በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን ትከሉ

በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን ትከሉ

በሜክሲኮ የምትኖር ሎይዳ * የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “በትምህርት ቤት ኮንዶም ይታደላል፤ በመሆኑም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ኮንዶም እስከተጠቀሙ ድረስ የፆታ ግንኙነት ቢያደርጉ ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል።”

በጃፓን የምትኖር ኖቡኮ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ከሴት ጓደኛው ጋር ብቻውን ቢሆን ምን እንደሚያደርግ ልጄን ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ ‘እኔ እንጃ፣ ምን እንደማደርግ አላውቅም’ የሚል ነበር።”

ልጆቻችሁ ሕፃናት ሳሉ በቤት ውስጥ ለአደጋ የሚያጋልጣቸው ነገር እንዳይኖር ጥንቃቄ ታደርጉ ነበር? ምናልባትም ሶኬቶችን ሸፍናችሁ፣ ስለታማ የሆኑ ነገሮችን ደብቃችሁ እንዲሁም ከደረጃ ላይ እንዳይወድቁ መከታ አድርጋችሁ ሊሆን ይችላል፤ ይህን ሁሉ ያደረጋችሁት ልጆቻችሁን ከአደጋ ለመጠበቅ ስትሉ ነው።

ልጃችሁ ሲጎረምስ ግን እሱን ከአደጋ መጠበቅ እንደዚያን ጊዜ ቀላል አይደለም! አሁን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይበልጥ ያሳስቧችኋል፦ ‘ልጄ የብልግና ምስሎችን ያይ ይሆን?’ ‘ሴቷ ልጄ የፆታ ስሜት በሚቀሰቅስ መንገድ ፎቶ ተነስታ በሞባይል ትልክ ይሆን?’ ይበልጥ የሚያስፈራው ጥያቄ ደግሞ ‘ልጄ የፆታ ግንኙነት ማድረግ ጀምሮ ወይም ጀምራ ይሆን?’ የሚለው ነው።

መፈናፈኛ ማሳጣት መፍትሔ ይሆናል?

አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን እግር በእግር እየተከተሉ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን በመቃኘት 24 ሰዓት ሊቆጣጠሯቸው ይሞክራሉ። ከጊዜ በኋላ ግን ብዙዎቹ ወላጆች እንዲህ ዓይነት የማያፈናፍን ቁጥጥር ማድረጋቸው ልጆቻቸው ድብቅ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ይገነዘባሉ። ልጆቹ ወላጆቻቸው የማይፈልጉትን ባሕርይ በመደበቅ ረገድ የተካኑ ይሆናሉ።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጥብቅ ቁጥጥር መፍትሔ አይደለም። ይሖዋ አምላክ ራሱ ፍጥረታቱ እንዲታዘዙት ለማድረግ ይህን ዘዴ አልተጠቀመም፤ እናንተ ወላጆችም እንዲህ ማድረግ የለባችሁም። (ዘዳግም 30:19) ታዲያ ልጆቻችሁ ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?—ምሳሌ 27:11

የመጀመሪያው እርምጃ ከትንሽነታቸው ጀምሮ ከልጆቻችሁ ጋር የመወያየት ልማድ ማዳበር ነው። * (ምሳሌ 22:6) በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ ሲሆኑም ከእነሱ ጋር ማውራታችሁን ቀጥሉ። ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ለልጆቻችሁ አስተማማኝ መመሪያ መስጠት ይኖርባችኋል። አሊሻ የተባለች በብሪታንያ የምትኖር አንዲት ወጣት “ብዙ ሰዎች የፆታ ግንኙነትን አስመልክቶ ከጓደኞቻችን ጋር ብቻ ማውራት እንደምንመርጥ ይሰማቸዋል፤ ይህ ግን ፈጽሞ ትክክል አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን መረጃ ከወላጆቻችን ብናገኝ ደስ ይለናል። እነሱ በሚነግሩን ነገር እንተማመናለን።”

የሥነ ምግባር እሴቶች ያላቸው ጥቅም

ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ልጅ እንዴት እንደሚወለድ ከማወቅ ባለፈ ስለ ፆታ ሰፊ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ልጆች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን” ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። (ዕብራውያን 5:14) በአጭሩ፣ ልጆች የፆታ ግንኙነትን አስመልክቶ በጥብቅ የሚያምኑበት ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ሊኖራቸውና ከአቋማቸው ጋር ተስማምተው ሊኖሩ ይገባል። ታዲያ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን መትከል የምትችሉት እንዴት ነው?

