በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተለመዱ ቅሬታዎችና መፍትሔዎቻቸው

የተለመዱ ቅሬታዎችና መፍትሔዎቻቸው

የተለመዱ ቅሬታዎችና መፍትሔዎቻቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ትዳር መምራት ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ያገቡ ሰዎች “ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል” በማለት በአምላክ መንፈስ መሪነት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:28 አ.መ.ት) ይሁንና የተጋቡ ሰዎች ችግሮችን መቀነስ አልፎ ተርፎም አንዳቸው ለሌላው ደስታ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። ከዚህ ቀጥሎ ባልና ሚስቶች የሚያሰሟቸውን የተለመዱ ስድስት ቅሬታዎች እንመለከታለን፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት እንዴት እንደሚረዳ እናያለን።

1

ቅሬታ፦

“በጣም ተራርቀናል።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”​—ፊልጵስዩስ 1:10

ትዳራችሁ በሕይወታችሁ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። ከምንም በላይ ቅድሚያ ልትሰጡት ይገባል። በመሆኑም የዕለት ተዕለት ፕሮግራማችሁ ለዚህ ቅሬታ አስተዋጽኦ አድርጎ እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። የዘወትር እንቅስቃሴያችሁ እንዳያራርቃችሁ ተጠንቀቁ። እርግጥ ነው፣ ሥራና ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች አብራችሁ ልታሳልፉት የሚገባውን ጊዜ አልፎ አልፎ ሊሻሙባችሁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በቁጥጥራችሁ ሥር በሆኑት ነገሮች ላይ ገደብ ማበጀት ትችላላችሁ። ለምሳሌ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ወይም ከጓደኞቻችሁ ጋር የምታጠፉትን ጊዜ መቀነስ ትችላላችሁ፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይገባችኋል።

ይሁንና አንዳንድ ያገቡ ሰዎች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ጊዜ ላለማሳለፍ ሲሉ ከመጠን በላይ በሥራ ሊጠመዱ አሊያም በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ብዙ ጊዜ ሊያጠፉ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ‘እየተራራቁ ነው’ ሊባል አይችልም። ከዚህ ይልቅ ከችግሮች እየሸሹ ነው። የእናንተ ወይም የትዳር ጓደኛችሁ ሁኔታ እንዲህ ከሆነ ችግሩ ምን እንደሆነ ለይታችሁ ለማወቅና መፍትሔ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ ጊዜ ማሳለፋችሁ ብቻ አንዳችሁ ከሌላው ጋር ይበልጥ እንድትቀራረቡና ከምንጊዜውም ይበልጥ “አንድ ሥጋ” እንድትሆኑ ሊረዳችሁ ይችላል።—ዘፍጥረት 2:24

አንዳንዶች ይህን ምክር የሠሩበት እንዴት ነው? አንድሩና * ታንጂ በአውስትራሊያ የሚኖሩ ባልና ሚስት ሲሆኑ በትዳር ዓለም አሥር ዓመት አሳልፈዋል። አንድሩ እንዲህ ይላል፦ “ከመጠን በላይ መሥራትና በማኅበራዊ ሕይወት መጠላለፍ ለትዳር አደገኛ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። በመሆኑም እኔና ባለቤቴ አብረን ለመጫወትና አንዳችን ለሌላው ስሜታችንን ለመግለጽ ጊዜ እንመድባለን።”

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩትና በትዳር ዓለም 22 ዓመት ያሳለፉት ዴቭና ጄን ሁልጊዜ ማታ ማታ ሲገናኙ የመጀመሪያውን 30 ደቂቃ ስለ ዕለት ውሏቸው ለማውራትና ሐሳባቸውን ለመለዋወጥ ይጠቀሙበታል። ጄን “ይህ ጊዜ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልብን አንፈልግም” ብላለች።

2

ቅሬታ፦

“ከትዳሬ የምፈልገውን ነገር እያገኘሁ አይደለም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“እያንዳንዱ ሰው ዘወትር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”1 ቆሮንቶስ 10:24

አንድ ሰው ይበልጥ የሚያስበው ከትዳሩ ስለሚያገኘው ነገር ብቻ ከሆነ ዕድሜ ልኩን ሲያገባ ቢኖር እውነተኛ ደስታ ሊያገኝ አይችልም። ትዳር የተሳካ የሚሆነው ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ላይ የሚያተኩሩ ከሆነ ነው። ኢየሱስ ምክንያቱን ሲገልጽ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

