በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች

ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች

ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች

የቱንም ያህል ወደ ሰማይ ብታንጋጥጥ መንፈሳዊ አካላትን ማየት አትችልም። ድምፃቸውንም ቢሆን መስማት አትችልም። ያም ሆኖ መንፈሳዊ አካላት እንዳሉ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። መንፈሳዊ አካላት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታና ኃይል ያላቸው ከመሆኑም ሌላ የየራሳቸው ስምና ባሕርይ አላቸው። አንዳንዶቹ ሊረዱን ሌሎቹ ደግሞ ሊጎዱን ይፈልጋሉ። ሁሉም መንፈሳዊ አካላት በትኩረት ይከታተሉናል።

እውነተኛው አምላክ ራሱም መንፈስ ነው። (ዮሐንስ 4:24) ይህ አምላክ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ሐሰተኛ አማልክት ተለይቶ እንዲታወቅ የሚያደርገው ልዩ የሆነ ስም አለው። ስሙም ይሖዋ ነው። (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ታላቅ ነውና፤ ውዳሴም የሚገባው ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል። የሕዝብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ ናቸው፤ ብርታትና ውበትም በመቅደሱ ውስጥ አሉ።”—መዝሙር 96:4-6

ስለ እውነተኛው አምላክ የሚገልጹ ራእዮች

መጽሐፍ ቅዱስ “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” ይላል። (ዮሐንስ 1:18) ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው ስለ ቀለማት መረዳት እንደማይችል ሁሉ እኛም ስለ ይሖዋ ገጽታና ግርማ ሞገስ መረዳት ከአቅማችን በላይ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ጥሩ አስተማሪ ውስብስብ የሆኑ ነገሮችን ለተማሪዎቹ ለማስረዳት በሚያውቋቸው ነገሮች እንደሚጠቀም ሁሉ አምላክም ልናያቸው ስለማንችላቸው ነገሮች ለማስረዳት ልናያቸው በምንችላቸው ነገሮች ተጠቅሟል፤ ይህንንም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። ይሖዋ በመንፈሱ ተጠቅሞ በጥንት ዘመን ለነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹ ራእዮችን ያሳያቸው ሲሆን እነዚህ ራእዮች፣ በሰማይ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል በአእምሯችን መሳል እንድንችል እንዲሁም በዚያ ከሚኖሩት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደሚኖረን ለመረዳት ያስችሉናል።

ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል ከተመለከታቸው ራእዮች በአንዱ ላይ የይሖዋ ታላቅ ክብር ከእሳት፣ ከደማቅ ብርሃን፣ ከሰንፔርና ከቀስተ ደመና ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል። በሌላ ራእይ ላይ ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ይሖዋን በዙፋን ላይ ተቀምጦ የተመለከተው ሲሆን “ገጽታው እንደ ኢያስጲድና ቀይ ቀለም እንዳለው የከበረ ድንጋይ” መሆኑን ገልጿል፤ አክሎም “በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር” ብሏል። እንደነዚህ ያሉት መግለጫዎች ይሖዋ ያለበት ቦታ ልዩና አስደናቂ ውበት የተላበሰ እንዲሁም አስደሳችና እርጋታ የሰፈነበት እንደሆነ ይጠቁሙናል።—ራእይ 4:2, 3፤ ሕዝቅኤል 1:26-28

ነቢዩ ዳንኤልም ይሖዋን በራእይ ያየው ሲሆን የተመለከተውን ሲገልጽ “እልፍ ጊዜ እልፍ [መላእክት] በፊቱ [በይሖዋ] ቆመዋል” በማለት ጽፏል። (ዳንኤል 7:10) ይህ እንዴት አስደናቂ ነገር ነው! በራእይም እንኳ ቢሆን አንድን መልአክ ማየት በጣም የሚያስደምም ነው፤ ፍጹማን የሆኑ እልፍ አእላፋት መላእክትን መመልከትማ ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ያዳግታል!

መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 400 ያህል ጊዜ የተጠቀሱ ሲሆን ከመካከላቸውም ሱራፌልና ኪሩቤል ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መልአክ” ተብለው የተተረጎሙት ሁለቱም የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት “መልእክተኛ” የሚል ፍቺ አላቸው። በመሆኑም መላእክት አንዳቸው ለሌላው መልእክት የሚያስተላልፉ ሲሆን በጥንት ጊዜ ለሰዎችም መልእክት አስተላልፈዋል። መላእክት ከዚህ ቀደም ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አይደሉም። ይሖዋ እነዚህን መንፈሳዊ ፍጥረታት የፈጠራቸው ሰውን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር።—ኢዮብ 38:4-7

ዳንኤል በተመለከተው ራእይ ላይ እልፍ አእላፋት መላእክት አንድን አስደናቂ ክንውን ለማየት ተሰብስበው ነበር። ዳንኤል በራእዩ ላይ “የሰውን ልጅ የሚመስል” ወደ ይሖዋ ዙፋን ሲቀርብ ተመለከተ፤ ከዚያም “ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት።” (ዳንኤል 7:13, 14) “የሰውን ልጅ የሚመስል” የተባለውና በመላው ምድር ላይ እንዲገዛ ሥልጣን የተሰጠው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን እሱም በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። በቅርቡ ኢየሱስ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ አስወግዶ መላውን ምድር የሚገዛ ከመሆኑም ሌላ በሽታን፣ ሐዘንን፣ ጭቆናን፣ ድህነትንና ሞትንም ጭምር ያስወግዳል።—ዳንኤል 2:44

ኢየሱስ ሥልጣን መያዙ የሰው ልጆች መልካም ነገር እንዲያገኙ ለሚመኙት ታማኝ የሆኑ እልፍ አእላፋት መላእክት ታላቅ ደስታ እንዳመጣላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የሚያሳዝነው ግን የተደሰቱት ሁሉም መንፈሳዊ ፍጥረታት አይደሉም።

የአምላክና የሰው ጠላቶች

በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ ከመላእክት አንዱ የመመለክ ምኞት ስላደረበት በይሖዋ ላይ በማመፅ ራሱን ሰይጣን (“ተቃዋሚ” ማለት ነው) አደረገ። የክፋት ተምሳሌት የሆነው ሰይጣን፣ ሁለንተናው ፍቅር የሆነው የይሖዋ ዋነኛ ተቃዋሚ ሆነ። ሌሎች መላእክትም ከሰይጣን ጋር በማበር ዓመፁ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ፍጥረታት አጋንንት በማለት ይጠራቸዋል። አጋንንትም እንደ ሰይጣን የሰው ልጆች ጨካኝ ጠላቶች ናቸው። በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራና ሥቃይ፣ የፍትሕ መዛባት፣ በሽታ፣ ድህነት እንዲሁም ጦርነት አብዛኛውን ጊዜ መንስኤው የአጋንንት ተጽዕኖ ነው።

በብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ስለ ሰይጣን ማውራት ጊዜ ያለፈበት ነገር ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የኢዮብ መጽሐፍ ስለዚህ ዓመፀኛ መልአክ ባሕርይና ዝንባሌ ለማወቅ ይረዳናል። የኢዮብ መጽሐፍ “አንድ ቀን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ በመጡ ጊዜ፣ ሰይጣንም መጥቶ በመካከላቸው ቆመ” በማለት ይናገራል። ከዚያ በኋላ በተደረገው ውይይት ላይ ሰይጣን፣ ኢዮብ የተባለው ሰው አምላክን የሚያገለግለው ከአምላክ ለሚያገኘው ጥቅም ሲል እንደሆነ በመግለጽ ወነጀለው። ሰይጣን በኢዮብ ላይ የሰነዘረው ክስ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል የኢዮብን ከብቶችና አሥር ልጆች በመግደል ታላቅ መከራ አመጣበት። ከዚያም ሰይጣን ኢዮብን ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በክፉ ቁስል መታው። ይሁንና ሰይጣን በኢዮብ ላይ የሰነዘራቸው ጥቃቶች በሙሉ ክሱ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ አልቻሉም።—ኢዮብ 1:6-19፤ 2:7

