በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጣቸውን የሕክምና እርዳታ ይቀበላሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጣቸውን የሕክምና እርዳታ ይቀበላሉ?

ኢየሱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 9:12) ይህ የኢየሱስ አነጋገር ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ባለሙያዎች መሄድን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይከለክል ይጠቁመናል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጣቸውን መድኃኒትም ሆነ የሕክምና እርዳታ በደስታ ይቀበላሉ። በተጨማሪም ጥሩ ጤንነት እንዲሁም ረጅም ዕድሜ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እንዲያውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው እንደ ሉቃስ አንዳንዶቹ ሐኪሞች ናቸው።—ቆላስይስ 4:14

ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጩ የሕክምና ዓይነቶችን አይቀበሉም። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትን ለማርዘም ሲባል ደም መውሰድን ስለሚከለክል ደም እንዲሰጣቸው አይፈልጉም። (ዘፍጥረት 9:4፤ ዘሌዋውያን 17:1-14፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘በአስማታዊ’ ወይም በመናፍስታዊ ድርጊት መካፈልን የሚጠይቁ የሕክምና ዓይነቶችን ይከለክላል።—ኢሳይያስ 1:13 NW፤ ገላትያ 5:19-21

ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የማይጋጩ ሕይወት አድን የሕክምና ዓይነቶችን ይሰጣሉ። በበርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እነዚህ የሕክምና ዓይነቶች የአምላክን ሕግ ከሚጻረሩ የሕክምና ዓይነቶች ጋር ሲነጻጸሩ ብዙውን ጊዜ የተሻለ ጥራት አላቸው።

እርግጥ ነው፣ ከሕክምና ጋር በተያያዘ በርካታ አማራጮች አሉ። ለአንድ ሰው ፈውስ ያስገኘ የሕክምና ዓይነት ሌላውን ሰው ላይጠቅመው ይችላል። በመሆኑም ለሕመማቸው ትክክለኛ ምርመራ ወይም ሕክምና ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ሌላ ቦታ በመሄድ ድጋሚ መታየት ይመርጡ ይሆናል።—ምሳሌ 14:15

ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ዓይነት የሕክምና ምርጫ ላያደርጉ ይችላሉ። የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ጋር በማይጋጩ ጉዳዮች ረገድ ሕሊናቸው ሊለያይ እንደሚችል ይጠቁማል። (ሮም 14:2-4) በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ የቀረበለትን ማንኛውንም የሕክምና አማራጭ በሚገባ መመርመር ብሎም በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነው ሕሊናው ጋር እንደማይጋጭ ማረጋገጥ ይኖርበታል።—ገላትያ 6:5፤ ዕብራውያን 5:14

አንድ የይሖዋ ምሥክር በዚህ ረገድ የሚያደርገውን እያንዳንዱን ምርጫ፣ መኪና እያሽከረከረ የትራፊክ መጨናነቅ ወደሚበዛበት መስቀለኛ መንገድ ሲቃረብ ከሚያደርገው ውሳኔ ጋር ሊያመሳስለው ይችላል። ከፊቱ ያለውን መኪና ተከትሎ በፍጥነት በማሽከርከር መስቀለኛ መንገዱን ለማለፍ ቢሞክር ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። አስተዋይ የሆነ አሽከርካሪ ወደዚህ አካባቢ ሲቃረብ ፍጥነቱን በመቀነስ የትራፊኩን ሁኔታ ያጤናል። በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች ከሕክምና ጋር በተያያዘ ተቻኩለው ውሳኔ አያደርጉም፤ እንዲሁም የብዙዎችን ሐሳብ በጭፍን አይከተሉም። ከዚህ ይልቅ ያሏቸውን አማራጮች የሚያመዛዝኑ ከመሆኑም በላይ ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ይመረምራሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎች በትጋትና በሙሉ ልብ ለሚያከናውኑት ሥራ ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። በተጨማሪም እነዚህ ባለሙያዎች ለታመሙ ሰዎች ለሚሰጡት እፎይታ አመስጋኞች ናቸው።