አንዳንዶች ይህን ምክር የሠሩበት እንዴት ነው? በሜክሲኮ የሚኖሩት ማሪያና ማርቲን በትዳር ዓለም 39 ዓመታት አሳልፈዋል። ይሁንና ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ነበር ማለት አይደለም። በተለይ በአንድ ወቅት የመረረ ጥል ተጣልተው እንደነበር ያስታውሳሉ። ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም እየተጨቃጨቅን ሳለ አክብሮት የጎደለው ነገር ተናገርኩት። በዚህ ጊዜ ማርቲን በጣም ተናደደ። ይህን ያልኩት ስለተበሳጨሁ እንጂ ከልቤ እንዳልሆነ ልነግረው ሞከርኩ። እሱ ግን ሊሰማኝ አልፈለገም።” ማርቲን ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ያን ጊዜ ስንጨቃጨቅ አብረን መኖር እንደማንችልና ትዳራችንን ለማሳካት የማደርገውን ጥረት እርግፍ አድርጌ መተው እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ።”

ማርቲን አክብሮት እንዲሰጠው ፈልጓል። ማሪያ ደግሞ ስሜቷን የሚረዳላት ሰው ፈልጋለች። ይሁንና አንዳቸውም ቢሆኑ የሚፈልጉትን አላገኙም።

ታዲያ ችግሩን የፈቱት እንዴት ነው? ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “ጊዜ ወስጄ ራሴን አረጋጋሁ። ከዚያም ሁለታችንም ጥበብ የተሞላበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል እርስ በርስ ለመከባበርና አንዳችን ለሌላው ደግነት ለማሳየት ወሰንን። በጊዜ ሂደት አንድ ነገር ተምረናል፦ ችግሮች ምንም ያህል ደጋግመው ቢነሱ አምላክ እንዲረዳን ከጸለይንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ከሠራንበት ማንኛውንም ችግር ማሸነፍ እንችላለን።”—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ኤፌሶን 4:31, 32

3

ቅሬታ፦

“የትዳር ጓደኛዬ ኃላፊነቱን አይወጣም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።”ሮም 14:12

ለትዳሩ መሳካት ደፋ ቀና የሚለው አንደኛው ወገን ብቻ ከሆነ ትዳሩ ሙሉ ለሙሉ የተቃና እንደማይሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ባልም ሆነ ሚስት ትዳራቸውን ለማቃናት ሳይጥሩ ሌላውን እየወቀሱ የሚኖሩ ከሆነ ሁኔታው የከፋ ይሆናል።

ሁልጊዜ የምታስቡት የትዳር ጓደኛችሁ ማድረግ ስለሚኖርበት ጉዳይ ከሆነ ራሳችሁን ችግር ውስጥ እየዘፈቃችሁ ነው። በተለይ የትዳር ጓደኛችሁን ድክመት ሰበብ በማድረግ የራሳችሁን ኃላፊነት የማትወጡ ከሆነ ችግሩ የከፋ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ጥሩ ባል ወይም ጥሩ ሚስት ለመሆን የምትጥሩ ከሆነ የትዳር ሕይወታችሁ እየተሻሻለ መምጣቱ አይቀርም። (1 ጴጥሮስ 3:1-3) ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ ላደረገው የጋብቻ ዝግጅት አክብሮት እንዳላችሁ ታሳያላችሁ፤ እሱም በምታደርጉት ጥረት እጅግ ይደሰታል።—1 ጴጥሮስ 2:19

አንዳንዶች ይህን ምክር የሠሩበት እንዴት ነው? በኮሪያ የምትኖረው ኪምና ባለቤቷ በትዳር ሕይወት 38 ዓመት አሳልፈዋል። ኪም እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ባለቤቴ ብስጭትጭት ይልና ያኮርፈኛል፤ ምን እንዳበሳጨው እንኳ አላውቅም። በዚህ ወቅት ‘ለእኔ ያለው ፍቅር ቀንሷል’ የሚል ስሜት ያድርብኛል። እንዲያውም አንዳንዴ ‘እሱ እኔን ለመረዳት ሳይሞክር የእሱን ችግር እንድረዳለት ለምን ይጠብቅብኛል?’ ብዬ አስባለሁ።”

