የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የሚነሱ አራት ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የሚነሱ አራት ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት ‘መጨረሻው እንደሚመጣ’ ትንቢት ተናግሯል። ኢየሱስ ስለዚህ ጊዜ ሲናገር “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:14, 21
ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን የተናገረው ሐሳብ እንዲሁም ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
1 ወደ ፍጻሜ የሚመጣው ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ግዑዟ ምድር ትጠፋለች ብሎ አያስተምርም። መዝሙራዊው ‘አምላክ ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረትዋ ላይ አጽንቷታል’ በማለት ጽፏል። (መዝሙር 104:5) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ያለው ፍጥረት በሙሉ ዓለም አቀፍ በሆነ እሳት ይጠፋል ብሎ አያስተምርም። (ኢሳይያስ 45:18) ኢየሱስ ራሱ አንዳንድ ሰዎች ከመጨረሻው ዘመን በሕይወት እንደሚተርፉ አመልክቷል። (ማቴዎስ 24:21, 22) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ፍጻሜው ይመጣል ብሎ የሚናገረው ምንን በተመለከተ ነው?
ስኬታማ ያልሆነው የሰው ልጅ አገዛዝ ወደ ፍጻሜው ይመጣል። አምላክ ነቢዩ ዳንኤልን እንዲህ ብሎ እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል፦ “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44
ጦርነትና የምድር ብክለት ወደ ፍጻሜው ይመጣል። መዝሙር 46:9 አምላክ ምን እንደሚያከናውን ሲናገር “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን እንደሚያጠፋቸው’ ያስተምራል።—ራእይ 11:18
ወንጀልና የፍትሕ መጓደል ወደ ፍጻሜው ይመጣል። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ተስፋ ይሰጣል፦ *—ምሳሌ 2:21, 22
“ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”2 መጨረሻው የሚመጣው መቼ ነው?
ይሖዋ አምላክ ክፋትን ወደ ፍጻሜው ለማምጣትና የራሱን መንግሥት ለማቋቋም ‘የተወሰነ ጊዜ’ ቀጥሯል። (ማርቆስ 13:33) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ማስላት እንደማንችል በግልጽ ይናገራል። ኢየሱስ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” ብሏል። (ማቴዎስ 24:36) ይሁን እንጂ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ አምላክ መጨረሻውን ሊያመጣ ሲል በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ትንቢት ተናግረዋል። ቀጥሎ የተዘረዘሩት ክንውኖች በሙሉ በተመሳሳይ ጊዜና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከሰቱ መጨረሻው በጣም እንደቀረበ ይታወቃል።
ፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ነውጥ ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን ሲከሰት። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጨረሻው ዘመን ላነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ በተለያየ ስፍራ የምድር ነውጥና የምግብ እጥረት ይከሰታል። እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።” (ማርቆስ 13:8) ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
በመላው ዓለም በብዙ ቋንቋዎች የስብከት ዘመቻ ሲካሄድ። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:14
3 መጨረሻው ከመጣ በኋላ ምን ይከናወናል?
መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ሰዎች ሁሉ በተድላና በደስታ ለዘላለም እንዲኖሩ ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ ብሎ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለሰው ዘር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚፈጸም ኢየሱስ አስተምሯል። ኢየሱስ “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5፤ 6:9, 10) መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት የሚሞቱ ሰዎች የትንሣኤ ተስፋ እንዳላቸው ይናገራል። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ታዲያ መጨረሻው ከመጣ በኋላ ምን ይከናወናል?
ኢየሱስ በሰማይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል [ከሞት የተነሳው ኢየሱስ] ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ [ይሖዋ አምላክ] መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል [ለኢየሱስ] ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።”—ዳንኤል 7:13, 14፤ ሉቃስ 1:31, 32፤ ዮሐንስ 3:13-16
የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ፍጹም ጤንነት፣ ዘላቂ ሰላምና ዘላለማዊ ሕይወት ያገኛሉ። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም።” (ኢሳይያስ 65:21-23) ሐዋርያው ዮሐንስም ስለዚያ ጊዜ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4
4 ከመጨረሻው ዘመን በሕይወት ለመትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ አንዳንዶች አምላክ በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ክፋትን ከምድር ላይ ያስወግዳል በሚለው ሐሳብ እንደሚያሾፉ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ያም ሆኖ ጴጥሮስ በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎች ቀጥሎ ያለውን እርምጃ እንዲወስዱ ማበረታቻ ሰጥቷል።
ከታሪክ መማር። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[አምላክ] የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።” (2 ጴጥሮስ 2:5) የሚያሾፉትን ሰዎች በተመለከተ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ከጥንት ጀምሮ ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ደረቁ ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንቶ እንደቆመና በውኃ መካከል እንደነበረ ለማስተዋል ፈቃደኞች አይደሉም። በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል። ሆኖም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር * ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።”—2 ጴጥሮስ 3:5-7
በሕይወትህ ውስጥ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተግባራዊ ማድረግ። ከመጨረሻው በሕይወት መትረፍ የሚፈልጉ ሁሉ ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር እንደሚከተሉና ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ተግባሮች’ እንደሚፈጽሙ ጴጥሮስ ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:11) ጴጥሮስ ስለ “ቅዱስ ሥነ ምግባር” እና ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን ስለሚያሳዩ ተግባሮች’ ጎላ አድርጎ መግለጹን ልብ በል። ስለዚህ ጉዳዩ እንዲሁ እምነት አለኝ ብሎ ከመናገር ወይም ከጥፋት ለመትረፍ ብሎ ባለቀ ሰዓት ላይ አምላክን ለማስደሰት ጥረት ከማድረግ ያለፈ ነገር ይጠይቃል።
በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሥነ ምግባሮችና ድርጊቶች ምንድን ናቸው? ስለዚህ ጉዳይ የምታውቀውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር ለምን አታወዳድርም? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ደስተኞች ናቸው። የሚሰጡህን መልስ ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያሳዩህ ጠይቃቸው። እንዲህ ማድረግህ በአሁኑ ጊዜ በሚያስፈሩ ነገሮች የተከበብን ቢሆንም እንኳ የወደፊቱን ጊዜ በድፍረትና በልበ ሙሉነት እንድትጠብቅ ሊረዳህ ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.8 በተጨማሪም በዚህ መጽሔት ገጽ 22 ላይ የሚገኘውን “ሁሉም ሰው አምላክን ለማወቅና ለመውደድ እንዲችል እኩል አጋጣሚ ያገኛል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.19 ጴጥሮስ እዚህ ላይ ምድር የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ሙሴም በተመሳሳይ ምድር የሚለውን ቃል በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅሞበት ነበር። “ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች” ሲል ጽፏል። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም) ግዑዟ ምድር “አንድ ቋንቋ” እንደማትናገር ሁሉ የምትጠፋውም ግዑዟ ምድር አይደለችም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ እንደተናገረው ጥፋት የሚደርስባቸው ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ናቸው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ምድር ሳትሆን፣ ምድርን የሚያበላሹ ሰዎች ይጠፋሉ