በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አፍራሽ ስሜቶችን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

አፍራሽ ስሜቶችን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

አፍራሽ ስሜቶችን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

አፍራሽ ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶት የማያውቅ ማን አለ? ባለንበት ዘመን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ብዙዎችን እያስጨነቋቸው ከመሆኑም ሌላ በብዙ አካባቢዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ዓመፅና ዓይን ያወጣ የፍትሕ መዛባት የተለመደ ሆኗል። ከዚህ አንጻር ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በሐዘን ቢዋጡ እንዲሁም ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነትና የዋጋ ቢስነት ስሜት ቢያድርባቸው አያስገርምም።

እንዲህ ዓይነቶቹ ስሜቶች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በራስ የመተማመን ስሜታችንን ሊሸረሽሩብን፣ የማመዛዘን ችሎታችንን ሊያዛቡብንና ደስታችንን ሊሰርቁብን ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” ይላል። (ምሳሌ 24:10) በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ ተስፋ ሳንቆርጥ ለመቀጠል ኃይል ያስፈልገናል። ስለዚህ አፍራሽ ስሜቶችን መቆጣጠር በጣም አስፈላጊ ነው። *

አፍራሽ ስሜቶችን ለመቋቋም የሚረዱ ጠንካራ መከላከያዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ሕያው የሆነውን ነገር ሁሉ የፈጠረውና ሕይወት እንዲቀጥል የሚያደርገው ይሖዋ አምላክ፣ ተስፋ መቁረጥ ወይም ዋጋ ቢስነት ተጭኖህ እንድትዝል አይፈልግም። (መዝሙር 36:9) እንግዲያው አፍራሽ ስሜቶችን መቋቋም እንድንችል የአምላክ ቃል ሊረዳን የሚችልባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

አምላክ እንደሚያስብልህ እወቅ

አንዳንድ ሰዎች አምላክ በብዙ ጉዳዮች የተጠመደ ስለሆነ ለግል ስሜታችን ትኩረት እንደማይሰጥ ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ ይሰማሃል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪያችን ስለ ስሜታችን እንደሚያስብ ያረጋግጥልናል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” ብሏል። (መዝሙር 34:18) ሁሉን ቻይ የሆነው ሉዓላዊ አምላክ በጭንቀታችን ጊዜ ከእኛ እንደማይለይ ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው!

አምላክ የሌሎችን ስሜት የማይረዳ ወይም የማይቀረብ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ ሰዎችን የሚወዳቸው ሲሆን መከራ ሲደርስባቸውም ሥቃያቸው ይሰማዋል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት በግብፅ በባርነት ቀንበር ሥር በነበሩበት ጊዜ አምላክ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ። ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ [እታደጋቸዋለሁ]።”—ዘፀአት 3:7, 8

አምላክ ስሜታችንን በሚገባ ይረዳል። ደግሞም እኮ ‘የፈጠረን እሱ ነው።’ (መዝሙር 100:3) በመሆኑም ሰዎች ስሜታችንን እንደማይረዱልን በሚሰማን ጊዜም እንኳ እሱ ስሜታችንን እንደሚረዳልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። የአምላክ ቃል “እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙኤል 16:7) ውስጣዊ ስሜቶቻችንም እንኳ ከአምላክ የተደበቁ አይደሉም።

እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የምንሠራቸውን ስህተቶችና ጉድለቶቻችንን ጭምር ያውቃል። ይሁን እንጂ አፍቃሪው ፈጣሪያችን ይቅር ባይ ነው፤ ለዚህም አመስጋኞች ነን። በመንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዱ የሆነው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።” (መዝሙር 103:13, 14) አምላክ የሚያየን እኛ ራሳችንን ከምናይበት በተለየ መንገድ ነው። ከኃጢአታችን ንስሐ እስከገባን ድረስ ጥሩ ጎናችንን ፈልጎ በማየት መጥፎውን ከአእምሮው ይሰርዘዋል።—መዝሙር 139:1-3, 23, 24

እንግዲያው በዋጋ ቢስነት ስሜት ስንዋጥ ይህን ስሜት ለመቋቋም ቆራጥ መሆን ያስፈልገናል። አምላክ እኛን የሚመለከትበትን መንገድ ማስታወስ ይኖርብናል!—1 ዮሐንስ 3:20

ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርት

አምላክ እኛን በሚመለከትበት መንገድ ራሳችንን መመልከታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችን አፍራሽ ስሜቶችን ለማሸነፍ የሚረዳንን ቀጣዩን እርምጃ ለመውሰድ ይኸውም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። በእርግጥ ይህን ማድረግ ይቻላል?

