በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ እንዳደረገው ሐዘንተኞችን አጽናኑ

ኢየሱስ እንዳደረገው ሐዘንተኞችን አጽናኑ

ኢየሱስ እንዳደረገው ሐዘንተኞችን አጽናኑ

የቢታንያ ነዋሪ የሆነው አልዓዛር በጠና ታሟል። በመሆኑም ማርታና ማርያም የተባሉት እህቶቹ የቅርብ ወዳጃቸው ወደሆነው ወደ ኢየሱስ መልእክተኞች ላኩ። ይሁን እንጂ አልዓዛር ሕመሙ ስለጠናበት ሕይወቱ አለፈ። ከቀብሩ በኋላ የማርታና የማርያም ወዳጆች እንዲሁም ጎረቤቶች እነሱን “ለማጽናናት” መጥተው ነበር። (ዮሐንስ 11:19) በመጨረሻም በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ኢየሱስ ቢታንያ ሲደርስ ወደሚወዳቸው ጓደኞቹ ሄደ። ኢየሱስ በዚህ ወቅት የተናገረውንና ያደረገውን ነገር መመርመራችን ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች እንዴት ማጽናናት እንደምንችል ለማወቅ ይረዳናል።

መሄድህ በራሱ እንደምታስብላቸው ያሳያል

ኢየሱስ ቢታንያ ለመድረስ የዮርዳኖስን ወንዝ አቋርጦ ከኢያሪኮ ወደ ቢታንያ በሚወስደው ጠመዝማዛና አቀበታማ መንገድ ለሁለት ቀናት ያህል መጓዝ ነበረበት። ማርታ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ገና ወደ መንደሩ ሳይገባ ልትቀበለው ቶሎ ብላ ወጣች። ማርያምም ኢየሱስ መምጣቱን ስታውቅ በፍጥነት ወደ እሱ ሄደች። (ዮሐንስ 10:40-42፤ 11:6, 17-20, 28, 29) ኢየሱስ ወደ ቢታንያ መሄዱ ሐዘን የደረሰባቸውን እህትማማቾች በጣም እንዳጽናናቸው ጥርጥር የለውም!

በዛሬው ጊዜም ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመጠየቅ መሄዳችን ሊያጽናናቸው ይችላል። ቲዮ የተባለውን የስድስት ዓመት ልጃቸውን በአደጋ ያጡት ስኮትና ሊዲያ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ እንዲህ ብለዋል፦ “የቤተሰቦቻችንና የጓደኞቻችን ድጋፍ በጣም ያስፈልገን ነበር። እነሱም ሌሊት ቢሆንም በቀጥታ ወደ ሆስፒታል መጡ።” እነዚህ ወዳጆቻቸው ምን አሏቸው? “በዚያ ሰዓት ምንም እንዲሉን አንፈልግም ነበር። በቦታው መገኘታቸው በራሱ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፤ እንደሚያስቡልን የሚያሳይ ነበር።”

ኢየሱስ፣ አልዓዛር በመሞቱ ሲያለቅሱ የነበሩትን ሰዎች ባየ ጊዜ ‘ውስጡ እንደተረበሸና እንባውን እንዳፈሰሰ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዮሐንስ 11:33-35, 38) ኢየሱስ በሰዎች ፊት እንባን ማፍሰስ ወንዶች ሊያደርጉት የማይገባ ነገር እንደሆነ አልተሰማውም። የሰዎቹ ሐዘንና ሥቃይ ተሰምቶት ነበር። ከዚህ ምን እንማራለን? ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመጠየቅ ስንሄድ ከሚያለቅሱ ጋር ማልቀስ ሊያሳፍረን አይገባም። (ሮም 12:15) በሌላ በኩል ደግሞ ሐዘንተኛው አልቅሶ እንዲወጣለት መገፋፋት እንዳለብህ አይሰማህ። አንዳንድ ሰዎች ለብቻቸው ሲሆኑ ማልቀስ ይመርጡ ይሆናል።

ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ አዳምጥ

ኢየሱስ ማርታንና ማርያምን ለማጽናናት ሲል ሊናገር ያሰበው ነገር ሊኖር ቢችልም መጀመሪያ እነሱ እንዲናገሩ አጋጣሚ እንደሰጣቸው ከሁኔታው መረዳት እንችላለን። (ዮሐንስ 11:20, 21, 32) ከማርታ ጋር ሲነጋገርም ጥያቄ ከጠየቃት በኋላ የምትሰጠውን መልስ አዳምጧል።—ዮሐንስ 11:25-27

