ጸሎት—ጊዜውና ቦታው ልዩነት ያመጣል?
አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ለተንቆጠቆጡ የጸሎት ቤቶች ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጡና ምዕመኖቻቸው በቀኑ ውስጥ በተወሰነ ሰዓት ላይ መጸለይ እንዳለባቸው እንደሚያስተምሩ ሳታስተውል አልቀረህም። መጽሐፍ ቅዱስ በተወሰነ ጊዜና ቦታ መጸለይ እንዳለብን ያስተምራል?
እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለጸሎት ተስማሚ የሆኑ ሁኔታዎች እንዳሉ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ማዕድ ላይ ቀርቦ ሳለ አምላክን በጸሎት አመስግኗል። (ሉቃስ 22:17) ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ለአምልኮ በተሰበሰቡባቸው ጊዜያት አብረው ይጸልዩ ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው በአይሁድ ምኩራቦችና ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ለረጅም ጊዜ ይከናወን የነበረውን የጸሎት ልማድ እንደቀጠሉበት ያሳያል። ደግሞም አምላክ ቤተ መቅደሱ “ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት” እንዲሆን ዓላማው ነበር።—ማርቆስ 11:17
የአምላክ አገልጋዮች ተሰብስበው በአንድነት ሲጸልዩ ልመናቸው በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት ሊኖረው ይችላል። ቡድኑ አንድ ዓይነት መንፈስ ካለውና ቡድኑን በመወከል የሚቀርበው ጸሎት ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ ከሆነ አምላክ ይደሰታል። እንዲያውም እንዲህ ያለው ጸሎት አምላክ ባይጠየቅ ኖሮ የማይፈጽማቸውን ነገሮች እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይችላል። (ዕብራውያን 13:18, 19) የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባዎቻቸው ላይ ሁልጊዜ ይጸልያሉ። አንተም በአቅራቢያህ ወዳለው የመንግሥት አዳራሽ ሄደህ እንደነዚህ ያሉ ጸሎቶችን እንድታዳምጥ ሞቅ ያለ ግብዣ ቀርቦልሃል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በተወሰነ ጊዜ ወይም ቦታ ላይ ብቻ እንድንጸልይ በመግለጽ ገደብ አያበጅም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ አገልጋዮች በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ስፍራ እንደጸለዩ የሚናገሩ ዘገባዎችን እናገኛለን። ኢየሱስ “ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል” ብሏል።—ማቴዎስ 6:6
በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ መጸለይ እንችላለን
እንዴት ያለ አስደሳች ግብዣ ነው! ብቻህን ሆነህ በማንኛውም ጊዜ ወደ አጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ መቅረብ እንደምትችልና እሱም ትኩረት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ሁን። በመሆኑም ኢየሱስ መጸለይ ሲፈልግ ብዙ ጊዜ ብቻውን ለመሆን መምረጡ ምንም አያስገርምም! ኢየሱስ አንድ ሙሉ ሌሊት ወደ አምላክ ሲጸልይ ያደረበት ጊዜ ነበር፤ ከሁኔታው መረዳት እንደምንችለው በዚያን ወቅት በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ውሳኔ ለማድረግ መመሪያ አስፈልጎት ነበር።—ሉቃስ 6:12, 13
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡ ሌሎች ወንዶችና ሴቶችም ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ወይም ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ይጸልዩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጮክ ብለው ሌላ ጊዜ ደግሞ ድምፅ ሳያሰሙ ጸልየዋል፤ እንዲሁም በቡድን ሆነውም ይሁን ብቻቸውን ጸልየዋል። ዋናው ቁም ነገር መጸለያቸው ነበር። እንዲያውም አምላክ ለአገልጋዮቹ “ያለማቋረጥ ጸልዩ” የሚል ግብዣ አቅርቦላቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎችን ለማዳመጥ ምንጊዜም ፈቃደኛ ነው። ይህ በእርግጥ ፍቅራዊ ግብዣ አይደለም?
እርግጥ ነው፣ እምነት በጠፋበት በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ጸሎት ያለውን ጥቅም ይጠራጠራሉ። አንተም ‘በእርግጥ ጸሎት ሊጠቅመኝ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።