ይሖዋ አምላክ አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት እኛን ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ያበረታታናል። (ያዕቆብ 4:8) እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ እውነታ ሰፍሯል፦ ደካሞችና ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን።

አምላክ፣ ማንነቱን ማወቅ እንድንችል በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ ራሱ ገልጾልናል። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በማንበብ ስለ አምላክ ግሩም ባሕርያት ማወቅ እንችላለን። * ባወቅነው ነገር ላይ ስናሰላስል ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብን ይሰማናል። እንዲሁም እውነተኛ ማንነቱን ይኸውም አፍቃሪና ርኅሩኅ አባት መሆኑን ይበልጥ እንገነዘባለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላነበብነው ነገር በጥልቅ ማሰብ ከዚህም የበለጠ ጥቅም ያስገኝልናል። የሰማዩ አባታችን አስተሳሰብ ወደ አእምሯችንና ልባችን ገብቶ እንዲያስተካክለን፣ እንዲያጽናናንና እንዲመራን ስንፈቅድለት ወደ እሱ ይበልጥ እየቀረብን እንሄዳለን። በተለይ ደግሞ የሚያስጨንቅ ወይም እረፍት የሚነሳን ስሜት በሚሰማን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ያስፈልገናል። መዝሙራዊው “አሳብና ጭንቀት በያዘኝ ጊዜ፤ አንተ ታጽናናኛለህ፤ ደስም ታሰኘኛለህ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 94:19 የ1980 ትርጉም) የአምላክ ቃል ታላቅ መጽናኛ የምናገኝበት ምንጭ ሊሆንልን ይችላል። እውነት የሆነውን የአምላክ ቃል በትሕትና የምንቀበል ከሆነ ቀስ በቀስ አፍራሽ ስሜቶቻችን ተወግደው አምላክ ብቻ የሚሰጠውን መጽናኛና ሰላም እናገኛለን። አንድ አፍቃሪ ወላጅ የተከፋ ወይም የተበሳጨ ልጁን እንደሚያባብለው ሁሉ ይሖዋም እኛን ያጽናናናል።

የአምላክ ወዳጅ ለመሆን የሚረዳን ሌላው ቁልፍ ነገር ከእሱ ጋር አዘውትሮ መነጋገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ [አምላክ] ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 5:14) የሚያስፈራን ወይም የሚያስጨንቀን ነገር ምንም ይሁን ምን ወደ አምላክ በመጸለይ እንዲረዳን መለመን እንችላለን። የልባችንን አውጥተን ለአምላክ ከነገርነው የአእምሮ ሰላም እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ፣ ለማሰላሰልና ለመጸለይ ቋሚ ፕሮግራም ካለህ ከሰማዩ አባትህ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደምትመሠርት ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ወዳጅነት ደግሞ አፍራሽ ስሜቶችን ለመቋቋም የሚረዳ ኃይለኛ መሣሪያ ነው። አፍራሽ ስሜቶችን ለመቋቋም ሌላስ ምን ሊረዳህ ይችላል?

አስተማማኝ በሆነው የወደፊት ተስፋህ ላይ አትኩር

እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ አእምሯችን አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ እንችላለን። እንዴት? አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን አስደናቂ ተስፋ በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።” (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ምን ማለት ነው?

“አዲስ ሰማያት” የሚለው አገላለጽ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ያመለክታል። “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ደግሞ በዚሁ ምድር ላይ የአምላክን ሞገስ አግኝቶ የሚኖረውን አዲስ ኅብረተሰብ ያመለክታል። ‘በአዲስ ሰማያት’ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የሚኖረው አዲስ ኅብረተሰብ አፍራሽ ስሜቶችን ከሚያስከትሉ ነገሮች ሁሉ ነፃ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚያ ጊዜ የሚኖሩ ታማኝ ሰዎች ስለሚኖራቸው ሕይወት ሲናገር “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ራእይ 21:4

እነዚህ ሐሳቦች ደስ የሚያሰኙና የሚያበረታቱ ናቸው ቢባል አንተም እንደምትስማማ የተረጋገጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የሰጣቸውን ተስፋ ‘አስደሳች የሆነው ተስፋ’ በማለት የሚገልጸው ለዚህ ነው። (ቲቶ 2:13) አምላክ ለሰው ዘር ቃል በገባቸው ተስፋዎች እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች አስተማማኝና እርግጠኛ መሆናቸውን እንድናምን ባደረጉን ምክንያቶች ላይ አእምሯችን እንዲያተኩር ካደረግን አፍራሽ ስሜቶችን መቋቋም እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 4:8

መጽሐፍ ቅዱስ የመዳን ተስፋችንን ከራስ ቁር ጋር ያመሳስለዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) በጥንት ዘመን አንድ ወታደር የራስ ቁሩን ሳይደፋ ጦር ሜዳ መግባት ጨርሶ የማይሞክረው ነገር ነበር። የራስ ቁሩ በራሱ ላይ የሚሰነዘርበት ጥቃት ኃይሉ እንዲበርድለት የሚረዳው ከመሆኑም ሌላ ተወንጭፈው የሚመጡት ፍላጻዎች ብዙም ሳይጎዱት ነጥረው እንዲመለሱ እንደሚያደርግ ያውቅ ነበር። የራስ ቁር የአንድን ወታደር ራስ ከጥቃት እንደሚከላከልለት ሁሉ ተስፋም አእምሯችንን ከአፍራሽ ስሜቶች ይጠብቅልናል። ብሩህ ተስፋ እንዲኖረን በሚያደርጉ ሐሳቦች ላይ ማውጠንጠናችን አፍራሽና አሉታዊ የሆኑ እንዲሁም ፍርሃት የሚያሳድሩ ስሜቶችን ለማስወገድ ይረዳናል።

