“መጨረሻው” የተባለው ምንድን ነው?
“መጨረሻው” የተባለው ምንድን ነው?
“. . . ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
በአሁኑ ወቅት የዓለም መጨረሻን አስመልክቶ የማይባል ነገር የለም። ከቀልድ መጻሕፍት አንስቶ ሳይንሳዊ ይዘት እስካላቸው ፊልሞችና መጽሔቶች ድረስ ሁሉም በመዓት ቀን ይከሰታል ብለው ስለሚያስቡት መቅሰፍት ብዙ ይናገራሉ። ከሚነገሩት ነገሮች መካከል የኒውክሊየር ጦርነት፣ ተወርዋሪ ኮከቦች፣ አደገኛ የሆኑ ቫይረሶች፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ወይም ከሌሎች ዓለማት የሚመጡ ወራሪዎች የሚያስከትሉት እልቂት ይገኙበታል።
ሃይማኖቶችም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው፤ ብዙዎቹ ‘በመጨረሻው’ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት ሕያዋን ነገሮች በሙሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል ብለው ያስተምራሉ። አንድ የሃይማኖት ምሑር ማቴዎስ 24:14ን አስመልክተው እንዲህ የሚል አስፈሪ ሐሳብ ጽፈዋል፦ “ይህ ጥቅስ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት እጅግ ጠቃሚ ከሆኑት ሐሳቦች መካከል አንዱ ነው። . . . አሁን ባለው ትውልድ ላይ ብዙዎቻችን አሰቃቂነቱን ያልተገነዘብነው አውዳሚ የሆነ ጥፋት ተደቅኖበታል።”
እንዲህ ያለው አመለካከት ይሖዋ አምላክ ‘ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን’ እንዳልሆነ የሚናገረውን ወሳኝ ሐቅ ያላገናዘበ ነው። (ኢሳይያስ 45:18) በመሆኑም ኢየሱስ “መጨረሻው” ሲል ምድር ትጠፋለች አሊያም ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከምድረ ገጽ ይጠፋል ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ፍቅራዊ መመሪያዎች ለመከተል አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች ማለትም ክፉዎች ይጠፋሉ ማለቱ ነበር።
አንድ ምሳሌ እንመልከት። እጅግ ያማረ ቤት አለህ እንበል፤ በዚህ ቤት ውስጥ ሰዎች በነፃ እንዲኖሩበት ፈቅደህላቸዋል። አንዳንዶቹ ነዋሪዎች ከሌሎች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ከመሆኑም በላይ ቤትህንም በጥሩ ሁኔታ ይዘውታል። ሌሎቹ ነዋሪዎች ግን ችግር ይፈጥራሉ፣ እርስ በርስ ይጋጫሉ እንዲሁም ሰላማዊ በሆኑት ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ።
እነዚህ ዓመፀኞች ንብረትህን ከማበላሸታቸውም በተጨማሪ መጥፎ ድርጊታቸውን ለማስቆም የምታደርገውን ጥረት ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም።ታዲያ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን እርምጃ ትወስዳለህ? ቤትህን ታፈራርሰዋለህ? እንደዚህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ዓመፀኞቹን ነዋሪዎች ከቤትህ አባረህ እነሱ በቤቱ ላይ ያደረሱትን ጉዳት ታስተካክላለህ።
ይሖዋም ቢሆን የሚያደርገው ተመሳሳይ ነገር ነው። መዝሙራዊው በመንፈስ ተገፋፍቶ የሚከተለውን እንዲጽፍ አድርጓል፦ “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:9-11
ሐዋርያው ጴጥሮስም ስለዚሁ ጉዳይ ተናግሯል። ጴጥሮስ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከጥንት ጀምሮ ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ደረቁ ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንቶ እንደቆመና በውኃ መካከል እንደነበረ [አያስተውሉም]፤ . . . በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል።” (2 ጴጥሮስ 3:5, 6) እዚህ ላይ ሐዋርያው የጠቀሰው በኖኅ ጊዜ ስለተከሰተው የጥፋት ውኃ ነው። በዚያን ወቅት ፈሪሃ አምላክ ያልነበራቸው ሰዎች ጥፋት የመጣባቸው ሲሆን ምድር ግን አልጠፋችም። ዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ “ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ [ይሆናል]።”—2 ጴጥሮስ 2:6
ጴጥሮስ አክሎም “አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳት . . . ተጠብቀው ይቆያሉ” በማለት ጽፏል። ይህንን ሐሳብ ብቻ ካየን የተሳሳተ አመለካከት ልንይዝ እንችላለን። ይሁንና ጥቅሱ “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት” እንደሚልም ልብ በል። ይጠፋሉ የተባለው ምድር ሳትሆን ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ቀጥሎስ? ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና [የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት] አዲስ ምድር [ጻድቅ የሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ] እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።”—2 ጴጥሮስ 3:7, 13
ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች “መጨረሻው” የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ማቴዎስ 24:3-14ን እና 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን በማንበብ መጨረሻው ቅርብ እንደሆነ አንተው ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ። *
አንድ ትንሽ ልጅ እንኳ በቀላሉ ሊረዳው የሚችለውን ማቴዎስ 24:14ን አስመልክቶ ይህን ያህል ግራ መጋባት መፈጠሩ የሚያስገርም አይደለም? ይህ የሆነበት በቂ ምክንያት አለ። ሰይጣን፣ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች እንዳይረዱ አሳውሯቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) በተጨማሪም አምላክ ዓላማውን የሚገልጠው ለትዕቢተኞች ሳይሆን ለትሑታን ነው። ይህንን በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥክላቸው በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ።” (ማቴዎስ 11:25) በእርግጥም የአምላክን መንግሥት ምንነትና ይህ መንግሥት እሱን ለሚደግፉ ሰዎች የሚያመጣቸውን በረከቶች በትክክል ከተገነዘቡ ሰዎች መካከል መሆን እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.11 የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9ን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንግሥት ‘በመጨረሻው’ ጊዜ በምድር ላይ ያለውን ክፋት ሁሉ ያስወግዳል