ጥሩ አድማጭ መሆንህ ከልብ እንደምታስብላቸው ያሳያል። ያዘኑትን ለማጽናናት ጆሯችንን ሰጥተን ማዳመጥ ያስፈልገናል። ሐዘንተኞቹ ስሜታቸውን እንዲገልጹ የሚጋብዙ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ጥሩ አድማጮች መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ይሁንና ሐዘንተኞቹ ዝም ለማለት የሚፈልጉ ከሆነ እንዲያወሩ መገፋፋት አይኖርብህም። ምናልባት ደክሟቸው ማረፍ ፈልገው ይሆናል።

ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ስሜታቸው ሊደነዝዝ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንድን ነገር እየደጋገሙ ሊናገሩ ይችላሉ። ሌሎች ስሜታቸውን አውጥተው ይናገራሉ። ማርያምም ሆነች ማርታ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” ብለውታል። (ዮሐንስ 11:21, 32) በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አደረገ? በትዕግሥትና ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ አዳመጣቸው። ‘እንዲህ ሊሰማችሁ አይገባም’ እንደሚሉ ያሉ ሐሳቦችን ከመሰንዘር ተቆጥቧል። የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች ጥልቅ የሆነ የሐዘን ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል ተገንዝቦ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ልትጠይቅ ስትሄድ ምን መናገር እንዳለብህ እርግጠኛ ካልሆንክ “እንዴት ነህ?” እንደሚሉ ያሉ ስሜታቸውን እንዲገልጹ የሚጋብዙ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ጨዋታ መጀመር ትችላለህ። ከዚያም ሐዘንተኛው ሲናገር በጥሞና አዳምጠው። ሙሉ ትኩረትህንም ስጠው። እንዲሁም ሲያወራ ዓይን ዓይኑን እያየህ ስሜቱን ለመረዳት ሞክር።

የሐዘንተኛውን ስሜት መረዳት ቀላል አይደለም። ከላይ የተጠቀሰችው ሊዲያ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ‘የሚያስፈልጋቸው ነገር እንደተለወጠ’ ገልጻለች። “አንዳንድ ጊዜ ሊያጽናኑን የመጡ ሰዎች እያሉ ስቅስቅ ብለን እናለቅስ ነበር። በዚህ ጊዜ ሌሎች እንዲያበረታቱን እንፈልግ ነበር። ጓደኞቻችን ስሜታችንን ለመረዳት የቻሉትን ያህል ጥረዋል።”

ኢየሱስም ያደረገው ይህንኑ ነው። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ‘ጭንቀትና ሕመም’ እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 6:29) ኢየሱስ የሁለቱን እህትማማቾች ሁኔታ በማገናዘብ እሱን ሲያገኙት ለተናገሩት ነገር የተለያየ መልስ ሰጥቷል። ማርታ ሐሳቧን አውጥታ ትናገር ስለነበር ኢየሱስም አዋርቷታል። ማርያም ደግሞ ስታለቅስ ስለነበር ከእሷ ጋር ብዙ አላወራም። (ዮሐንስ 11:20-28, 32-35) እሱ ከተወው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን? ሐዘንተኛው የሚፈልገውን ነገር እንዲያወራ ዕድል መስጠቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ የተሰማውን ሐዘን ሲገልጽ ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆንህ በጣም ሊያጽናናው ይችላል።

ፈዋሽ የሆኑ ቃላት

ማርያምና ማርታ ኢየሱስን “አንተ እዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ” ሲሉት ኢየሱስ ጥፋቱ የእሱ ብቻ እንዳልሆነ ለመናገር አልሞከረም፤ ወይም ደግሞ በተናገሩት ነገር ቅር አልተሰኘም። ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት የሚያጽናና መልስ ሰጥቷታል። (ዮሐንስ 11:23) ኢየሱስ በእነዚህ ጥቂት ቃላት አማካኝነት የወደፊቱን ጊዜ አሻግራ እንድትመለከት የረዳት ከመሆኑም ሌላ ተስፋ መኖሩን በደግነት አስታውሷታል።

