በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

እስራኤል ረጅም የበጋ ወቅት ያላት እንደመሆኑ መጠን በጥንት ጊዜ ነዋሪዎቿ ውኃ ለማግኘት ምን ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር?

በእስራኤል ከጥቅምት እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራት ዝናብ ስለሚጥል አንዳንድ ጊዜ ጎርፍ ወደ ሸለቆዎች ይፈስ ነበር። በበጋ ወቅት ይህ ውኃ በአብዛኛው የሚደርቅ ከመሆኑም በላይ ለወራት ዝናብ ላይጥል ይችላል። ታዲያ በጥንት ጊዜ የነበሩ ሰዎች በቋሚነት ውኃ የሚያገኙት እንዴት ነበር?

በዚያ ዘመን ሰዎች ይህን ችግር ለማስወገድ ቦይ በመቆፈር ከኮረብታ የሚወርደው ጎርፍ በውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች ውስጥ እንዲገባ ያደርጉ ነበር። የቤት ጣሪያዎች ዘቅዘቅ ተደርገው ስለሚሠሩ ከጣሪያዎቹ ላይ የሚፈሰው የዝናብ ውኃ ወደ እነዚህ ጉድጓዶች ይገባ ነበር። በርካታ ቤተሰቦች የራሳቸው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ስለሚኖራቸው ጥማቸውን ለማርካት ከዚህ ጉድጓድ ውኃ መቅዳት ይችሉ ነበር።—2 ነገሥት 18:31፤ ኤርምያስ 6:7

ከዚህም በላይ እስራኤላውያን ውኃ ለማግኘት ምንጮችን ይጠቀሙ ነበር። በተራራማ አካባቢዎች የዝናብ ውኃ መሬት ውስጥ ሰርጎ ከገባ በኋላ ውኃ የማያሳልፍ ዐለታማ አካባቢ ሲደርስ እንደምንጭ ሆኖ ይፈልቃል። እስራኤል ውስጥ ዓይንሳሚስ፣ ዓይንሮ ጌል እና ዓይንጋዲ እንደሚባሉ ያሉ ቦታዎች መኖራቸው ብዙውን ጊዜ መንደሮች ምንጭ (በዕብራይስጥ ዓይ) አካባቢ እንደሚመሠረቱ ያሳያል። (ኢያሱ 15:7, 62) ኢየሩሳሌም ከተቦረቦረ ዐለት በተሠራ ቱቦ አማካኝነት የምንጭ ውኃ ታገኝ ነበር።—2 ነገሥት 20:20

ምንጭ በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ የከርሰ ምድር ውኃ ለማግኘት በቤርሳቤህ እንደነበረው ያሉ ጉድጓዶች (በዕብራይስጥ ቤር) ይቆፈሩ ነበር። (ዘፍጥረት 26:32, 33) አንድሬ ሹራኪ የተባሉ ደራሲ “ችግሩን ለመፍታት [እስራኤላውያን] የቀየሷቸው ዘዴዎች ዛሬም እንኳ በጣም የሚያስገርሙ ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

አብራም (አብርሃም) የኖረው በምን ዓይነት ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል?

አብራምና ሚስቱ የሚኖሩት የበለጸገች የከለዳውያን ከተማ በነበረችው በዑር ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ይህችን ከተማ ለቀው በድንኳን መኖር ጀመሩ። (ዘፍጥረት 11:31፤ 13:12) እነዚህ ሰዎች ይህን ለውጥ ማድረጋቸው ምን መሥዋዕትነት መክፈል ጠይቆባቸው ሊሆን እንደሚችል እስቲ እንመልከት።

ሊዮናርድ ዉሊ ከ1922 እስከ 1934 ባሉት ዓመታት ባደረጉት የመሬት ቁፋሮ ዑርን ማግኘት ችለዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ይህ ቦታ ኢራቅ ውስጥ ይገኛል። እኚህ ሰው በቁፋሮ ካገኟቸው ሕንፃዎች መካከል በጡብ የተሠሩ 73 የሚያህሉ ቤቶች ይገኙበታል። እያንዳንዱ ቤት በድንጋይ የተነጠፈ ኮሪደር ያለው ሲሆን የቤቱ ክፍሎች የተሠሩት በዚህ ኮሪደር ዙሪያ ነበር። ይህ ኮሪደር ወደ መሃል ዘቅዘቅ ብሎ የተሠራ ሲሆን ከየአቅጣጫው የሚመጣው ፍሳሽ በቱቦ አማካኝነት በቀላሉ ወደ ውጭ ይወጣል። ትልልቆቹ ቤቶች የእንግዳ ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን እነዚህ ክፍሎች መጸዳጃ ቤት አላቸው። ከታች ካሉት ክፍሎች ውስጥ ምድጃዎች ያሏቸው ኩሽናዎችና ባሪያዎች የሚያድሩባቸው መኝታ ክፍሎች ይገኙበታል። የቤተሰቡ አባላት የሚኖሩት ግን ፎቅ ላይ ባሉት ክፍሎች ውስጥ ነበር። በደረጃዎቹ አማካኝነት ወደ ፎቅ ሲወጣ በፎቁ ላይ ባሉት ክፍሎች ዙሪያ የእንጨት በረንዳ አለ።

ዉሊ “በድንጋይ የተነጠፈ ክፍት ቦታ፣ የተለሰኑ ነጭ ግድግዳዎች፣ የራሱ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ . . . አሥር ወይም ከዚያ የሚበልጡ ክፍሎች ያሉት . . . ቤት መኖሩ በዚያን ጊዜ የነበረው የኑሮ ደረጃ ከፍተኛ እንደነበረ ያመለክታል” ብለዋል። “እንዲህ ባሉ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩት መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው፣ የሱቅ ባለቤቶች፣ አነስተኛ ነጋዴዎች፣ ጸሐፍት እና የመሳሰሉት ነበሩ።”

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤል ውስጥ በሃርቮት ሜዛዳ የሚገኝ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Masada National Park, Israel Nature and Parks Authority

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም በኖረበት ዘመን የነበረውን የቤት አሠራር የሚያሳይ ንድፍ

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Drawing: A. S. Whitburn