ጸሎት—ለምን አስፈለገ?
ጸሎት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የጸሎትን ያህል የብዙዎችን ትኩረት የሚስቡና የማወቅ ጉጉት የሚቀሰቅሱ ርዕሰ ጉዳዮች የሉም ማለት ይቻላል። እስቲ ጸሎትን በተመለከተ ዘወትር የሚጠየቁ ሰባት ጥያቄዎችን እናንሳና መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ አብረን እንመልከት። እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የተዘጋጁት የማትጸልይ ከሆነ መጸለይ እንድትጀምር፣ የምትጸልይ ከሆነ ደግሞ ጸሎትህ ይበልጥ ተሰሚነት እንዲኖረው ማድረግ እንድትችል ለመርዳት ታስበው ነው።
በዓለም ዙሪያ የተለያየ ባሕልና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ይጸልያሉ። እነዚህ ሰዎች የሚጸልዩት ብቻቸውን አሊያም በቡድን ሊሆን ይችላል። በቤተ ክርስቲያን፣ በቤተ መቅደስ፣ በምኩራብ፣ በመስጊድ ወይም ቅዱስ ብለው በሚጠሯቸው ሌሎች ስፍራዎች ሆነው ይጸልያሉ። በሚጸልዩበት ጊዜም የጸሎት ምንጣፎችን፣ መቁጠሪያዎችን፣ የጻድቃን ምስሎችን፣ የጸሎት መጻሕፍትን ወይም በትንንሽ ሰሌዳዎች ላይ ተጽፈው የሚሰቀሉ ጸሎቶችን ይጠቀሙ ይሆናል።
ጸሎት፣ እኛ ሰዎች በዚህች ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ፍጥረታት ከምንለይባቸው ነገሮች አንዱ ነው። እርግጥ ነው፣ ከእንስሳት ጋር የሚያመሳስለን ብዙ ነገር አለ። እኛም ሆን እንስሳት ምግብ፣ አየርና ውኃ ያስፈልገናል። እኛም እነሱም እንወለዳለን፣ እንኖራለን ከዚያም እንሞታለን። (መክብብ 3:19) የምንጸልየው ግን እኛ ሰዎች ብቻ ነን። ለምን?
ምናልባትም ለዚህ ጥያቄ ቀላሉ መልስ መጸለይ ስለሚያስፈልገን ነው የሚል ነው። ደግሞም ብዙ ሰዎች ጸሎትን የሚመለከቱት ቅዱስና ዘላለማዊ ነው ብለው ከሚያስቡት መንፈሳዊ ዓለም ጋር የሚያገናኛቸው መንገድ አድርገው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የመጸለይ ፍላጎት እንዲኖረን ተደርገን እንደተፈጠርን ይናገራል። (መክብብ 3:11 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 5:3
“መንፈሳዊ” ፍላጎት እንዲኖረን ተደርገን ባንፈጠር ኖሮ እነዚህ ሁሉ የተንቆጠቆጡና ያጌጡ የአምልኮ ሕንፃዎች ባልኖሩ ነበር! ስፍር ቁጥር የሌለው ሰዓትም በጸሎት ባላጠፋን ነበር! እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት በራሳቸው መንገድ ይሄዳሉ ወይም የሌሎች ሰዎችን ምክር ይከተላሉ። ይሁንና ሰዎች ሌሎችን ሙሉ በሙሉ መርዳት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ አይሰማህም? እኛ ሰዎች በጣም ደካሞችና አርቆ ማስተዋል የሚጎድለን ከመሆኑም በላይ ዕድሜያችን አጭር ነው። የሚያስፈልገንን ሊሰጠን የሚችለው ከእኛ እጅግ የላቀ ኃይልና ጥበብ ያለው እንዲሁም ከእኛ ይበልጥ ረጅም ጊዜ መኖር የሚችል አካል ብቻ ነው። ለመሆኑ እንድንጸልይ የሚያነሳሱን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ መመሪያና ጥበብ ለማግኘት ወይም ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ተመኝተህ ታውቃለህ? በአሰቃቂ ሁኔታ የምትወደውን ሰው በሞት በመነጠቅህ ምክንያት ከደረሰብህ ሐዘን መጽናናት ወይም ውሳኔ የሚጠይቅ አስጨናቂ ጉዳይ ስለገጠመህ መመሪያ ማግኘት አሊያም በጥፋተኝነት ስሜት በመደቆስህ ይቅርታ ማግኘት እንደሚያስፈልግህ ተሰምቶህ ያውቃል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እነዚህ ሁኔታዎች እንድንጸልይ የሚያነሳሱን ተገቢ ምክንያቶች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎትን በተመለከተ የሚናገረው ሐሳብ እጅግ አስተማማኝ ከመሆኑም በላይ መጽሐፉ ብዙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ያቀረቧቸውን ጸሎቶች ይዟል። እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ማጽናኛ፣ መመሪያና ይቅርታ ለማግኘት እንዲሁም ከባድ ለሆኑ ጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ጸልየው ነበር።—መዝሙር 23:3፤ 71:21፤ ዳንኤል 9:4, 5, 19፤ ዕንባቆም 1:3
እነዚህ ሰዎች ያቀረቡት ጸሎት የተለያየ ቢሆንም ጸሎታቸውን የሚያመሳስለው አንድ ነገር አለ። ሰዎቹ በዛሬው ዓለም የተረሳ ወይም ችላ የተባለ ሆኖም ለጸሎት ስኬታማነት ቁልፍ የሆነውን ነገር ያውቁ ነበር። በሌላ አባባል ወደ ማን መጸለይ እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር።