በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ በእርግጥ ሐቀኝነት ማጉደል ነው?

ይህ በእርግጥ ሐቀኝነት ማጉደል ነው?

ይህ በእርግጥ ሐቀኝነት ማጉደል ነው?

“ሪፖርት ስታደርግ ያደረስከውን አደጋ ትንሽ ለወጥ አድርገህ ካቀረብከው ሁሉ ነገር ይስተካከላል።”

“ግብር ሰብሳቢዎቹ ሁሉንም ነገር ማወቅ የለባቸውም።”

“ዋናው ነገር እንዳትያዝ መጠንቀቅ ነው።”

“በነፃ ማግኘት እየቻልክ ለምን ትከፍላለህ?”

በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ረገድ ምክር ብትጠይቅ እነዚህን የመሰሉ አስተያየቶችን ትሰማ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ለሁሉም ነገር “መፍትሔ” ያላቸው ይመስላሉ። እዚህ ላይ በእርግጥ እነዚህ መፍትሔዎች በሐቀኝነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው? የሚል ጥያቄ ይነሳል።

ሐቀኝነትን ማጉደል በዛሬው ጊዜ በጣም ከመስፋፋቱ የተነሳ ብዙውን ጊዜ ሰዎች መዋሸትን፣ ማጭበርበርንና መስረቅን የሚመለከቷቸው ከቅጣት ለማምለጥ፣ ገንዘብ ለማግኘት ወይም ራስን ለማሻሻል እንደሚረዱ ተቀባይነት ያላቸው ዘዴዎች አድርገው ነው። በኅብረተሰቡ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በሐቀኝነት ረገድ ጥሩ ምሳሌ አይሆኑም። በአንድ የአውሮፓ አገር ማጭበርበርና ሙስና ከ2005 እስከ 2006 ባለው ጊዜ ውስጥ 85 በመቶ ጨምሯል። ይህ አኃዝ አንዳንድ ሰዎች “ቀላል ነገር ነው” የሚሏቸውን በርካታ ትናንሽ የማጭበርበር ድርጊቶችን አይጨምርም። በዚያች አገር ያሉ ታዋቂ የንግድና የፖለቲካ ሰዎች የሥራ እድገት ለማግኘት ሲሉ የሐሰት ዲፕሎማዎችን በመጠቀም አሳፋሪ ተግባር መፈጸማቸው የሚገርም አይደለም።

በዓለም ላይ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት በጣም ቢስፋፋም እንኳ ብዙ ሰዎች ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ አንተ ልትሆን ትችላለህ። ምናልባት አምላክን ስለምትወድ በፊቱ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ትፈልግ ይሆናል። (1 ዮሐንስ 5:3) “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር ስለምንመኝ ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን” በማለት እንደጻፈው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ሊኖርህ ይችላል። (ዕብራውያን 13:18) ስለዚህ አንድ ሰው “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ያለውን ፍላጎት ሊፈትኑ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። በተጨማሪም እንደ እነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሊረዱን የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመለከታለን።

ላደረስከው አደጋ መክፈል ያለበት ማን ነው?

ሊሳ * የተባለች አንዲት ወጣት አንድ ቀን መኪና ስታሽከረክር ስህተት በመሥራቷ ከአንድ ሌላ መኪና ጋር ተጋጨች። የተጎዳ ሰው ባይኖርም ሁለቱም መኪናዎች ጉዳት ደረሰባቸው። ሊሳ በምትኖርበት አገር ወጣቶች ለመኪና የሚከፍሉት ኢንሹራንስ ብዙ ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ አደጋ ባደረሰ ቁጥር ይህ ክፍያ እየጨመረ ይሄዳል። በመሆኑም አንድ ጓደኛዋ፣ በአደጋው ወቅት ከሊሳ በዕድሜ የሚበልጠው ግሬጎር የተባለው ዘመዷ ከእሷ ጋር ስለነበር መኪናውን ሲነዳ የነበረው ግሬጎር ነው ብለው ሪፖርት እንዲያደርጉ ሐሳብ አቀረበ። በዚህ መንገድ ሊሳ ለኢንሹራንስ ብዙ ከመክፈል ልትድን ትችላለች። ይህ መፍትሔ በጣም ጥሩ ሐሳብ ይመስላል። ታዲያ ሊሳ ምን ታደርግ ይሆን?

የኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ ደንበኞቻቸው የሚከፍሉትን ክፍያ ለሚገባቸው ሰዎች ኢንሹራንስ ለመክፈል ይጠቀሙበታል። ስለዚህ ሊሳ የጓደኛዋን ምክር ሰምታ ያላትን ብታደርግ እሷ ላደረሰችው አደጋ ሌሎች የድርጅቱ ደንበኞች ከፍተኛ ክፍያ እንዲፈጽሙ ታደርጋለች ማለት ነው። እንዲህ በማድረጓ የሐሰት ሪፖርት እያቀረበች ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች እየሰረቀች ነው ማለት ይቻላል። ከፍተኛ የኢንሹራንስ ክፍያ ለማግኘት ብሎ መዋሸትም ቢሆን ተመሳሳይ ነው።

ሕጋዊ ቅጣቶች እንዲህ ዓይነቱን ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ለመከላከል ዓይነተኛ መንገዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር ከመፈጸም እንድንርቅ የሚያደርገን ዋነኛው ምክንያት በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኛል። ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱ “አትስረቅ” ይላል። (ዘፀአት 20:15) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ትእዛዝ “የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ” በማለት ለክርስቲያኖች በድጋሚ ነግሯቸዋል። (ኤፌሶን 4:28) እንዲህ ባሉ የኢንሹራንስ ጉዳዮች ረገድ የአምላክን ቃል ተግባራዊ በማድረግ አምላክ የሚያወግዘውን ነገር ከመፈጸም ትቆጠባለህ። በተጨማሪም ለአምላክ ሕግ ብሎም ለሰዎች ፍቅርና አክብሮት እንዳለህ ታሳያለህ።—መዝሙር 119:97

“የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር”

ፒተር ነጋዴ ነው። ፒተር ውድ የኮምፒውተር መሣሪያ “ገዝቻለሁ” ብሎ የግብር ቅናሽ እንዲጠይቅ የሒሳብ ሠራተኛው ሐሳብ ያቀርብለታል። እንደ ፒተር ላለ ነጋዴ እንዲህ ያለ ዕቃ መግዛት የተለመደ ነገር ነው። ፒተር እንዲህ ዓይነቱን ግዢ ባይፈጽምም እንኳ በአብዛኛው መንግሥት መግዛቱንና አለመግዛቱን አያጣራም። በዚህ መንገድ የሚያስቀንሰው ገንዘብ ፒተር የሚከፍለው ግብር በእጅጉ እንዲቀንስለት ያደርጋል። ታዲያ ፒተር ምን ያደርግ ይሆን? ውሳኔ ለማድረግ የትኛው መመሪያ ይረዳው ይሆን?

ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ . . . ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ፣ ግብር ለሚጠይቅ ግብር ስጡ” ብሏቸዋል። (ሮም 13:1, 7) የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ባለሥልጣናት የሚጠይቁትን ግብር በሙሉ ይከፍላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የአገሩ ሕግ ለአንዳንድ ግለሰቦች ወይም የንግድ ዓይነቶች የግብር ቅናሽ የሚፈቅድ ከሆነና አንድ ሰው ሕጉ የሚጠይቀውን መሥፈርት አሟልቶ እንዲህ ዓይነቱን ቅናሽ ለማግኘት መጠየቁ ምንም ስህተት የለውም።