ሐዘን የደረሰበትን ሰው ስታነጋግር አጠር ያለ ቢሆንም እንኳ ከልብ የመነጨ የሚያጽናና ሐሳብ መሰንዘርህ ለግለሰቡ ትልቅ ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል አትዘንጋ። ከግለሰቡ ጋር ስታወራ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ልታካፍለው ትችላለህ፤ አሊያም እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች ጽፈህ ልትሰጠው ትችላለህ። ግለሰቡ ደብዳቤዎችንና ካርዶችን ደጋግሞ ማንበብ ስለሚችል ሐዘን ከደረሰበት ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ ሊያጽናኑት ይችላሉ። ካት፣ ባለቤቷ ቦብ ከሞተ ከዘጠኝ ወራት በኋላ በሐዘኑ ጊዜ የደረሷትን ካርዶች በሙሉ በድጋሚ አነበበቻቸው። “እንዲያውም እነዚህ ካርዶች ይበልጥ ያጽናኑኝ በዚያ ጊዜ ነበር” ብላለች።

ታዲያ ሐዘንተኛውን ለማጽናናት በምትጽፈው ማስታወሻ ላይ ምን ነጥቦችን ማካተት ትችላለህ? ስለ ሟቹ ይኸውም አብራችሁ ስላደረጋችኋቸው ነገሮች ወይም ግለሰቡ ስለነበረው ግሩም ባሕርይ ልትጽፍ ትችላለህ። ካት እንዲህ ትላለች፦ “ስለ ቦብና ስለ ባሕርዩ የሚገልጹ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ሐሳቦችን ሳነብ በአንድ በኩል ደስ ይለኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንባዬ ይመጣል። ከእሱ ጋር የተያያዙ የሚያስቁ አጋጣሚዎችን ሳነብ ፈገግ እላለሁ፤ እንዲሁም አብረን ያሳለፍነውን አስደሳች ሕይወት አስታውሳለሁ። በጣም ከምወዳቸው ካርዶች ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የያዙ ናቸው።”

የሚያስፈልጋቸውን እገዛ አድርግላቸው

ኢየሱስ የአልዓዛርን ቤተሰብ ለመርዳት እኛ ልናደርገው የማንችለውን ነገር አድርጓል። አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል። (ዮሐንስ 11:43, 44) እኛ ደግሞ ምግብ ማዘጋጀትን፣ እንግዶችን ማስተናገድን፣ ልብስ ማጠብን፣ ትንንሽ ልጆችን መጠበቅን፣ መላላክን ወይም መጓጓዣ ማቅረብን የመሳሰሉ ነገሮች በማድረግ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ማበርከት እንችላለን። ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች፣ እውነተኛ ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን ቀላል የሚመስሉ ተግባሮች ስናከናውን በጣም እንደሚደሰቱ ጥርጥር የለውም።

ሐዘንተኞች ብቻቸውን መሆን ሊፈልጉ እንደሚችሉ እሙን ነው። ያም ቢሆን እነሱ እስከሚጠሩህ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ አንተ ቅድሚያውን ወስደህ አብረሃቸው ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አድርግ። ልጇን በሞት ያጣች አንዲት እናት “ሐዘን የደረሰበት ሰው በዚህ ጊዜ መጽናናት አለበት ብሎ ገደብ ማበጀት አይቻልም፤ ሰዎች ከሐዘናቸው ለመጽናናት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይለያያል” ብላለች። አንዳንዶች፣ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች የጋብቻ በዓል የሚውልበትን ቀን ወይም የሚወዱት ሰው የሞተበትን ቀን አስታውሰው አንድ ነገር ለማድረግ ይሞክራሉ። እንዲህ ባሉት ጊዜያት አብረሃቸው በመሆን በችግራቸው ጊዜ የሚደርስ እውነተኛ ወዳጅ ልትሆንላቸው ትችላለህ።—ምሳሌ 17:17

ኢየሱስ ሌሎችን ለማጽናናት ካደረጋቸው ነገሮች መካከል ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ተስፋ ይገኝበታል፤ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፍ ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 11:11) ኢየሱስ ሙታን እንደሚነሱ ለተከታዮቹ አረጋግጦላቸዋል። ማርታንም “ይህን ታምኛለሽ?” በማለት ጠይቋታል። እሷም “አዎ፣ ጌታ ሆይ” በማለት መልሳለች።—ዮሐንስ 11:24-27

አንተስ ኢየሱስ ሙታንን እንደሚያስነሳ ታምናለህ? ከሆነ ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች ይህን ውድ ተስፋ ንገራቸው። የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማድረግ አግዛቸው። የምትናገራቸው ቃላትና የምታደርጋቸው ነገሮች ሐዘንተኞቹን ያጽናኗቸዋል።—1 ዮሐንስ 3:18

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፔሪያ

የዮርዳኖስ ወንዝ

ኢያሪኮ

ቢታንያ

የጨው ባሕር

ኢየሩሳሌም

ሰማርያ