በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ ይጠብቅብናል?

አምላክ ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ ይጠብቅብናል?

አምላክ ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ ይጠብቅብናል?

በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ኃጢአትን ለቄስ ወይም ለአንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መናዘዝ ሃይማኖታዊ ሥርዓትና የአምልኮ ክፍል ሆኖ ለበርካታ ዘመናት ኖሯል። ይሁንና ማንኛውም ዓይነት አመለካከት ተቀባይነት ሊኖረው እንደሚገባ በሚታሰብበት በዛሬው ጊዜ ኃጢአትን መናዘዝ ጠቃሚ አልፎ ተርፎም አስፈላጊ ነው?

ስለዚህ ጉዳይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። ለምሳሌ በካናዳው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ግለሰብ፣ ለሌላ ሰው የሠራኸውን ስህተት መናገር የሚከብድ ቢሆንም “አንድ ሰው ሐሳብህን ሲያዳምጥህ፣ አብሮህ ሲጸልይና ስህተትህን ለማስተካከል ምን ማድረግ እንደሚገባህ ሲነግርህ ቀለል ይልሃል” በማለት ተናግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ አባ፣ ኃጢአት ሠርቻለሁና ይቅር ይበሉኝ በተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ኃጢአትን የመናዘዝ ሥነ ሥርዓት ከቤተ ክርስቲያን ጎጂ ልማዶች አንዱ ነው። ይህ ልማድ ሰዎችን ከልክ በላይ እንዲጨነቁ ያደርጋቸዋል።” ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ለእስራኤል ብሔር በሰጠው ሕግ ውስጥ አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ምን ማድረግ እንዳለበት ግልጽ መመሪያ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድል ወይም የአምላክን ሕግ ቢተላለፍ ከሌዊ ነገድ ለሆነ የተቀባ ካህን ኃጢአቱን መናዘዝ ይኖርበታል፤ ካህኑም ሰውየው የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኝ የኃጢአት ማስተሰረያ መሥዕዋት ለአምላክ ያቀርባል።—ዘሌዋውያን 5:1-6

ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ንጉሥ ዳዊት ስለሠራው ኃጢአት ነቢዩ ናታን ሲገሥጸው ምን ምላሽ ሰጠ? ወዲያውኑ ጥፋቱን በማመን “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” አለ። (2 ሳሙኤል 12:13) በተጨማሪም ይሖዋ ሞገሱን እንዲሰጠው በጸሎት ተማጸነ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ከጊዜ በኋላ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም ‘መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ’ አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ።”—መዝሙር 32:5፤ 51:1-4

በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ኃጢአትን መናዘዝ አምላክ ከክርስቲያን ጉባኤ የሚጠብቀው ብቃት ሆኖ ቀጥሏል። በኢየሩሳሌም ጉባኤ ውስጥ አመራር ይሰጡ ከነበሩት ወንድሞች አንዱ የሆነው የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “ፈውስ ማግኘት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ኃጢአታችሁን በግልጽ ተናዘዙ፤ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ” በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ያዕቆብ 5:16) ታዲያ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች መናዘዝ ያለባቸው ምን ዓይነት ኃጢአቶችን ነው? ደግሞስ የሚናዘዙት ለማን ነው?

መናዘዝ ያለብን ምን ዓይነት ኃጢአቶችን ነው?

የሰው ልጆች በሙሉ ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን በየቀኑ ደግነት የጎደለው ድርጊት በመፈጸም ወይም አንደበታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም ሌሎችን ልንበድል እንችላለን። (ሮም 3:23) ይህ ሲባል ታዲያ የፈጸምነውን እያንዳንዱን ስህተት በኃላፊነት ቦታ ላይ ለሚገኝ አንድ የተሾመ ሰው መናዘዝ አለብን ማለት ነው?

