ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ
4ኛው ቁልፍ
ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው? ጓደኞቻችን ባለን የምንረካ ሰዎች እንድንሆን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም የማንረካ ሰዎች እንድንሆን ሊያደርጉን ይችላሉ። የጓደኞቻችን አስተሳሰብም ሆነ የሚናገሩት ነገር ለሕይወት በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።—1 ቆሮንቶስ 15:33
ለምሳሌ ያህል፣ የከነዓንን ምድር ሰልለው ስለተመለሱ 12 ሰዎች የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ተመልከት። አብዛኞቹ “ስለ ሰለሏት ምድር በእስራኤላውያን መካከል . . . መጥፎ ወሬ አሠራጩ።” እንደዚያም ሆኖ ከሰዎቹ መካከል ሁለቱ ከነዓንን ‘እጅግ ሲበዛ መልካም ምድር’ በማለት ጠርተዋታል። ይሁን እንጂ የአሥሩ ሰላዮች አፍራሽ አስተሳሰብ በሕዝቡ መካከል ተዛመተ። ዘገባው ‘ማኅበረሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ። እስራኤላውያን በሙሉ አጕረመረሙ’ በማለት ይናገራል።—ዘኍልቍ 13:30 እስከ 14:9
በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች “የሚያጉረመርሙና ስለ ኑሯቸው የሚያማርሩ” ናቸው። (ይሁዳ 16) በምንም ነገር የማይረኩ ሰዎችን ወዳጆቻችን አድርገን ባለን ረክተን እንኖራለን ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።
ምን ማድረግ ትችላለህ? ከጓደኞችህ ጋር የምታደርገውን ጭውውት አጢነው። ጓደኞችህ ብዙውን ጊዜ ስላላቸው ነገር በጉራ ይናገራሉ? ወይስ ስለሌላቸው ነገር ዘወትር ያማርራሉ? አንተስ ምን ዓይነት ጓደኛ ነህ? ጓደኞችህን ለማስቀናት ትጣጣራለህ? ወይስ ባላቸው ነገር እንዲረኩ ታበረታታቸዋለህ?
ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ የነበረው ዳዊትና የሳኦል ልጅ ዮናታን የተዉትን ምሳሌ ተመልከት። ዳዊት ተሰዶ በምድረ በዳ ይኖር ነበር። ንጉሥ ሳኦል፣ ዳዊት ንግሥናውን እንደሚቀማው ስለተሰማው ዳዊትን ለመግደል ይፈልግ ነበር። ዮናታን በአባቱ እግር ተተክቶ የመንገሥ መብት የነበረው ቢሆንም የዳዊት የቅርብ ወዳጅ ሆነ። ዮናታን፣ ዳዊት ከሳኦል ቀጥሎ ንጉሥ እንዲሆን አምላክ እንደመረጠው የተረዳ ከመሆኑም ሌላ ባለው ረክቶ በመኖር ከጓደኛው ጎን ቆሟል።—1 ሳሙኤል 19:1, 2፤ 20:30-33፤ 23:14-18
አንተም ባላቸው ነገር ለመርካት የሚጥሩና መልካሙን ሁሉ የሚመኙልህ ወዳጆች ያስፈልጉሃል። (ምሳሌ 17:17) እርግጥ ነው፣ እንደነዚህ ዓይነት ጓደኞችን ለማፍራት አንተ ራስህ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት ይኖርብሃል።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጓደኞችህ ባለህ እንድትረካ ያበረታቱሃል? ወይስ ምንም የማትረካ ሰው እንድትሆን እያደረጉህ ነው?