በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነፃ ምርጫ በመስጠት አክብሮናል

ነፃ ምርጫ በመስጠት አክብሮናል

ወደ አምላክ ቅረብ

ነፃ ምርጫ በመስጠት አክብሮናል

2 ነገሥት 18:1-7

ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን አለባቸው። ወላጆች የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ፣ ልጆች ጥሩ ባሕርያትን እንዲያፈሩ አልፎ ተርፎም በሕይወታቸው ውስጥ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል። የሚያሳዝነው ግን በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ አይሆኑም። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ወላጆች ያሏቸው ልጆች ጥሩ ሊሆኑ አይችሉም ማለት ነው? የዚህን መልስ ለማግኘት አንድ የሚያጽናና ሐቅ እንመልከት፦ ይሖዋ አምላክ እያንዳንዳችንን ነፃ ምርጫ በመስጠት አክብሮናል። በ2 ነገሥት 18:1-7 ላይ የሚገኘው የሕዝቅያስ ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል።

ሕዝቅያስ “የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ” ነው። (ቁጥር 1) አካዝ ተገዢዎቹን ከይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ፈቀቅ እንዲሉ አድርጓቸው ነበር። ይህ ክፉ ንጉሥ በበዓል አምልኮ ይካፈል ስለነበር ሰዎችን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ደርሷል። አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት የሕዝቅያስ ወንድሞች መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይሠዉ አልቀሩም። አካዝ የቤተ መቅደሱን በሮች ያስዘጋ ከመሆኑም በላይ “በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጎዳናው ማዕዘን ላይ መሠዊያ አቆመ።” በዚህም የተነሳ ይሖዋን “ለቍጣ አነሣሣው።” (2 ዜና መዋዕል 28:3, 24, 25) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ሕዝቅያስ በጣም መጥፎ የሆነ አባት ነበረው። ታዲያ ሕዝቅያስ የአባቱን ዓይነት ስህተት መድገሙ አይቀርም ማለት ነው?

ሕዝቅያስ በአካዝ እግር ተተክቶ ከነገሠ በኋላ የአባቱ መጥፎ ምሳሌ የእሱን ማንነት እንዳልቀረጸው ለማሳየት ጊዜ አልወሰደበትም። ሕዝቅያስ “በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።” (ቁጥር 3) ሕዝቅያስ በይሖዋ ታመነ፤ እንዲያውም “ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም።” (ቁጥር 5) ወጣቱ ንጉሥ፣ የአረማውያን ጣዖቶች የሚመለኩባቸውን በየኰረብታው ላይ ያሉትን ማምለኪያዎች በማስወገድ በግዛቱ የመጀመሪያ ዓመት ላይ መንፈሳዊ ተሃድሶ ማካሄድ ጀመረ። ቤተ መቅደሱ የተከፈተ ከመሆኑም ሌላ ንጹሕ አምልኮ ዳግመኛ ተቋቋመ። (ቁጥር 42 ዜና መዋዕል 29:1-3, 27-31) ሕዝቅያስ ከይሖዋ ‘ጋር የተጣበቀ’ ሲሆን ይሖዋም “ከእርሱ ጋር” ነበር።—ቁጥር 6, 7

ሕዝቅያስ የአባቱን መጥፎ ምሳሌ እንዳይከተል የረዳው ምንድን ነው? ብዙም ስለ እሷ ያልተጠቀሰው እናቱ አብያ በልጇ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት አድርጋ ይሆን? ሕዝቅያስ ከመወለዱ በፊት የነቢይነቱን ሥራ የጀመረው ነቢዩ ኢሳይያስ የተወው ጥሩ ምሳሌ ወጣቱን ንጉሥ ቀርጾት ይሆን? * በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በአንድ ነገር እርግጠኞች ነን፦ ሕዝቅያስ ከአባቱ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ የሕይወት መንገድ ለመከተል መርጧል።

የሕዝቅያስ ምሳሌ፣ ጥሩ አርዓያ ባልሆኑ ወላጆች ምክንያት አስቸጋሪ የልጅነት ሕይወት ላሳለፈ ለማንኛውም ሰው ግሩም ማበረታቻ ይሆናል። ያለፈው ነገር አልፏል፤ ያለፉትን መጥፎ ተሞክሮዎች መቀልበስ አንችልም። ይሁን እንጂ እነዚህ መጥፎ ተሞክሮዎች ጥሩ ሰው እንዳንሆን ያግዱናል ማለት አይደለም። አሁኑኑ ወደፊት ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ የሚያስችሉንን ምርጫዎች ማድረግ እንችላለን። እንደ ሕዝቅያስ ሁሉ እኛም እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለመውደድና እሱን ለማምለክ መምረጥ እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ በአሁኑ ጊዜ እርካታ ያለው ሕይወት እንድንመራ ወደፊት ደግሞ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4) አፍቃሪው አምላካችን በጣም ውድ የሆነውን ስጦታ ይኸውም ነፃ ምርጫ በመስጠት እያንዳንዳችንን በማክበሩ ልናመሰግነው አይገባም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ኢሳይያስ ከ778 ዓ.ዓ. ገደማ አንስቶ ከ732 ዓ.ዓ. በኋላ እስካለው ጊዜ በነቢይነት አገልግሏል። ሕዝቅያስ ንጉሥ የሆነው በ745 ዓ.ዓ. በ25 ዓመቱ ነበር።