ማንኛውም ኃጢአት በአምላክ ፊት የተጠላ ቢሆንም እንኳ አምላክ ስህተት የምንፈጽመው በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት መሆኑን ከግምት በማስገባት ምሕረት ያሳየናል። በእርግጥም መዝሙራዊው እንደሚከተለው ማለቱ የተገባ ነው፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።” (መዝሙር 130:3, 4) ታዲያ ስህተት ስንሠራና ሌሎችን ስንበድል ምን ማድረግ ይኖርብናል? ምናልባትም ይህንን ያደረግነው ባለማወቅ ቢሆንስ? ኢየሱስ ለተከታዮቹ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ “እኛ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ስለምንል ኃጢአታችንን ይቅር በለን” የሚለውን ልመና ማካተቱን ልብ በል። (ሉቃስ 11:4) አዎን፣ አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን በኢየሱስ ስም ቀርበን ከጠየቅነው ምሕረት ያደርግልናል።—ዮሐንስ 14:13, 14

ኢየሱስ፣ አምላክ ይቅር እንዲለን እኛም “የበደሉንን ሁሉ” ይቅር ማለት እንዳለብን መናገሩን ልብ በል። ሐዋርያው ጳውሎስም የእምነት ባልንጀሮቹን “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 4:32) ሌሎች ሲበድሉን ይቅር የምንል ከሆነ አምላክም የእኛን በደል ይቅር ይለናል ብለን ለመጠበቅ የሚያስችል በቂ ምክንያት ይኖረናል።

እንደ መስረቅ፤ ሆን ብሎ መዋሸት፤ የፆታ ብልግና መፈጸምና መስከርን የመሳሰሉ ሌሎች ከባድ ኃጢአቶችንስ አምላክ ይቅር ይለናል ብለን መጠበቅ እንችላለን? እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት የሚፈጽም ሰው የአምላክን ሕጎች የተላለፈ ሲሆን ኃጢአት የሠራውም በአምላክ ላይ ነው። ታዲያ አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት መናዘዝ አለበት?

ኃጢአትን መናዘዝ ያለብን ለማን ነው?

አምላክ በእሱ ላይ የተፈጸሙ ኃጢአቶችን የማስተሰረይ ሥልጣንን ለማንም ሰው አልሰጠም፤ ይህንን ማድረግ የሚችለው እሱ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንዲህ ይላል፦ “ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ [አምላክ] ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፣ እንዲሁም ከክፋት ሁሉ ያነጻናል።” (1 ዮሐንስ 1:9) ይሁንና እንዲህ ያሉትን ኃጢአቶች መናዘዝ ያለብን ለማን ነው?

የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው ከአምላክ ብቻ በመሆኑ ኃጢአታችንንም መናዘዝ ያለብን ለእሱ ነው። ከላይ እንዳየነው ዳዊት ያደረገው እንዲሁ ነው። ይሁንና የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን? መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል” በማለት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) በእርግጥም፣ አንድ ሰው የኃጢአት ይቅርታ ማግኘቱ የተመካው ድርጊቱ ትክክል አለመሆኑን አምኖ በመቀበሉና ኃጢአቱን በመናዘዙ ላይ ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ መንገዱን እርግፍ አድርጎ ለመተው ፈቃደኛ በመሆኑ ላይ ነው። ብዙ ጊዜ እንዲህ ማድረጉ ቀላል ባይሆንም እርዳታ ማግኘት የምንችልበት መንገድ አለ።

ከላይ የተመለከትነውን “ፈውስ ማግኘት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ኃጢአታችሁን በግልጽ ተናዘዙ፤ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ” የሚለውን የደቀ መዝሙሩን ያዕቆብ ምክር አስታውስ። አክሎም “የጻድቅ ሰው ጸሎት ታላቅ ኃይል አለው፤ ብዙ ነገርም ያከናውናል” ብሏል። (ያዕቆብ 5:16) እዚህ ጥቅስ ላይ “ጻድቅ ሰው” የተባለው ያዕቆብ በቁጥር 14 ላይ ከጠቀሳቸው “የጉባኤ ሽማግሌዎች” መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት የሚፈልጉትን ለመርዳት የተሾሙ መንፈሳዊ “ሽማግሌዎች” ይገኛሉ። ማንኛውም ሰው በአምላክ ላይ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን ይቅር የማለት ሥልጣን ስለሌለው እነዚህ “ሽማግሌዎች” የማንንም ኃጢአት ይቅር ማለት አይችሉም። * ይሁንና አንድን ከባድ ኃጢአት የሠራ ሰው የኃጢአቱን ክብደትና ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ለመርዳት የመገሠጽና የማስተካከል መንፈሳዊ ብቃት አላቸው።—ገላትያ 6:1

ኃጢአትን መናዘዝ ለምን አስፈለገ?