ኪም ባለቤቷ በፈጸመው ስህተትና ባልተወጣው ኃላፊነት ላይ ማተኮር ትችል ነበር። እሷ ግን እንዲህ አላደረገችም። ኪም እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከማኩረፍ ይልቅ ቀዳሚ ሆኖ ሰላም ለመፍጠር ጥረት ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። አሁን ሁለታችንም ራሳችንን አረጋግተን ችግሩን ለመፍታት በሰላም መነጋገር ችለናል።”—ያዕቆብ 3:18

4

ቅሬታ፦

“ባለቤቴ ለራስነት ሥልጣን አትገዛም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ [ነው]።”—1 ቆሮንቶስ 11:3

ሚስቱ ለራስነት ሥልጣን እንደማትገዛ የሚሰማው ባል በመጀመሪያ እሱ ራሱ፣ ራስ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን እየተገዛ መሆን አለመሆኑን መመርመር ይኖርበታል። አንድ ባል የኢየሱስን አርዓያ በመከተል ለራስነት ሥልጣን የሚገዛ መሆኑን ማሳየት ይችላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌሶን 5:25) ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ‘ሥልጣኑን ለማሳየት’ አልሞከረም። (ማርቆስ 10:42-44) ለተከታዮቹ ግልጽ የሆነ መመሪያ ያስቀምጥላቸው ብሎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እርማት ይሰጣቸው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አምባገነን አልነበረም። ደግነት ያሳያቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከአቅማቸው በላይ አይጠብቅባቸውም ነበር። (ማቴዎስ 11:29, 30፤ ማርቆስ 6:30, 31፤ 14:37, 38) ምንጊዜም ከራሱ ይልቅ የእነሱን ፍላጎት ያስቀድም ነበር።—ማቴዎስ 20:25-28

አንድ ባል እንዲህ በማለት ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘ለራስነት ሥልጣንና ለሴቶች ባለኝ አመለካከት ላይ ይበልጥ ተጽዕኖ ያሳደረብኝ ምንድን ነው? ያደግኩበት ማኅበረሰብ የሚከተለው ወግ ነው? ወይስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምክሮችና ምሳሌ ተደርገው የተጠቀሱ ሰዎች?’ ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሴት ከባሏ የተለየ ሐሳብ ቢኖራትና በአክብሮት ሆኖም በማያወላውል መልኩ የተቃውሞ ሐሳቧን ብታቀርብ ምን ይሰማሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ለሥልጣን በመገዛት ረገድ በአርዓያነት ከሚጠቅሳቸው ሴቶች አንዷ የአብርሃም ሚስት ሣራ ናት። (1 ጴጥሮስ 3:1, 6) ይሁን እንጂ ሣራ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ የተሰማትን ከመናገር ወደኋላ አትልም ነበር፤ ለምሳሌ ቤተሰቡን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር መኖሩን አብርሃም እንዳላስተዋለ በተገነዘበች ጊዜ የተሰማትን ነግራዋለች።—ዘፍጥረት 16:5፤ 21:9-12

አብርሃም ሣራን የያዛት እሱን ማነጋገር እንዲያስፈራት በሚያደርግ መንገድ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ጨካኝና አምባገነን አልነበረም። በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርግ ባል፣ የተናገረውን ሁሉ ካላደረገች ብሎ በረባ ባልረባው በሚስቱ ላይ አይደነፋም። እንዲህ ያለው ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀመው ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለሆነ የሚስቱን አክብሮት ያተርፋል።

አንዳንዶች ይህን ምክር የሠሩበት እንዴት ነው? በእንግሊዝ የሚኖረውና በትዳር ዓለም ስምንት ዓመት የቆየው ጄምስ እንዲህ ብሏል፦ “አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን በማደርግበት ጊዜ ባለቤቴን ማማከር እየለመድኩ ነው። የራሴን ጉዳይ ብቻ ላለማሰብ እሞክራለሁ። እንዲያውም የራሴን ሳይሆን የእሷን ፍላጎት ለማስቀደም እጥራለሁ።”

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ጆርጅ የተባሉ አረጋዊ በትዳር ዓለም 59 ዓመታት አሳልፈዋል። እንዲህ ይላሉ፦ “ባለቤቴን ከእኔ እንደምታንስ ሳይሆን አስተዋይና ብቃት ያላት አጋር እንደሆነች አድርጌ ለመመልከት ጥረት አደርጋለሁ።”—ምሳሌ 31:10

5

ቅሬታ፦

“ባለቤቴ ቅድሚያውን አይወስድም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች።”​ምሳሌ 14:1

