቅ ያስመጣ ነበር። (1 ነገሥት 9:26) ምሑራን ዔጽዮንጋብር ትገኝ የነበረው በአቃባ ባሕረ ሰላጤ ጫፍ ላይ ወይም በዛሬው ጊዜ ኤላት አሊያም አቃባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነ ይናገራሉ። መርከቦች ከዚያ ተነስተው በቀይ ባሕር ላይ ወደሚገኙ የንግድ ቀጠናዎች ከዚያም አልፎ ኦፊር ሊገኝባቸው ወደሚችሉ የአፍሪካ ወይም የሕንድ የባሕር ዳርቻዎች መጓዝ ይችሉ ነበር። ሌሎች ደግሞ ኦፊር የሚገኘው ጥንታዊ የወርቅ ማዕድን ጉድጓዶች በተገኙበትና አሁንም ወርቅ በሚወጣበት በዓረብ ምድር እንደሆነ ያምናሉ።

አንዳንዶች የሰለሞን የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች አፈ ታሪክ እንደሆኑ ቢናገሩም ስለ ጥንታዊቷ ግብፅ ሥልጣኔ የሚያጠኑት ኬነዝ ኪቸን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ኦፊር አፈ ታሪክ አይደለም። በ8ኛው መቶ ዘመን [ዓ.ዓ.] እንደተጻፈ በሚገመት አንድ በዕብራይስጥ የተጻፈ የሸክላ ስብርባሪ ላይ ‘ለቤትሆሮን የኦፊር ወርቅ—30 ሰቅል’ የሚል አጭር ማስታወሻ ተቀርጾ ይገኛል። ኦፊር በግብፃውያን ጽሑፎች ላይ እንደሚገኙት ‘የአማው ወርቅ፣’ ‘የፑንት ወርቅ’ ወይም ‘የኩሽ ወርቅ’ ሁሉ ትክክለኛ የወርቅ መገኛ ቦታ ነው፤ በእያንዳንዳቸው ላይ የተገለጸው ወርቅ በስም ከተጠቀሰው ምድር የተገኘውን ወርቅ አሊያም የዚያን ምድር የወርቅ ዓይነት ወይም ጥራት ያመለክታል።”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም በከተማዋ በር አጠገብ ሆኖ መሬት ለመግዛት ሲዋዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኦፊር የሚል ስም የተቀረጸበት በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ የሸክላ ስብርባሪ

[ምንጭ]

Collection of Israel Antiquities Authority, Photo © The Israel Museum, Jerusalem