አንድ ሰው የፈጸመው ኃጢአት ከባድ ሆነም አልሆነ ግለሰቡ ከሰዎችና ከአምላክ ጋር ያለው ግንኙነት ሻክሯል። በመሆኑም ግለሰቡ ሊረበሽ ወይም ሊጨነቅ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርገው ፈጣሪያችን የሰጠን ሕሊና ነው። (ሮም 2:14, 15) ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይቻላል?

አሁንም ወደ ያዕቆብ መጽሐፍ ስንመለስ የሚከተሉትን አበረታች ቃላት እናገኛለን፦ “ከእናንተ መካከል [በመንፈሳዊ] የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባልለታል።”—ያዕቆብ 5:14, 15

እዚህም ላይ መንጋው የሚያስፈልገውን ለሟሟላት ሽማግሌዎች እርምጃ እንደሚወስዱ ተገልጿል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ግለሰቡ ኃጢአቱን ሲናዘዝ መስማት ብቻ በቂ ሊሆን አይችልም። ይህ ሰው መንፈሳዊ ሕመም ስላለበት ‘እንዲፈወስ’ ሽማግሌዎች ሊያደርጓቸው የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ነገሮች አሉ። ያዕቆብ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮችን ጠቅሷል።

በመጀመሪያ ‘ዘይት መቀባት’ ያስፈልጋቸዋል። ይህ የአምላክ ቃል ያለውን የመፈወስ ኃይል ያመለክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ . . . የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል” በማለት ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል። (ዕብራውያን 4:12) ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም በመንፈሳዊ የታመመው ሰው የችግሩን መንስኤ እንዲያስተውልና በአምላክ ፊት ያለውን አቋም ለማስተካከል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሊረዱት ይችላሉ።

ቀጥሎም “በእምነት የቀረበ ጸሎት” ያስፈልጋል። ሽማግሌዎቹ የሚያቀርቡት ጸሎት አምላክ ፍትሕን የሚያስፈጽምበትን መንገድ ባያስለውጠውም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ኃጢአትን ይቅር ለማለት ዝግጁ በሆነው አምላክ ፊት ጸሎታቸው ትልቅ ቦታ አለው። (1 ዮሐንስ 2:2) አምላክ ከልቡ ንስሐ የገባና “ለንስሐ የሚገባ ሥራ” የሚሠራ ማንኛውንም ኃጢአተኛ ለመርዳት ዝግጁ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 26:20

በሰውም ይሁን በአምላክ ላይ የሠራነውን በደል ለመናዘዝ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ማግኘት ስለምንፈልግ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው አምላክን በንጹሕ ሕሊና ለማምለክ አስቀድመን ከሰዎች ጋር ያለንን አለመግባባት መፍታትና እርቅ መፍጠር ይኖርብናል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ምሳሌ 28:13 “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” ይላል። ራሳችንን በይሖዋ አምላክ ፊት ዝቅ አድርገን ይቅርታ ለማግኘት ከለመንን አምላክ ሞገሱን የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ በተገቢው ጊዜ ከፍ ያደርገናል።—1 ጴጥሮስ 5:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 አንዳንዶች በዮሐንስ 20:22, 23 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ለሰዎች እንደተሰጠ እንደሚገልጽ ይሰማቸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሚያዝያ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28, 29⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን በኢየሱስ ስም ከጠየቅነው ድክመቶቻችንን አይቆጥርብንም እንዲሁም ምሕረት ያደርግልናል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሠራነውን በደል ለመናዘዝ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ማግኘት ስለምንፈልግ ነው