ግብር መክፈልን የሚጠይቅ ሌላ ሁኔታ ደግሞ የሚከተለው ነው። ዴቪድ የአንድ ድርጅት ባለቤት ነው። ይሁንና ጓደኞቹ ለሚሸጠው ነገር ሁለት ዓይነት ደረሰኝ እንዲያዘጋጅ ያበረታቱታል። በአንደኛው ደረሰኝ ላይ ትክክለኛውን ዋጋ ሲጽፍ በሌላኛው ደረሰኝ ላይ ግን ዋጋውን አሳንሶ ይጽፋል። ይህን የሚያደርገው ከፍተኛ ግብር እንዳይጠየቅ ነው። ግብር እንዲከፍል ሲጠየቅ የሚያሳየው አነስተኛ ዋጋዎችን የያዘውን ደረሰኝ ነው። ዴቪድ አምላክን ማስደሰት ስለሚፈልግ ሌላ ደረሰኝ የመሥራቱን ጉዳይ እንዴት ሊመለከተው ይገባል?

እንዲህ ያለ አድራጎት የሚፈጽም ሰው ባይያዝም እንኳ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር እየከፈለ አይደለም። ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” በማለት አዟል። (ማቴዎስ 22:17-21) ኢየሱስ ይህን የተናገረው አድማጮቹ ግብር ስለ መክፈል የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማረም ስለፈለገ ነበር። ኢየሱስ ቄሳር ብሎ የጠራቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ግብርን መቀበል ሕጋዊ መብታቸው እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። በመሆኑም የክርስቶስ ተከታዮች የሚጠየቁትን ግብር በሙሉ መክፈል ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታቸው እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ፈተና ላይ መኮረጅ

ማርታ የምትባል አንዲት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የመጨረሻ ፈተናዋን ለመውሰድ እየተዘጋጀች ነው። ጥሩ ሥራ የማግኘት አጋጣሚዋ የተመካው ከፍተኛ ውጤት በማግኘቷ ላይ ስለሆነ ለብዙ ሰዓታት ስታጠና ቆይታለች። እሷ ክፍል የሚማሩ አንዳንድ ልጆችም ለፈተናው ተዘጋጅተዋል፤ እነሱ ግን የተዘጋጁት በተለየ መንገድ ነበር። ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ሲሉ ፔጀሮችን፣ ቀደም ብሎ ፕሮግራም የተደረገላቸውን የስሌት ማሽኖችንና ሞባይል ስልኮችን ተጠቅመው ሊኮርጁ ነው። ታዲያ ማርታ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ብላ “ሁሉም ሰው” የሚያደርገውን ማድረግ ይኖርባታል?

ፈተና ላይ መኮረጅ በጣም የተለመደ በመሆኑ ብዙ ሰዎች እንዲህ ማድረግ ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማቸዋል። “ዋናው ነገር እንዳትያዝ መጠንቀቅ ነው” ብለው ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ምንም እንኳ አስተማሪው የሚኮርጁትን ተማሪዎች ባያያቸውም የሚመለከታቸው ሌላ አካል ግን አለ። ይሖዋ አምላክ ምን እያደረግን እንዳለን የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ በምናደርገው ተግባር በእሱ ፊት ተጠያቂዎች ነን። ጳውሎስ “ከእሱ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 4:13) ትክክለኛውን ነገር ስናደርግ ማየት የሚያስደስተው አምላክ እኛን እንደሚመለከተን ማወቃችን ለፈተና ስንቀመጥ ሐቀኞች እንድንሆን የሚያነሳሳን ጠንካራ ምክንያት አይደለም?

አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

ሊሳ፣ ግሬጎር፣ ፒተር፣ ዴቪድና ማርታ የገጠማቸውን ሁኔታ አሳሳቢነት ተገንዝበዋል። በሐቀኝነት ለመመላለስ ውሳኔ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ንጹሕ ሕሊና ለመያዝ እንዲሁም ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ ችለዋል። አንተስ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?

የሥራ ባልደረቦችህ፣ የክፍልህ ተማሪዎችና ጎረቤቶችህ መዋሸት፣ ማጭበርበር ወይም መስረቅ ምንም ላይመስላቸው ይችላል። እንዲያውም በአንተ ላይ በማሾፍ ልክ እንደነሱ እንድታደርግ ለማስገደድ ይጥሩ ይሆናል። ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንድትፈጽም ግፊት ቢደረግብህም ትክክለኛውን ውሳኔ እንድታደርግ ምን ሊረዳህ ይችላል?

ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም የአምላክን ሞገስ እንደሚያስገኝልን አስታውስ። ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ኰረብታህስ ማን መኖር ይችላል? አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር፤ . . . እነዚህን የሚያደርግ፣ ከቶ አይናወጥም” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 15:1-5) ንጹሕ ሕሊና መያዝ እንዲሁም በሰማይ ያለው አምላክ ወዳጅ መሆን ሐቀኝነት በጎደለው መንገድ ከሚገኝ ከማንኛውም ቁሳዊ ጥቅም እጅግ የላቀ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ።”

ለአምላክ ሕግ ያለን አክብሮትና ለሰዎች ያለን ፍቅር በኢንሹራንስ ጉዳዮች ረገድ ሐቀኞች እንድንሆን ይገፋፋናል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ . . . ስጡ።”

የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ስለምንፈልግ መንግሥት የሚጠይቅብንን ግብር በሙሉ እንከፍላለን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።”

ምንም እንኳ አስተማሪዎች ስንኮርጅ ባያዩንም በአምላክ ፊት ሐቀኞች ሆነን መገኘት እንፈልጋለን

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“የማይታይ” ስርቆት

ጓደኛህ በቅርብ የወጣ አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራም የገዛ ሲሆን አንተም ፕሮግራሙን ትፈልገዋለህ። ጓደኛህ ገንዘብ ከምታወጣ ፕሮግራሙን ቀድቶ እንደሚሰጥህ ይነግርሃል። ይህ ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር ነው?

ኮምፒውተር ተጠቃሚዎች የኮምፒውተር ፕሮግራም በሚገዙበት ጊዜ በገዙት ፕሮግራም የፈቃድ ስምምነት (ላይሰንስ አግሪመንት) ላይ የተዘረዘሩ ደንቦችን ለማክበር ይስማማሉ። ይህ የፈቃድ ስምምነት ገዥው ፕሮግራሙን በአንድ ኮምፒውተር ላይ ብቻ እንዲጭንና በዚያ ላይ እንዲጠቀም ይጠይቅበታል። በዚህ ረገድ ፕሮግራሙን ለሌላ ሰው አባዝቶ መስጠት ስምምነቱን መጣስ ከመሆኑም ሌላ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ነው። (ሮም 13:4) እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ስርቆትም ነው፤ ምክንያቱም ቅጂ የማዘጋጀት ሕጋዊ መብት ያለው አካል መብቱን ማለትም ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ ስለሚነፍገው ነው።—ኤፌሶን 4:28

አንዳንዶች ‘ማንም ሊያውቅ አይችልም’ ይሉ ይሆናል። ይህ እውነት ሊሆን ቢችልም ኢየሱስ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 7:12) ሁላችንም ብንሆን ለሠራነው ሥራ ተገቢውን ክፍያ ብናገኝ ደስ የሚለን ሲሆን ሌሎችም ንብረታችንን እንዲያከብሩልን እንፈልጋለን። ስለዚህ እኛም ለሌሎች እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል። የእኛ ያልሆነውን የሌሎችን የአእምሮ ንብረት * መውሰድን ከመሰለው “የማይታይ” ስርቆት እንቆጠባለን።—ዘፀአት 22:7-9

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.40 የአእምሮ ንብረት፣ በወረቀት ላይ የታተመም ሆነ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ውስጥ የተጫነን እንደ ሙዚቃ፣ መጻሕፍት ወይም የኮምፒውተር ፕሮግራም ያሉ የባለቤትነት መብት ያላቸውን ነገሮች ያጠቃልላል። የንግድ ምልክቶች፣ የፈጠራ ባለቤትነት፣ የንግድ ሚስጥርና ይፋ የማድረግ መብት ጭምር በዚህ ውስጥ የሚፈረጁ ናቸው።