“ዛሬ የእናንተ ቀን ነው”
129ኛው የጊልያድ ምረቃ
“ዛሬ የእናንተ ቀን ነው”
መስከረም 11, 2010 ወደ 8,000 የሚጠጉ ሰዎች በአንድ ልዩ ዝግጅት ይኸውም በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ129ኛው ክፍል የምረቃ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ተሰብስበዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ ተማሪዎቹን “ዛሬ የእናንተ ቀን ነው። እኛም እዚህ የተገኘነው የደስታችሁ ተካፋይ ለመሆን ነው!” አላቸው።
“የሚሰሙ ጆሮዎች”
ወንድም ሳሙኤል ኸርድ ፕሮግራሙን የጀመረው ሁሉም ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል ትኩረት በመስጠት ‘የሚሰሙ ጆሮዎቻቸውን’ በሚገባ መጠቀማቸው ያለውን አስፈላጊነት በማብራራት ነው። (ምሳሌ 20:12) ከዚያም ተመራቂዎቹን “ላለፉት ጥቂት ወራት ጆሮዎቻችሁን ለይሖዋ አውሳችሁት ነበር፤ እንዲህ ማድረጋችሁንም ለዘላለም ትቀጥላላችሁ” አላቸው።
ታዲያ አዲሶቹ ሚስዮናውያን ጆሮዎቻቸውን በጥበብ መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው? ወንድም ሳሙኤል ኸርድ “ለአምላክ ቃል ጆሯችሁን በመስጠት ነው” ብሏቸዋል። ቀጥሎም “በመጪዎቹ ዓመታት ሚስዮናዊ ሆናችሁ ለምታከናውኑት ሥራ የሚያዘጋጇችሁ በርካታ ነጥቦችን በዛሬው ፕሮግራም ላይ ታዳምጣላችሁ” አላቸው።
“በሙሉ ልባችሁ በይሖዋ ታመኑ”
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ ስሜት ቀስቃሽ በሆነው በዚህ ጭብጥ ዙሪያ የሚያጠነጥን ንግግር ለተማሪዎቹ አቀረበ። ወንድም በንግግሩ ላይ ጥንትም ሆነ ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች በይሖዋ እንደሚታመኑ ያሳዩባቸውን በርካታ አጋጣሚዎች ጠቅሷል።
በተመሳሳይም “ሚስዮናውያን ተልእኳቸውን በመወጣት ረገድ በይሖዋ መታመን ይገባቸዋል” በማለት ተናግሯል። ከዚያም “ለምሳሌ ‘አዲሱን ቋንቋ መልመድ እችል ይሆን? ከአዲሱ ባሕል ጋር እላመድ ይሆን? ናፍቆት ያስቸግረኝ ይሆን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ትጠይቁ ይሆናል” አላቸው። ታዲያ መፍትሔው ምን ይሆን? ወንድም ሎሽ ተማሪዎቹን “በይሖዋ ታመኑ” በማለት አሳሰባቸው።
በተጨማሪም ወንድም ሎሽ፣ ይሖዋን “ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው” የሚል ሐሳብ የያዘውን ምሳሌ 14:26ን አነበበ። ይሖዋ ባደረገልን በርካታ ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ በእሱ ይበልጥ እየታመንን እንሄዳለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ስለሚታመን ሰው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”—ኤርምያስ 17:7, 8
ወንድም ሎሽ ነጥቡን ግልጽ ሲያደርግ “ወደፊት የሚጠብቃችሁ ምንም ይሁን ምን በይሖዋ መታመን ይኖርባችኋል” በማለት ተናገረ።
“ታማኝ የሆኑትን መላእክት ምሳሌ ተከተሉ”
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት በዚህ ጭብጥ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቅርቦ ነበር። መላእክት ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ወንድም ሌት “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት የሚናገረውን እያንዳንዱን ነገር እንደ ምሳሌ ልንከተለው ይገባል” በማለት ተናገረ። ከዚያም ታማኝ መላእክት እንደ ምሳሌ ልንከተላቸው የምንችላቸውን አራት ባሕርያት ይኸውም ጽናትን፣ ትሕትናን፣ ሌሎችን የመርዳት መንፈስንና ንጹሕ አቋምን እንዳንጸባረቁ ጠቀሰ።
አንድ መልአክ ‘የፋርስ አለቃ’ የተባለውን አንድ ኃይለኛ ጋኔን ለ21 ቀናት እንደተቋቋመ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዳንኤል 10:13) ይህ መልአክ ጽናት አሳይቷል። ወንድም ሌት ሲቀጥል ክርስቲያኖችም ‘ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ትግል እንደገጠሙ’ ገለጸ። (ኤፌሶን 6:12) ከዚያም “በተሰጣችሁ ሥራ መቀጠል እንድትችሉ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ” በማለት ተማሪዎቹን አሳሰባቸው።
