አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
ሁሉም ሰው አምላክን ለማወቅና ለመውደድ እንዲችል እኩል አጋጣሚ ያገኛል?
ኢየሱስ ከሁሉም የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 22:37) ይሁን እንጂ ሰዎች አምላክን መውደድ እንዲችሉ ስለ እሱ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) ታዲያ ሁሉም ሰው ይህን እውቀት ለመቅሰም የሚያስችል እኩል አጋጣሚ ያገኛል?
ስለ አምላክ የሚገልጸው እውቀት በዋነኝነት የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ብዙዎች የሚኖሩት መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ማግኘት በሚቻልባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች በግል በሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንዲችሉ ተደጋጋሚ ግብዣ ይቀርብላቸው ይሆናል። (ማቴዎስ 28:19) አንዳንዶቹ ደግሞ በየዕለቱ ልጆቻቸውን ስለ አምላክ በሚያስተምሩ አፍቃሪ ክርስቲያን ወላጆች ያደጉ ናቸው።—ዘዳግም 6:6, 7፤ ኤፌሶን 6:4
ሌሎች ግን የሚኖሩት ለዚህ እምብዛም የሚመች ሁኔታ በሌለበት አካባቢ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች ያደጉት በልጆቻቸው ላይ በደል በሚፈጽሙና ተፈጥሯዊ ፍቅር በማያሳዩ ወላጆች ሥር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያደጉ ሰዎች አምላክን በሰማይ የሚኖር አፍቃሪ አባት አድርገው ለመመልከት ሊቸገሩ ይችላሉ። ብዙዎች በቂ ትምህርት ሳያገኙ ማደጋቸው መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ችሎታ እንዳይኖራቸው እንቅፋት ሆኗል። ሌሎች ደግሞ በሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች አእምሯቸው ታውሯል፤ አለዚያም የሚኖሩት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር በሚከለከልባቸው ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቦች ወይም አገሮች ውስጥ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች ያሉበት ሁኔታ ስለ አምላክ ለመማርና እሱን ለመውደድ የሚያስችል አጋጣሚ እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል?
ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ፈታኝ ሁኔታ አምላክን ለመውደድና ለመታዘዝ እንዲቸገሩ የሚያደርግ እንቅፋት ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ገልጿል። (ማቴዎስ 19:23, 24) ይሁን እንጂ ኢየሱስ አንዳንድ መሰናክሎች በሰዎች ዓይን ሲታዩ ሊወጧቸው የማይችሉ ቢመስሉም “በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስገንዝቧቸዋል።—ማቴዎስ 19:25, 26
የሚከተሉትን መረጃዎች ተመልከት፦ ይሖዋ አምላክ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ዘመን ከተሰራጩት መጻሕፍት ሁሉ እጅግ በላቀ መጠን እንዲሰራጭ አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ የሚገልጸው ምሥራች “በመላው ምድር” እንደሚሰበክ ተንብዮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ምሥራች ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች እየሰበኩ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን 500 በሚያህሉ ቋንቋዎች እያዘጋጁ በማቅረብ ላይ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ አጋጣሚ የሌላቸው ሰዎችም እንኳን አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች በመመልከት ስለ እሱ ብዙ ነገር መማር ይችላሉ።—ሮም 1:20
ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ . . . ከፈለግኸው ታገኘዋለህ” በማለት ይናገራል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) በመሆኑም ይሖዋ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የሚሰጠው አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት እንደሚሆን ቃል ባይገባም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ስለ እሱ ማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲዘረጋላቸው ያደርጋል። ስለ እሱ ለመማር ምንም ዓይነት አጋጣሚ ያላገኙ ሰዎች እንኳ ጽድቅ በሰፈነበት ዓለም ውስጥ ከሞት ተነስተው ስለ እሱ ለማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ያደርጋል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15