ባለቤትሽ ውሳኔ ለማድረግ ወይም ቤተሰቡን ለመምራት ቅድሚያውን የማይወስድ ከሆነ ቢያንስ ሦስት ምርጫዎች አሉሽ። (1) እያንዳንዱን ስህተት እየለቀምሽ ልትነግሪው ትችያለሽ ወይም (2) የራስነት ሥልጣኑን ልትነጥቂው ትችያለሽ አሊያም ደግሞ (3) ለሚያደርገው ማንኛውም ጥረት ከልብሽ ልታመሰግኚው ትችያለሽ። የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ምርጫዎች የምትከተይ ከሆነ ቤትሽን በገዛ እጅሽ ታፈርሽዋለሽ። ሦስተኛውን ምርጫ ከመረጥሽ ግን ትዳርሽን መገንባትና ማጠናከር ትችያለሽ።

በርካታ ወንዶች አክብሮት ማግኘትን ከመወደድ እንኳ አስበልጠው ይመለከቱታል። በመሆኑም ባልሽ ቤቱን በመምራት ረገድ እንደተሳካለትና ጥረቱ የሚደነቅ እንደሆነ በመግለጽ እንደሚከበር እንዲሰማው የምታደርጊ ከሆነ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ማሻሻያ ማድረጉ አይቀርም። እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ከባለቤትሽ ሐሳብ ጋር የማትስማሚበት ጊዜ ይኖራል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብላችሁ መወያየት ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 18:13) ሆኖም የምትመርጪው ቃልም ሆነ የድምፅሽ ቃና ትዳርሽን ለማፍረስ ወይም ለመገንባት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 21:9፤ 27:15) ስሜትሽን በአክብሮት ግለጪ። እንዲህ ካደረግሽ የምትፈልጊውን ውጤት ማግኘትሽ አይቀርም፤ በሌላ አማርኛ ባለቤትሽ ቅድሚያውን የሚወስድ ባል እንደሚሆንልሽ ጥርጥር የለውም።

አንዳንዶች ይህን ምክር የሠሩበት እንዴት ነው? በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውና ለ30 ዓመታት በትዳር ያሳለፈችው ሚሼል እንዲህ ትላለች፦ “እናቴ እኔንና ሁለት እህቶቼን ያሳደገችን ያለ ባል እርዳታ መሆኑ በጣም ኃይለኛና በራሷ የምትመራ ሴት እንድትሆን አድርጓታል። ይህ የእሷ ባሕርይ በእኔም ላይ ተጽዕኖ አድርጓል። በመሆኑም ለራስነት ሥልጣን ለመገዛት ምንጊዜም ጥረት ማድረግ አለብኝ። ለምሳሌ ለብቻዬ ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ባለቤቴን ማማከር እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።”

በአውስትራሊያ የምትኖረውና ከማርክ ጋር በትዳር ዓለም 21 ዓመታት ያሳለፈችው ሪቸልም ብትሆን አስተዳደጓ ተጽዕኖ አሳድሮባታል። እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ለአባቴ የራስነት ሥልጣን በፍጹም አትገዛም ነበር። በቤታችን ውስጥ ጭቅጭቅና መናናቅ የተለመደ ነገር ነበር። በትዳራችን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የእናቴን ዓይነት ባሕርይ አንጸባርቅ ነበር። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን አክብሮት በማሳየት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር መከተል ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። አሁን እኔና ማርክ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ደስተኛ ትዳር አለን።”

6

ቅሬታ፦

“የባለቤቴን ባሕርይ መታገሥ አልቻልኩም።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦

“አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”​ቆላስይስ 3:13

መጀመሪያ ስትጠናኑ የወደፊት የትዳር ጓደኛችሁ መልካም ባሕርያት ላይ ብቻ ስለምታተኩሩ ጉድለቱ አይታያችሁም ነበር። አሁንስ እንደዚያ ማድረግ አትችሉም? የትዳር ጓደኛችሁ ለቅሬታ ምክንያት የሚሆን ነገር ማድረጉ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ይሁንና ‘ትኩረት ማድረግ የምፈልገው በየትኛው የባለቤቴ ባሕርይ ላይ ነው? በጥሩው ወይስ በመጥፎው?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ።

