በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በልሳን መናገር ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው?

በልሳን መናገር ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው?

በልሳን መናገር ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ ነው?

“ፈጽሞ ሊገባኝ ያልቻለ ነገር አለ” በማለት ዴቨን ይናገራል። “ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየሳምንቱ ብዙ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የሚቀበሉ ይመስላል፤ ምክንያቱም በተአምራዊ ሁኔታ በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገራሉ። ሆኖም ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ አኗኗራቸው ሥነ ምግባር የጎደለው ነው። በሌላ በኩል ግን እኔ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኜ ለመኖር እጥራለሁ። ያም ሆኖ ምንም ያህል ብጸልይ ይህን የመንፈስ ስጦታ አግኝቼ አላውቅም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?”

ጋብርኤልም በሚሄድበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ተቀብለው በልሳኖች የሚናገሩ ይመስላል። እንዲህ ብሏል፦ “እየጸለይኩ እያለ ሌሎች በመሃል ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እኔም ሆንኩ እነሱ የማይረዱትን ነገር ሲናገሩ ይረብሹኛል። እውነቱን ለመናገር፣ እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ማንንም አይጠቅምም። የአምላክ መንፈስ ስጦታ ጠቃሚ ዓላማ ሊኖረው አይገባም?”

ዴቨንና ጋብርኤል ያጋጠማቸው ሁኔታ ትኩረት የሚያሻው ጥያቄ ያስነሳል፦ በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰዎች በልሳን የሚናገሩት ከአምላክ ባገኙት ስጦታ ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የነበራቸውን በልሳን የመናገር ስጦታ መመርመራችን ጠቃሚ ነው።

“በተለያዩ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከዚያ በፊት በማያውቁት ቋንቋ የመናገር ችሎታ ስለተሰጣቸው አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች ይናገራል። ይህ ሁኔታ መጀመሪያ የተከሰተው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት ነበር። በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም የነበሩ 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”፤ ከዚያም “በተለያዩ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” ከሌሎች አገሮች የመጡት ሰዎች ይህን ሲያዩ ምን እንደተሰማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 1:15፤ 2:1-6

መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ዘመን የነበሩ ሌሎች የኢየሱስ ተከታዮችም ይህ አስደናቂ ችሎታ እንደነበራቸው ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በብዙ ልሳኖች መናገር ይችል ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:6፤ 1 ቆሮንቶስ 12:10, 28፤ 14:18) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስጦታ የሚያከናውነው ዓላማ ሊኖረው ይገባል። ታዲያ በልሳን መናገር በዚያ ዘመን ምን ዓላማ አከናውኗል?

የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው የሚጠቁም ምልክት ነበር

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች (ከመካከላቸው አንዳንዶቹ በልሳኖች ሳይናገሩ አይቀሩም) ሲጽፍ “በልሳኖች መናገር . . . አማኝ ላልሆኑት ምልክት ነው” ብሎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:22) በመሆኑም ሌሎች ተአምራዊ ችሎታዎችን ጨምሮ በልሳን የመናገር ችሎታ፣ አዲስ የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው እንዲሁም እሱ እንደሚደግፈው የሚጠቁም ምልክት ነበር። አቅጣጫ እንደሚጠቁሙ ምልክቶች ሁሉ እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎችም እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች በዚያ ወቅት የአምላክን ሕዝቦች የት እንደሚያገኟቸው የሚያመላክቱ ነበሩ።

ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆነ በቅድመ ክርስትና ዘመን ከነበሩት ነቢያት መካከል አንዳቸውም ቢሆን ከዚያ በፊት በማያውቋቸው ቋንቋዎች በተአምር እንደተናገሩ መጽሐፍ ቅዱስ የማይገልጽ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተሰጠው በልሳን የመናገር ስጦታ ሌላም ዓላማ ነበረው።

ምሥራቹን ለማስፋፋት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል

ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለአይሁዳውያን ብቻ እንዲሰብኩ አዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:6፤ 15:24) በዚህም የተነሳ ደቀ መዛሙርቱ በአብዛኛው አይሁዶች ከሚኖሩባቸው ማኅበረሰቦች ውጭ አልሰበኩም ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የሚለወጥበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም።

በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹን “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዘዛቸው። በተጨማሪም ለተከታዮቹ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንደሚሆኑ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 28:19፤ የሐዋርያት ሥራ 1:8) ምሥራቹን እስከ ምድር ዳር ለማሰራጨት ከዕብራይስጥ በተጨማሪ ብዙ ቋንቋዎችን መጠቀም ያስፈልግ ነበር።

ይሁን እንጂ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መካከል ብዙዎቹ “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 4:13) ታዲያ መናገር ይቅርና ሰምተዋቸውም እንኳ የማያውቁ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው ሩቅ አገሮች መስበክ የሚችሉት እንዴት ነው? ቀናተኛ ከነበሩት ከእነዚህ ሰባኪዎች አንዳንዶቹ ከዚያ በፊት ፈጽሞ በማይችሏቸው ቋንቋዎች አቀላጥፈው መስበክ እንዲችሉ መንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ችሎታ ሰጥቷቸዋል።

ከዚህ ለማየት እንደምንችለው በልሳን የመናገር ስጦታ ሁለት ዓበይት ዓላማዎችን አከናውኗል። በመጀመሪያ፣ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው የሚጠቁም ምልክት ነበር። ሁለተኛ፣ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩ ሕዝቦች እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ እንዲፈጽሙ በመርዳት ረገድ ውጤታማ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰዎች በልሳን መናገራቸው እነዚህን ዓላማዎች ለማከናወን ያስችላል?

በዛሬው ጊዜ በልሳን መናገር—የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው የሚጠቁም ምልክት ነው?

በምትኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች እንዲያዩት የምትፈልገውን ምልክት የምትለጥፈው የት ነው? በአንድ ትንሽ ቤት ውስጥ ነው? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! በጴንጤቆስጤ ዕለት ስለተፈጸመው ሁኔታ ከሚገልጸው ዘገባ ማየት እንደምንችለው ደቀ መዛሙርቱ በተአምራዊ ሁኔታ በልሳን ሲናገሩ በአካባቢው የነበረ “ብዙ ሕዝብ” ይህን ምልክት በግልጽ አይቷል። እንዲያውም በዚህ የተነሳ በዚያው ቀን በክርስቲያን ጉባኤ ላይ “ሦስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ነፍሳት ተጨመሩ!” (የሐዋርያት ሥራ 2:5, 6, 41) በዛሬው ጊዜ በልሳን እንናገራለን የሚሉ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ብቻ ከሆነ ይህ ተግባር ለማያምኑ ብዙ ሰዎች በግልጽ የሚታይ ምልክት ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው?

ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል ዝሙትና ሌሎች “የሥጋ ሥራዎች” መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ እንዳይሠራ እንደሚያደርጉ የሚጠቅስ ከመሆኑም በላይ “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ይናገራል። (ገላትያ 5:17-21) እንግዲያው አጠያያቂ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች በልሳን ሲናገሩ የምትመለከት ከሆነ ‘የአምላክ ቃል የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች የመፈጸም ልማድ ላላቸው ሰዎች የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሰጠቱ በቃሉ ውስጥ ከሰፈረው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ አልፎ ተርፎም የሚያሳስት አይሆንም?’ ብለህ ብታስብ አይፈረድብህም። እንዲህ ያለው ሁኔታ ተሽከርካሪዎችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ የሚመራ የመንገድ ምልክት እንደ መትከል ይቆጠራል።

በዛሬው ጊዜ በልሳን መናገር—ምሥራቹን ለማስፋፋት መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው በልሳን የመናገር ስጦታ ስለነበረው ሌላ ዓላማስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በልሳን የሚናገሩ ሰዎች ይህን ችሎታቸውን የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩ ሕዝቦች ምሥራቹን ለመስበክ እየተጠቀሙበት ነው? በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም የነበሩት ሰዎች ከብዙ አገሮች የመጡ እንደነበሩና ደቀ መዛሙርቱ በተአምራዊ መንገድ የተናገሯቸውን ቋንቋዎች በግልጽ መረዳት እንደቻሉ አስታውስ። ከዚህ በተቃራኒ በዛሬው ጊዜ በልሳን የሚናገሩ ሰዎች በአብዛኛው የሚናገሩት ነገር ለማንም የሚገባ አይደለም።

