በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከፈለግኸው ታገኘዋለህ”

“ከፈለግኸው ታገኘዋለህ”

ወደ አምላክ ቅረብ

“ከፈለግኸው ታገኘዋለህ”

1 ዜና መዋዕል 28:9

አምላክን ታውቀዋለህ? የዚህ ጥያቄ መልስ የምናስበውን ያህል ቀላል አይደለም። አምላክን ማወቅ ሲባል የእሱን ፈቃድና መንገዶቹን ጠንቅቆ ማወቅን ያካትታል። እንዲህ በማድረግ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት የምንችል ሲሆን ይህ ደግሞ መላ ሕይወታችንን ይነካል። በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና መመሥረት ይቻላል? የሚቻል ከሆነስ እንዴት? በ1 ዜና መዋዕል 28:9 ላይ የሚገኘውና ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ሰለሞን የሰጠውን ምክር የያዘው ዘገባ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ዳዊት በእስራኤል ላይ ለ40 ዓመታት የገዛ ሲሆን ሕዝቡም በእሱ አገዛዝ ሥር ብልጽግና አግኝቷል። በጣም ወጣት የሆነው ልጁ ሰለሞን፣ በቅርቡ እሱን ተክቶ ሊነግሥ ነው። (1 ዜና መዋዕል 29:1) ታዲያ ዳዊት ከመሞቱ በፊት ለልጁ ምን ምክር ይሰጠው ይሆን?

ዳዊት አምላክን በማገልገል ካካበተው ብዙ ተሞክሮ በመነሳት “ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ . . . የአባትህን አምላክ ዕወቅ” በማለት ምክሩን ጀመረ። ዳዊት እንዲህ ሲል ከጭንቅላት እውቀት የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልግ እየተናገረ መሆን አለበት። ሰለሞን ቀድሞውንም ቢሆን የዳዊት አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ነበር። አንድ ሦስተኛ የሚያህለው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ተጽፎ ስለነበር ሰለሞን እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ አምላክ የሚናገሩትን ነገር እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ምሑር እንደተናገሩት “ማወቅ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “በጣም የቀረበ ትውውቅ ያላቸው ወዳጆችን” ሊያመለክት ይችላል። አዎን፣ ዳዊት ልጁ ሰለሞን እሱ ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር እንዲያደርግ ይኸውም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲመሠርት ፈልጎ ነበር።

እንዲህ ያለው የጠበቀ ዝምድና በሰለሞን አመለካከትና ሕይወቱን በሚመራበት መንገድ ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት። ዳዊት “[አምላክን] በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው” በማለት ልጁን አሳስቦታል። ዳዊት ይሖዋን እንዲያገለግል ለልጁ የነገረው አምላክን እንዲያውቅ ካሳሰበው በኋላ እንደሆነ ልብ በል። አንድ ሰው አምላክን በደንብ ሲያውቅ እሱን ለማገልገል ይነሳሳል። ይሁንና አምላክ፣ በተከፈለ ልብ ይኸውም እያመነታን ወይም ደግሞ በመንታ ልብ ማለትም ግብዝነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንድናገለግለው አይፈልግም። (መዝሙር 12:2፤ 119:113 NW) ዳዊት፣ አምላክን በሙሉ ልብና በፈቃደኝነት እንዲያገለግለው ልጁን አሳስቦታል።

ዳዊት ልጁ በትክክለኛ አስተሳሰብና የልብ ዝንባሌ ተገፋፍቶ አምላክን እንዲያመልክ ያሳሰበው ለምንድን ነው? ዳዊት “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ” እንደሆነ ተናግሯል። ሰለሞን አባቱን ዳዊትን ለማስደሰት ሲል አምላክን ማገልገል የለበትም። ይሖዋ የሚፈልገው እሱን ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ነው።

ታዲያ ሰለሞን የአባቱን ምሳሌ በመከተል ወደ ይሖዋ ይቀርብ ይሆን? ይህ በራሱ ላይ የተመካ ነው። ዳዊት ለልጁ “ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውከው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል” ብሎታል። ሰለሞን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖረው ከፈለገ ይሖዋን ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት። *

የዳዊት አባታዊ ምክር እንደሚያረጋግጥልን ይሖዋ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንድንመሠርት ይፈልጋል። እንዲህ ዓይነቱን የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ከፈለግን ‘እሱን መፈለግ’ ማለትም እሱን በደንብ ለማወቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቅ መመርመር ይኖርብናል። አምላክን ማወቃችን እሱን በሙሉ ልብና በፈቃደኝነት እንድናገለግለው ሊያነሳሳን ይገባል። ይሖዋ በዚህ መልኩ እንድናገለግለው ይፈልጋል፤ ደግሞም እንዲህ ያለው አምልኮ ይገባዋል።—ማቴዎስ 22:37

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የሚያሳዝነው ሰለሞን አምላክን በፍጹም ልቡ ማገልገል ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ታማኝ ሆኖ አልቀጠለም።—1 ነገሥት 11:4