በመጀመሪያ የራሳችሁን የሥነ ምግባር አቋም ፈትሹ። ለምሳሌ በጋብቻ ባልተሳሰሩ ሁለት ሰዎች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ማለትም ዝሙት ትክክል እንዳልሆነ በጥብቅ ታምኑ ይሆናል። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ልጆቻችሁም ቢሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አቋም ያውቁ አልፎ ተርፎም ይህን እምነታችሁን የሚደግፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይጠቅሱ ይሆናል። ጥያቄ ቢቀርብላቸው እንኳ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነት ትክክል እንዳልሆነ አፋቸውን ሞልተው ይናገሩ ይሆናል።

ይሁንና በዚህ ብቻ መርካት የለባችሁም። ሴክስ ስማርት የተባለው መጽሐፍ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው ስለ ፆታ ግንኙነት ባላቸው አቋም እንደሚስማሙ የሚናገሩት ለአፋቸው ያህል እንደሆነ ታዝቧል፤ መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፦ “የራሳቸውን የሥነ ምግባር አቋም በተመለከተ እርግጠኞች እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ያልጠበቁት ሁኔታ ሲያጋጥማቸውና ‘ገደቡ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ’ ለመወሰን አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ግራ ሊጋቡና ከባድ ችግር ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ።” ይህ ሁኔታ የሥነ ምግባር እሴቶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ በግልጽ ያሳያል። ታዲያ ልጆቻችሁ እንዲህ ያሉ የሥነ ምግባር እሴቶች እንዲኖሯቸው ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

የሥነ ምግባር አቋማችሁን ግልጽ አድርጉ።

የፆታ ግንኙነት የተፈቀደው በጋብቻ ለተሳሰሩ ሰዎች ብቻ እንደሆነ ታምናላችሁ? ከሆነ ይህን አቋማችሁን ለልጆቻችሁ ሳታሰልሱ በግልጽ ንገሯቸው። ቢዮንድ ዘ ቢግ ቶክ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ “ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ትክክል እንዳልሆነ በግልጽ በሚናገሩ ወላጆች ያደጉ ልጆች ብዙውን ጊዜ የፆታ ግንኙነት ለመጀመር [አይቸኩሉም]።”

እርግጥ ነው፣ ቀደም ሲል እንዳየነው የሥነ ምግባር አቋማችሁ ምን እንደሆነ መግለጻችሁ ብቻ ልጆቻችሁ ይህን አቋማችሁን እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። ይሁንና ቤተሰባችሁ እንዲኖረው የምትፈልጉትን የሥነ ምግባር አቋም በግልጽ መናገራችሁ ልጆቻችሁ የራሳቸውን አቋም በሚገነቡበት ጊዜ እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላቸዋል። ብዙ ወጣቶች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው መመሪያዎችን ለመከተል እንቢተኛ የሆኑ ቢመስሉም በኋላ ላይ ግን የወላጆቻቸውን የሥነ ምግባር እሴት እንደተከተሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የዜና ዘገባዎችን ከልጆቻችሁ ጋር ውይይት ለመጀመርና ስለ ሥነ ምግባር አቋማችሁ ለመነጋገር ተጠቀሙባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በሴቶች ላይ ስለተፈጸመ የወንጀል ዘገባ ስትሰሙ እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ፦ “አንዳንድ ወንዶች ሴቶችን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚጥሩበት መንገድ በጣም ይዘገንነኛል። እንዲህ ያለውን ጭካኔ የሚማሩት ከየት ይመስልሃል?”

ስለ ፆታ ምንም ሳትደብቁ አስተምሯቸው።

ማስጠንቀቂያ መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ያዕቆብ 1:14, 15) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነትን በዋነኝነት የሚገልጸው የአምላክ ስጦታ እንደሆነ እንጂ የሰይጣን ወጥመድ አድርጎ እንዳልሆነ መዘንጋት የለባችሁም። (ምሳሌ 5:18, 19፤ ማሕልየ መሓልይ 1:2) ለልጆቻችሁ የምትነግሯቸው የፆታ ግንኙነት ስለሚያስከትለው አደጋ ብቻ ከሆነ ስለ ጉዳዩ የተዛባና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት ሊይዙ ይችላሉ። በፈረንሳይ የምትኖር ኮሪና የተባለች ወጣት “ወላጆቼ ስለ ፆታ ሲያወሩ ብዙ ጊዜ የሚቀናቸው መጥፎ ጎኑን መናገር ነበር። ይህ ደግሞ ስለ ፆታ ግንኙነት አሉታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ አድርጓል” ብላለች።

ልጆቻችሁ ስለ ፆታ ግንኙነት የተሟላ መረጃ እንዲኖራቸው አድርጉ። በሜክሲኮ የምትኖር ናዲያ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “የፆታ ግንኙነት እርካታ የሚሰጥ ተፈጥሯዊ ስሜት እንደሆነና ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጣቸው እንዲደሰቱበት እንደሆነ ልጆቼን ለማስገንዘብ ሁልጊዜ እጥራለሁ። ይሁንና የፆታ ግንኙነት ሊፈጸም የሚገባው በትዳር ውስጥ ብቻ ነው። ይህን ስጦታ የምንጠቀምበት መንገድ ደስታ ሊያመጣልን ወይም ሥቃይ ሊያስከትልብን ይችላል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በሚቀጥለው ጊዜ ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ ስታወሩ ንግግራችሁን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመቋጨት ሞክሩ። የፆታ ግንኙነት ከአምላክ የተገኘ አስደሳች ስጦታ እንደሆነና ልጆቻችሁ ወደፊት ትዳር ከመሠረቱ ከዚህ ስጦታ ደስታ ማግኘት እንደሚችሉ መናገር ሊያሳፍራችሁ አይገባም። ልጆቻችሁ ትዳር እስኪመሠርቱ ድረስ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጠብቀው መኖር እንደሚችሉ ንገሯቸው።