መሳፍንት 13:17, 18) ወንድም ሌት ለተማሪዎቹ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ሰው ችሎታችሁን እየጠቀሰ ሊያሞጋግሳችሁ ወይም አድናቆት ሊቸራችሁ ቢሞክር ትሑት በመሆን ትኩረቱን ከእናንተ ይልቅ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ እንዲያሳርፍ አድርጉ።”—1 ቆሮንቶስ 4:7
የሳምሶን አባት የሆነው ማኑሄ ያነጋገረውን መልአክ ስሙን ሲጠይቀው መልአኩ ለመናገር ፈቃደኛ አልነበረም። ይህ መልአክ ትሕትና አሳይቷል። (ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሳለ “አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።” (ሉቃስ 22:43) ይህ መልአክ ሌሎችን የመርዳት መንፈስ አሳይቷል። ወንድም ሌት እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በሚስዮናዊነት በምታገለግሉበት አካባቢ ያሉት ሰዎች ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ በጸሎት አስቡበት፤ ከዚያም በይሖዋ እርዳታ የእነዚህን ሰዎች ፍላጎት ለሟሟላት ጥረት አድርጉ።”
ሰይጣን በቀሰቀሰው ዓመፅ የተባበሩት መላእክት ቁጥር አነስተኛ እንደመሆኑ መጠን አብዛኞቹ መንፈሳዊ ፍጥረታት ንጹሕ አቋም ጠባቂ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል ማለት ይቻላል።—ራእይ 12:4
ወንድም ሌት “እንደነዚህ ታማኝ መላእክት ዲያብሎስን ተቋቋሙት” በማለት ተማሪዎቹን አሳሰባቸው። አክሎም “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ እሱም ይሸሻል” አላቸው።—ያዕቆብ 4:7
በፕሮግራሙ ላይ የጎሉ ሌሎች ሦስት ክፍሎች
“ይሖዋ ምንጊዜም የልባችሁ ዐለት እንዲሆን አድርጉ።” የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጋሪ ብሮን ተማሪዎቹ በይሖዋ ላይ መታመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለመርዳት በመዝሙር 73:26 (NW) ላይ የተመሠረተውን ቀልብ የሚስብ ንግግር አቀረበ። ይሖዋ ዐለት ይሆናል ሲባል ምን ማለት ነው? ወንድም ብሮን እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ወረቀት ላይ ድንጋይ በማስቀመጥ ወረቀቱን ነፋስ እንዳይወስደው ማድረግ ይቻላል፤ በተመሳሳይም ይሖዋ ልባችሁ እንዳይሸፍት በማድረግ ተረጋግታችሁ እንድትቆዩ ይረዳችኋል።” እርግጥ ነው፣ ጽናት የሚጠይቁ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ልባችን ሊያታልለን ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) አዲስ የአየር ንብረትና አዳዲስ ምግቦችን መልመድ፣ በሚስዮናዊ ቤቶች አብረዋችሁ ከሚኖሩት ጋር መስማማት ወይም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን መቋቋም ሲከብዳችሁ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጋችሁ ለመተው ታስቡ ይሆናል። ወንድም ብሮን እንዲህ አለ፦ “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ምን አማራጮች እንዳሏችሁ ማሰብና ውሳኔ መወሰን ይኖርባችኋል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ታደርጉ ይሆን? እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ይሖዋ ‘የልባችሁ ዐለት’ ይሆናል። እንዲሁም አካሄዳችሁን ይመራላችኋል።”