ይሖዋ ሰይጣንን ይህን ለሚያህል ረጅም ጊዜ የታገሠበት በቂ ምክንያት ቢኖረውም ለዘላለም አይታገሠውም። በቅርቡ ዲያብሎስ ይወገዳል። ለዚህም መቅድም የሆኑ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን ሁኔታው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል፤ በሌላ በምንም መንገድ ልናየው የማንችለው አንድ ትልቅ ክንውን የመንፈሳዊው ዓለም መጋረጃ የተገለጠ ያህል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተብራርቷል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና [ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ] መላእክቱ ከዘንዶው [ከሰይጣን] ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤ ሆኖም ዘንዶው ማሸነፍ አልቻለም፤ ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተወረወረ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ።”—ራእይ 12:7-9

ሰይጣን “መላውን ዓለም እያሳሳተ” እንደሆነ መገለጹን ልብ በል። ሰዎችን ከይሖዋና ከቃሉ ለማራቅ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን በማስፋፋት እያሳሳታቸው ነው። ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች አንዱ፣ ሁሉም ሰው ሲሞት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖር ይቀጥላል የሚል ነው። ይህ ሐሳብ በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ይሰማል። ለምሳሌ በአፍሪካና በእስያ ብዙዎች፣ ሰዎች ሲሞቱ የቀድሞ አባቶቻቸው ወደሚኖሩበት መንፈሳዊ ዓለም እንደሚሄዱ ያምናሉ። ስለ መንጽሔና ሲኦል የሚገልጹት ትምህርቶችም ሰው ከሞተ በኋላ መኖሩን ይቀጥላል በሚለው እምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

ሰው ከሞተ በኋላ በሰማይ መኖሩን ይቀጥላል?

ይሁንና በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚያምኑት ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ? አንዳንድ ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱ መሆኑ እውነት ቢሆንም እነዚህ ሰዎች በሞት ካንቀላፉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንጻር ቁጥራቸው ጥቂት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ 144,000 ሰዎች ‘ከምድር እንደሚዋጁ’ እንዲሁም በምድር ላይ “ካህናት” እና “ነገሥታት ሆነው” እንደሚያገለግሉ ይገልጻል። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3) እነዚህ ሰዎች የሰው ልጅ ከተባለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው በመሆን በሰማይ የሚገኘውን መስተዳድር ማለትም የአምላክን መንግሥት ያቋቁማሉ። ይህ መንግሥት ሰይጣንንና አጋንንቱን በማስወገድ ምድርን ገነት ያደርጋታል። ከሞቱት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ወደፊት ትንሣኤ የሚያገኙ ሲሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል።—ሉቃስ 23:43

እስከ አሁን የተመለከትናቸውን ነጥቦች ስናጠቃልላቸው፣ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እልፍ አእላፋት መንፈሳዊ አካላት ይኖራሉ። የሁሉም የበላይ የሆነውና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ነው። እሱን የሚያገለግሉ እልፍ አእላፋት ታማኝ መላእክት አሉ። በሰይጣን የሚመሩት ሌሎች መላእክት ግን በይሖዋ ላይ ዓምፀው ሰዎችን ለማሳሳት እየጣሩ ነው። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ በሰማይ የተዘጋጀላቸውን ልዩ ኃላፊነት ለመቀበል ከምድር ‘ተዋጅተዋል’ ወይም ተመርጠዋል። እነዚህን ነጥቦች በአእምሯችን በመያዝ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ማንን ማነጋገር እንደምንችልና ይህን ማድረግ ስለምንችልበት መንገድ እስቲ እንመልከት።