በግልጽ ለማየት እንደምንችለው በዘመናችን በልሳን መናገር የሚባለው ነገር ለጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ከተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በጣም የተለየ ነው። እንዲያውም ከሐዋርያት ሞት በኋላ ማንም ሰው የእነሱን ዓይነት ተአምራዊ ስጦታ ማግኘቱን የሚገልጽ ሊታመን የሚችል የታሪክ መዝገብ የለም። ይህ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያነቡ ሰዎች የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በልሳን መናገርን ጨምሮ ተአምራዊ ስጦታዎች ‘እንደሚያበቁ’ በመንፈስ መሪነት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ታዲያ አንድ ሰው በዛሬው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው እነማን እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?

መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸው በማስረጃ ማረጋገጥ የሚችሉት እነማን ናቸው?

ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በልሳን የመናገር ስጦታ እንደሚያበቃ በሚገባ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እውነተኛ ተከታዮቹን ለይቶ የሚያሳውቀውን ዘመን የማይሽረው ምልክት ተናግሯል። “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) እንዲያውም የአምላክ ቃል፣ ተአምራዊ ስጦታዎች ውሎ አድሮ እንደሚያቆሙ በሚናገርበት በዚያው ጥቅስ ላይ “ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 13:8

ከዘጠኙ የአምላክ መንፈስ “ፍሬ” ገጽታዎች ወይም መንፈሱ ከሚያፈራቸው ባሕርያት መካከል መጀመሪያ የተጠቀሰው ፍቅር ነው። (ገላትያ 5:22, 23) በመሆኑም የአምላክ መንፈስና የአምላክ ድጋፍ በእርግጥ ያላቸው ሰዎች በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር ይኖራቸዋል። ከዚህም ሌላ በሦስተኛ ደረጃ የተጠቀሰው የመንፈስ ፍሬ ገጽታ ሰላም ነው። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻን፣ ዘረኝነትንና ዓመፅን አስወግደው ሰላማዊ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

በሐዋርያት ሥራ 1:8 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢትም አስታውስ። ደቀ መዛሙርቱ ኃይል እንደሚቀበሉና “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንደሚሆኑ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ በትንቢቱ ላይ ይህ ሥራ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” እንደሚቀጥልም አመልክቷል። (ማቴዎስ 28:20 አ.መ.ት.) በመሆኑም ይህ ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ዛሬም አምላክ መንፈስ ቅዱስን የሰጣቸውን ሰዎች ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ይሆናል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከላይ ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር በዛሬው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸው በማስረጃ ማረጋገጥ የሚችሉት እነማን ይመስሉሃል? የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን በተለይም ፍቅርንና ሰላምን በግልጽ የሚያንጸባርቁት እነማን ናቸው? እነዚህን ባሕርያት ለማፍራት ሲሉ በየትኛውም ቦታ በጦርነት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በመንግሥታት እጅ ብዙ ሥቃይ የደረሰባቸው እነማን ናቸው? (ኢሳይያስ 2:4) እንደ ዝሙት ካሉት የሥጋ ሥራዎች ለመራቅ ጥረት የሚያደርጉትና እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እየፈጸሙ ንስሐ የማይገቡትን ከመካከላቸው እስከ ማስወገድ ድረስ እርምጃ የሚወስዱት እነማን ናቸው? (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ የሚገልጸውን ምሥራች በመላው ምድር እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው?—ማቴዎስ 24:14

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች፣ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች ሊያሟሏቸው እንደሚገቡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሳቸውን ነጥቦች ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። አንተስ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የበለጠ በመመርመር የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለምን ራስህ አታረጋግጥም?