“እግራችሁን ውኃው ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል እምነት አላችሁ?” የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ሳም ሮበርሰን በኢያሱ ምዕራፍ 3 ላይ የተመሠረተውን ይህን ጭብጥ አብራራ። በሚሊዮን የሚቆጠሩት እስራኤላውያን ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላውን የዮርዳኖስ ወንዝ ማቋረጥ የቻሉት እንዴት ነው? ይሖዋ “በወንዙ ውስጥ ገብታችሁ ቁሙ” የሚል ትእዛዝ ለካህናቱ እንዲሰጥ ለኢያሱ ነገረው። ከዚያም “[ካህናቱ] ገና እግራቸውን በዮርዳኖስ ውሃ ውስጥ እንዳስገቡ፣ . . . [ውሃው] ወዲያውኑ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል” በማለት አምላክ ቃል ገባ። (ኢያሱ 3:8, 13) በመቀጠል ወንድም ሮበርሰን ተማሪዎቹን “እናንተም ከፈቀዳችሁ የአምላክን በረከት እንዳታገኙ በሕይወታችሁ ውስጥ ጋሬጣ የሚሆኑባችሁ ‘የዮርዳኖስ ወንዞች’ ሊኖሩ ይችላሉ” አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ አብረዋችሁ ከሚኖሩ ሚስዮናውያን ጋር ተጣጥማችሁ መኖር ተፈታታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? “አብረዋችሁ በሚሠሩት ላይ ሳይሆን በሥራው ላይ ትኩረት አድርጉ።” ወንድም ሮበርሰን ተማሪዎቹን “እግራችሁን ውኃው ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል እምነት ካሳያችሁ ይሖዋ በሚስዮናዊ ሕይወታችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁን ‘የዮርዳኖስ ወንዞች’ መሻገር እንድትችሉ ይረዳችኋል” በማለት አሳሰባቸው።
“እቅዳችሁ እንዲሳካ አድርጉ።” በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ንግግር ያቀረበው የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ዊልያም ሳሙኤልሰን ነበር። ንግግሩ የተመሠረተው “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ ምሳሌ 16:3 ላይ ነበር። ወንድም ሳሙኤልሰን ለተማሪዎቹ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው፦ “ይህ ጥቅስ፣ የምታደርጉትን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ከመስጠት ውጪ እቅዳችሁን በማሳካት ረገድ ምንም ድርሻ እንደሌላችሁ የሚገልጽ ነው?” ወንድም ሳሙኤልሰን ምሳሌ 16:1 (የ1954 ትርጉም) “የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” ስለሚል የጥቅሱ ሐሳብ እንዲህ እንዳልሆነ ተናገረ። ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ልባችሁን አያዘጋጅም። ከዚህ ይልቅ ልባችሁ ያዘነበለው ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ አለባችሁ። በትጋት የምታጠኑና የምትጸልዩ እንዲሁም በአካባቢያችሁ ከሚገኘው የቅርንጫፍ ቢሮ ጋር የምትተባበሩ ከሆነ ጥሩ ልብ ይዛችሁ መቀጠል የምትችሉ ሲሆን ይሖዋም እቅዳችሁን ሁሉ ያሳካላችኋል።”
ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል” የሚል ሐሳብ ባለው በተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች
ለጊልያድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚሰጣቸው ሥልጠና በአካባቢያቸው ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈልን ይጨምራል። ማርክ ኑሜር የተባለ ሌላ የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች እንዲናገሩ ለበርካታ ተማሪዎች ቃለ ምልልስ አደረገ። እነዚህ ተሞክሮዎች፣ ጸሎት በክልሉ ውስጥ ያሉትን ልበ ቅን ሰዎች ለማግኘት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይበልጥ አጉልተዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባልና ሚስት ወደ አንድ ምግብ ቤት ገብተው ነበር። በምግብ ቤቱ ውስጥ የሚሠራ አንድ ሰው እነዚህ ባልና ሚስት ከመመገባቸው በፊት በልባቸው ሲጸልዩ ተመለከተ። ከዚያም ወደ እነሱ ቀረብ ብሎ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ጠየቃቸው። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ሲገነዘብ በልጅነቱ የይሖዋ ምሥክር እንደነበርና አሁን ግን ከጉባኤ እንደራቀ ነገራቸው። እንዲያውም ወንጀል በመፈጸሙ ወኅኒ ወርዶ ነበር። አሁን ይህ ወጣት ወደ ይሖዋ መመለስ እንዳለበት ተሰምቶታል። በተጨማሪም እነሱ ወደ ምግብ ቤቱ ከመግባታቸው በፊት ሕይወቱን ለማስተካከል ፍላጎት እንዳለው ወደ አምላክ እየጸለየ እንደነበር ነገራቸው። በእርግጥም ጸሎቱ ተመልሶለታል!