የሚያስከትለውን ውጤት እንዲያመዛዝኑ እርዷቸው።

በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆች በየትኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉ ያሏቸውን አማራጮች መለየትና እያንዳንዱ ምርጫ የሚያስከትለውን ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። ትክክልና ስህተት የሆነውን ማወቃቸው ብቻ በቂ እንደሆነ ሊሰማችሁ አይገባም። በአውስትራሊያ የምትኖር ኤማ የተባለች ክርስቲያን እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አወቃችሁ ማለት ትስማሙበታላችሁ ማለት እንዳልሆነ ወጣት ሳለሁ ከሠራሁት ስህተት መናገር እችላለሁ። እነዚህን መሥፈርቶች መከተል ያለውን ጥቅምም ሆነ መሥፈርቶቹን መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ መገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ መመሪያዎች አድርግ አታድርግ በማለት ብቻ ሳይወሰኑ መጥፎ አካሄድ የሚያስከትለውን መዘዝ ጭምር ስለሚናገሩ በጣም ጠቃሚ ናቸው። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 5:8, 9 (1954 ትርጉም) አንድን ወጣት ከዝሙት መሸሽ ያለበት ለምን እንደሆነ ሲያስጠነቅቅ “ክብርህን ለሌላ እንዳትሰጥ” በማለት ተናግሯል። ይህ ጥቅስ እንደሚጠቁመው ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውንና ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት ያጣሉ። በተጨማሪም እንደነዚህ ዓይነት ባሕርያት ባላቸው ሰዎች ዘንድ አክብሮት ስለሚያጡ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ላያገኙ ይችላሉ። ልጆቻችሁ የአምላክን ሕጎች ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ በሚያስከትለው አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ አደጋ ላይ ማሰላሰላቸው ከእነዚህ ሕጎች ጋር ተስማምተው ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል። *

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጠበቅ የጥበብ አካሄድ እንደሆነ ለልጆቻችሁ ለማስረዳት ምሳሌዎችን ተጠቀሙ። ለአብነት ያህል፣ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “ምግብ ለማብሰል በምንጠቀምበት እሳትና በሰደድ እሳት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? አምላክ የፆታ ግንኙነትን አስመልክቶ ካስቀመጠው ገደብ ጋር በተያያዘ ይህን ምሳሌ እንዴት ልትሠራበት ትችላለህ?” በ⁠ምሳሌ 5:3-14 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ልጆቻችሁ ዝሙት የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ተጠቀሙበት።

በጃፓን የምትኖር ታካኦ የተባለች የ18 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ፤ ይሁንና ይህንን ለማድረግ ከሥጋዊ ፍላጎቶቼ ጋር ሁልጊዜ መታገል ይኖርብኛል።” የታካኦን ስሜት የሚጋሩ ወጣቶች እንዲህ የሚሰማቸው እነሱ ብቻ እንዳልሆኑ ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። ጠንካራ ክርስቲያን የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት የተሰማውን ሳይሸሽግ ተናግሯል።—ሮም 7:21

ወጣቶች እንዲህ ዓይነቱ ትግል ሁልጊዜ መጥፎ እንዳልሆነ መገንዘባቸው ጠቃሚ ነው። ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደሚፈልጉ ቆም ብለው እንዲያስቡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። የሚከተሉትን ጥያቄዎች በሚገባ እንዲያጤኑም ይረዳቸዋል፦ ‘የራሴን ሕይወት ራሴ መምራት እንዲሁም አቋም ያለው ሰው መሆን ነው የምፈልገው? ወይስ ሌሎችን የምከተልና ለምኞቶቼ በቀላሉ የምሸነፍ ደካማ ሰው?’ ልጆቻችሁ ጥሩ የሥነ ምግባር እሴት ያላቸው መሆኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች ጥበብ የታከለበት መልስ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል።

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.10 ከልጆቻችሁ ጋር ፆታን አስመልክቶ እንዴት ውይይት እንደምትጀምሩና ለዕድሜያቸው የሚመጥን መረጃ እንዴት መስጠት እንደምትችሉ የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ለማግኘት የኅዳር 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12-14 ተመልከቱ።

^ አን.22 ለተጨማሪ መረጃ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ ያቀራርበን ይሆን?” የሚለውን ርዕስ በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው የሚያዝያ 2010 ንቁ! ተመልከት።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  • ልጆቼ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም እንዳላቸው የሚጠቁም ምን ነገር ተመልክቻለሁ?

  • ከልጆቼ ጋር ስለ ፆታ ስነጋገር የፆታ ግንኙነትን በዋነኝነት የምገልጸው ከአምላክ እንደተገኘ ስጦታ አድርጌ ነው ወይስ ሰይጣን እንዳስቀመጠው ወጥመድ?