ከዚህ ማየት እንደምንችለው አፍራሽ ስሜቶችን መቋቋም ይቻላል። አንተም ይህን ልታደርግ ትችላለህ! አምላክ እንዴት እንደሚመለከትህ አስታውስ፣ ወደ እሱ ይበልጥ ቅረብ እንዲሁም በወደፊት ተስፋህ ላይ አተኩር። እንዲህ ካደረግህ አፍራሽ አስተሳሰቦች ለዘላለም የሚወገዱበትን ጊዜ እንደምታይ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!—መዝሙር 37:29

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ረዘም ላለ ጊዜ የዘለቀ ወይም ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች የሕክምና ባለሙያ ማማከር ሊያስፈልጋቸው ይችላል።—ማቴዎስ 9:12

^ አን.14 በነሐሴ 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚረዳ ጠቃሚና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም ወጥቷል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።”—ዘፀአት 3:7, 8

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አሳብና ጭንቀት በያዘኝ ጊዜ፤ አንተ ታጽናናኛለህ፤ ደስም ታሰኘኛለህ።”—መዝሙር 94:19 የ1980 ትርጉም

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:7

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ስለ አምላክ የሚናገሩ አጽናኝ ጥቅሶች

“እግዚአብሔር ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ።”—ዘፀአት 34:6

“በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና።”—2 ዜና መዋዕል 16:9

“እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።”—መዝሙር 34:18

“ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ።”—መዝሙር 86:5

“እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።”—መዝሙር 145:9

“እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ።”—ኢሳይያስ 41:13

“ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . የተባረከ ይሁን።”—2 ቆሮንቶስ 1:3

“ልባችንም በፊቱ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት እናደርጋለን፤ ይህንም የምናደርገው ልባችን እኛን በሚኮንንበት ነገር ሁሉ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከልባችን ይበልጥ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።”—1 ዮሐንስ 3:19, 20

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አፍራሽ ስሜቶችን በመቋቋም ረገድ ተሳክቶላቸዋል

“አባቴ የመጠጥ ሱሰኛ ነው፤ በዚህም የተነሳ ብዙ ሥቃይ አድርሶብኛል። ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ በዋጋ ቢስነት ስሜት ስሠቃይ ኖሬያለሁ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ግን በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚገልጸውን ተስፋ ተማርኩ። ይህ ተስፋ አእምሮዬንና ልቤን በደስታ ሞላው። ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሕይወቴ ክፍል ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜም አይለየኝም። በአፍራሽ ስሜቶች ስዋጥ መጽሐፍ ቅዱሴን ገልጬ የሚያጽናኑ ጥቅሶችን አነባለሁ። ግሩም ስለሆኑት የአምላክ ባሕርያት ማንበቤ በእሱ ፊት በጣም ውድ እንደሆንሁ እርግጠኛ እንድሆን ያደርገኛል።”—የ33 ዓመቷ ካቲያ *

“የአልኮል፣ የማሪዋና፣ የኮኬይን እና የክራክ ኮኬይን ሱሰኛ የነበርኩ ሲሆን ማስቲሽም አሸት ነበር። የነበረኝን ንብረት ሁሉ ስለጨረስኩ ልመና ጀምሬ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ከተቀበልሁ በኋላ ግን አኗኗሬን ሙሉ በሙሉ ለወጥኩ። ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ቻልኩ። አሁንም እንኳ ከጥፋተኝነትና ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር እየታገልኩ ቢሆንም በአምላክ ምሕረትና ፍቅራዊ ደግነት ላይ መተማመንን ተምሬያለሁ። አምላክ አፍራሽ ስሜቶቼን ለመቋቋም እንድችል ምንጊዜም ብርታት እንደሚሰጠኝ እርግጠኛ ነኝ። ካገኘኋቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የሚበልጠው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቄ ነው።”—የ37 ዓመቱ ሬናቶ

“ትንሽ ልጅ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ራሴን ከታላቅ ወንድሜ ጋር አወዳድር ነበር። ሁልጊዜ ከእሱ የበታች እንደሆንሁ ይሰማኝ ነበር። እስካሁንም ድረስ በራስ ያለመተማመን ችግር አለብኝ። ይሁን እንጂ ይህን ስሜት ለማሸነፍ ቆርጫለሁ። ያለማቋረጥ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ፤ አምላክም ብቁ እንዳልሆንሁ የሚሰማኝን ስሜት እንዳሸንፍ ረድቶኛል። አምላክ በእርግጥም እንደሚወደኝና እንደሚያስብልኝ ማወቅ በጣም የሚያበረታታ ነው!”—የ45 ዓመቷ ሮቤርታ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.45 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።