የደብዳቤ ልውውጥ ክፍል ባልደረባ የሆነው ሩዲ ሃርትል “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፣ እዩም” በሚል ጭብጥ ባቀረበው ንግግር ላይ ከሞዛንቢክ ለመጣው ለወንድም ዌን ሪጅዌ፣ ከቺሊ ለመጣው ለወንድም ጄሰን ሪድ እና ከኔፓል ለመጣው ለወንድም ኬንጂ ቺቺኢ ቃለ ምልልስ አደረገላቸው። ሦስቱም በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናዊያን ናቸው። እነዚህ ወንድሞች አዲስ ሚስዮናዊ በነበሩበት ወቅት አዲስ ቋንቋ መማር፣ አዲስ ባሕል መልመድ ወይም ናፍቆትን መቋቋም ተፈታታኝ ሆኖባቸው እንደነበር በግልጽ ተናግረዋል። ወንድም ቺቺኢ እንዲህ ብሏል፦ “ከሁኔታዎች ጋር እንድንላመድ የረዳን ነገር ቢኖር በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ቶሎ ብለን ጓደኞች ማፍራታችን ነው። ከጉባኤው ጋር ይበልጥ በተቀራረብን ቁጥር ናፍቆቱ እየለቀቀን ሄደ።”
ሃምሳ ስድስቱም ተማሪዎች ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከመካከላቸው አንዱ የተመራቂዎቹን አድናቆት የሚገልጽ ስሜት የሚነካ ደብዳቤ አነበበ። የበላይ አካሉን አስመልክቶ በደብዳቤው ላይ የሰፈረው ሐሳብ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ሥርዓተ ትምህርቱን ለመቅረጽ፣ የምንማርበት ክፍል ድረስ እየመጣችሁ ለመጎብኘትና ግሩም መንፈሳዊ መመሪያዎችን ለመስጠት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ በፍቅር ያደረጋችሁትን ጥረት መመልከት ችለናል። ፍቅራችሁን ስለቀመስን በምንመደብባቸው ቦታዎች ፍቅርን፣ ትዕግሥትን፣ አሳቢነትንና ትሕትናን በማሳየት ረገድ የእናንተን ግሩም ምሳሌ ለመከተል የቻልነውን ያህል እንጥራለን።”
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘አንድ ሰው ሊያሞጋግሳችሁ ቢሞክር ትኩረቱን ከእናንተ ይልቅ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ እንዲያሳርፍ አድርጉ’
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘በሕይወታችሁ ውስጥ “የዮርዳኖስ ወንዞች” ሊኖሩ ይችላሉ’
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ቻርት/ካርታ]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
9 የተውጣጡባቸው አገሮች
56 ተማሪዎች
28 ባልና ሚስት
33.0 አማካይ ዕድሜ
17.9 ከተጠመቁ በኋላ ያሳለፉት ዓመታት በአማካይ
13.3 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ
[ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ተመራቂዎቹ የተመደቡት ከታች ወደሚገኙት 25 አገሮች ነው
ሚስዮናውያን የተመደቡባቸው አገሮች
ቦሊቪያ
ቦትስዋና
ቡልጋሪያ
ኮንጎ (ኪንሻሳ)
ኮት ዲቩዋር
ጋምቢያ
ጀርመን
ሕንድ
ኢንዶኔዥያ
ኬንያ
ላይቤሪያ
መቄዶንያ
ማዳጋስካር
ማሌዥያ
ሞዛምቢክ
ፓናማ
ፔሩ
ፖላንድ
ሩማኒያ
ሰርቢያ
ሴራ ሊዮን
ስዋዚላንድ
ታንዛኒያ
ኡጋንዳ
ዚምባብዌ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ ተማሪዎች ካገኟቸው ተሞክሮዎች መካከል አንዱን በሠርቶ ማሳያ ሲያቀርቡ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ129ኛው ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ሬቤካ ሙናሬቶ፣ ኢቮን ኡሎቭሶን፣ ናይታ በደን፣ ሊንሴ ናይጆን፣ ጂኔት ሞያ፣ ግሪሴልዳ ትሬቪንዮ፣ አንድሪያ ዲዮን፣ አንድሪያ ፍሊገል
(2) ጃኪ ስሚዝ፣ ጀንሲ ማይክል ራጅ፣ ሻላነ ስሚዝ፣ አውሮራ ፓራሞ፣ ጄኒፈር ማክዶናልድ፣ ሜላኒ ዲንስ፣ ሱኒተ ጆያል፣ ሉሲ ዋትሰን
(3) ሲ ጆያል፣ ቶኒ ክራሊ፣ ዶን ሃከር፣ ጄሲካ ሺንካሬንኮ፣ ትሬሲ ናፕ፣ ጄኒ ኤሊንግ፣ ከሚል ሃይሊ፣ ብዮርን ኡሎቭሶን
(4) ማይክል ፊትስፓትሪክ፣ ብራየን ናይጆን፣ ሊንድቬ ስካለሩድ፣ አሽሊ ሃሪስ፣ ሴሼል ሃሪስ፣ ሮሪ በደን፣ ዮናታን ፓራሞ፣ ኬንየን ስካለሩድ
(5) ብሬንደን ክራሊ፣ ጆሴፍ ማይክል ራጅ፣ አንዲ ላጅ፣ ሬቸል ላጅ፣ ናዲን ኸርምስ፣ ጁልያ ፊትስፓትሪክ፣ ሮቤርቶ ሞያ፣ ፕየትሮ ሙናሬቶ
(6) ስቴቨን ዋትሰን፣ ማቲው ዲንስ፣ ጄፍ ሃከር፣ ጆሹዋ ማክዶናልድ፣ ጆን ትሬቪንዮ፣ ሾን ሃሪስ፣ ክሪስ ኸርምስ፣ ፒተር ሃሪስ
(7) ቪክቶር ሺንካሬንኮ፣ ታድ ሃይሊ፣ አሊክስ ስሚዝ፣ ጄፍ ዲዮን፣ ራይን ኤሊንግ፣ ቤን ስሚዝ፣ ቶኒ ናፕ፣ ብሬ ፍሊገል