ኢየሱስ በሌሎች ላይ የምናየውን ጉድለት አጋነን መመልከት እንደሌለብን የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ተጠቅሟል። “በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?” በማለት ጠይቋል። (ማቴዎስ 7:3) ጉድፍ በጣም ትንሽ ነገር ነው። በሌላ በኩል ግን ግንድ የአንድን ቤት ጣሪያ ደግፎ ሊያቆም የሚችል ትልቅ እንጨት ነው። ታዲያ ኢየሱስ ማስተላለፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? “በመጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።”—ማቴዎስ 7:5

ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ትኩረት ሊሰጠው በሚገባ ማስጠንቀቂያ ነው። “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:1, 2) አምላክ በዓይናችሁ ውስጥ ያለውን ግንድ ማለትም ጉድለቶቻችሁን ችላ ብሎ እንዲያልፍላችሁ የምትፈልጉ ከሆነ እናንተም የትዳር ጓደኛችሁን ስህተቶች ችላ ብላችሁ ማለፍ ይኖርባችኋል፤ ደግሞም እንዲህ ማድረጋችሁ በብዙ መንገድ ይጠቅማችኋል።—ማቴዎስ 6:14, 15

አንዳንዶች ይህን ምክር የሠሩበት እንዴት ነው? በእንግሊዝ የምትኖረውና ከሳይመን ጋር በትዳር ለዘጠኝ ዓመት ያሳለፈችው ጄኒ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ጊዜ የሚያበሳጨኝ ባለቤቴ አስቀድሞ እቅድ የማያወጣ ወይም ሁሉን ነገር በመጨረሻው ደቂቃ ማከናወን የሚፈልግ ሰው መሆኑ ነው። የሚገርመው ግን ስንጠናና በመጨረሻው ሰዓት ላይ ነገሮችን የሚያከናውን መሆኑን እወድለት ነበር። ይሁን እንጂ አሁን አሁን እኔም ችግር እንዳለኝ ማለትም መፈናፈኛ እንደማሳጣው ተገንዝቤያለሁ። እኔና ሳይመን አንዳችን የሌላውን ጥቃቅን ጉድለቶች ችላ ብሎ ማለፍን እየተማርን ነው።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው የሚሼል ባለቤት የሆነው ኩርት እንዲህ ብሏል፦ “በትዳር ጓደኛችሁ የሚያበሳጭ ባሕርይ ላይ ትኩረት የምታደርጉ ከሆነ ጉድለቱ ይበልጥ እየተጋነነ ይሄዳል። በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ሚሼልን እንድወዳት ባደረጉኝ ባሕርያት ላይ ትኩረት ማድረግ እመርጣለሁ።”

ለስኬት ቁልፍ የሆነው ነገር

ከላይ የተጠቀሱት ጥቂት ምሳሌዎች በትዳር ውስጥ ችግሮች መከሰታቸው እንደማይቀር ሆኖም ችግሮቹን መፍታት ከአቅማችን በላይ እንዳልሆነ ያሳያሉ። ታዲያ ለስኬት ቁልፍ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ቁልፉ ለአምላክ ያላችሁን ፍቅር ማሳደግና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ነው።

ለ20 ዓመት በጋብቻ ያሳለፉት አሊክስና ኢቶሃን የተባሉ በናይጄሪያ የሚኖሩ ባልና ሚስት ይህን ቁልፍ አግኝተዋል። አሊክስ እንዲህ ይላል፦ “የደረስኩበት አንድ እውነታ ቢኖር ባልና ሚስቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ እስካደረጉ ድረስ በጋብቻ ውስጥ የሚነሳ ማንኛውንም ችግር መፍታት ይችላሉ።” ባለቤቱ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “አዘውትሮ አብሮ የመጸለይን እንዲሁም ከልብ መዋደድና እርስ በርስ መቻቻል እንዳለብን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ የማድረግን ጠቀሜታ ተገንዝበናል። የተጋባን ሰሞን ከነበረው ሁኔታ አንጻር አሁን ምንም ችግር የለብንም ማለት ይቻላል።”

በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ተግባራዊ ምክር ቤተሰብህን ሊጠቅም ስለሚችልባቸው መንገዶች ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 14⁠ን እንዲያወያዩህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.63 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብረን ለማሳለፍ ጊዜ እንመድባለን?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከምቀበለው የበለጠ ለመስጠት እሞክራለሁ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለመግባባቶችን ለመፍታት ቅድሚያውን እወስዳለሁ?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውሳኔ ከማድረጌ በፊት ሚስቴን አማክራለሁ?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትዳር ጓደኛዬ መልካም ባሕርያት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ?